1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመገናኛ ብዙኃን ቅኝት

ዓርብ፣ ነሐሴ 24 2011

በተገባደደው ሳምንት የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረቦች በአደባባይ ሰው ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ከተሰራጨ በኋላ ተቋሙ እና ጸጥታ ለማስከበር ያሰማራቸው አባላቱ ጉዳይ ዋንኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። የትምህርት እና ፍኖተ-ካርታ ያነሳቸው ውዝግቦች ዛሬም አልበረዱም። 

https://p.dw.com/p/3Ol6G
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የመገናኛ ብዙኃን ቅኝት

ባለፈው ሰኞ አቤል ደ. የተባሉ ሰው በትዊተር ገፃቸው ያጋሩት 35 ሰከንዶች የሚረዝም ቪዲዮ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና የመነጋገሪያ ርዕሰ-ጉዳይ አድርጎት ሰንብቷል። ጉዳዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ በፌስቡክ ገፁ ማብራሪያ እንዲሰጥ ዘግየት ብሎም ይቅርታ እንዲጠይቅ አስገድዶታል። 

በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በርካቶች ያሻቸውን ርዕስ እየሰጡ ሲቀባበሉት በከረሙት ቪዲዮ የመጀመሪያ ሰከንዶች አንድ የፖሊስ ባልደረባ አንድን ግለሰብ ሲደበድብ ይታያል። በቅርበት ሆነው ተደብዳቢውን ለመገላገል የሞከሩ እንስትንም ይገፈትራል። በቦታው የነበረ ሌላ የፖሊስ ባልደረባ በርከት ያሉ ሰዎች ባሉበት አንድ ጥይት ወደ ሰማይ ይተኩሳል። 

አቤል ደ. በትዊተር ገፃቸው ባጋሩት ቪዲዮ ሥር «ለደኅንነታችን የጸጥታ አስከባሪ የደንብ ልብስ በለበሱ ወንዶች እና ሴቶች ላይ ጥገኞች ነን። ለማኅበረሰቡ አደጋ በሆኑ ጊዜ ደግሞ ስህተታቸውን በይፋ እንናገራለን» የሚል አስተያየት ያሰፈሩት ብሌን መሐመድ ምስሉን ላጋሩት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። 
ናትናኤል ሰለሞን ደግሞ «ይኸ ከሕግ በላይ መሆን ነው። ምክንያቱ ምንም ቢሆን ተጠቂው የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል። ፖሊሶቹ ክስተቱን ከማረጋጋት ይልቅ ማባባስን መርጠዋል» ሲሉ ተችተዋል። ክብሩ ይስፋ « ሰውዬው እኮ እጁ በካቴና ታስሮ መሬት ላይ ከፖሊሱ እግር ስር ነው ወድቆ የሚታየው። ያ ሁሉ ቡጢ፣ ግፍተራ፣ የተኩስ እሩምታ፣ የአካባቢውን ሰላም ብጥበጣ ለምን አስፈለገ? ሰውዬው በምንም ይጠርጠር ድብደባው ኢ-ሰብዓዊ ነው» ሲሉ ወቅሰዋል። 
 

ምን ተፈጠረ?

አቤል ደ. እንዳሉት ኩነቱ የተፈጠረው ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3:50 ሰዓት በአዲስ አበባ በተለምዶ ቄራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ወደ ጎፋ ገብርኤል ቤተ-ክርስትያን የሚወስደው መንገድ ላይ ነው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ኩነቱ የተፈጸመው ባለፈው ሰኞ «ከረፋዱ 5 ሰዓት ባለው ጊዜ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ቄራ ጎፋ ማዙሪያ አካባቢ» ነው። 

ፖሊስ «በድለላ ስራ ላይ በተሰማሩ ሁለት ቡድኖች መካከል የተፈጠረን አለመግባባት ለመዳኘት ወደ ቦታው ያቀኑ ሁለት የፖሊስ አባላት ያለመግባባቱን ለማብረድ የሁለቱም ቡድን አባላት ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄዱ በሚጠይቁበት ወቅት አለመግባባቱ ተካሮ የፖሊስ አባላቱ ጥይት የተከሱና በሰዎች ላይ ድብደባ መፈፀማቸው» ገልጿል። 
«የፖሊስ አባላቱ አዲስ እና በቅርቡ ሰራዊቱን የተቀላቀሉ» ቢሆኑም ድርጊቱ ግን «ተገቢ እና ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ ጉዳያቸው በወንጀልና በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት እየተጣራ» መሆኑን መግለጫው ይጠቁማል። ለፌስቡክ ተጠቃሚው ጸጋዬ አቶ ግን ፖሊስ የሰጠው ማብራሪያ አልተዋጠላቸውም። ጸጋዬ «አዲስ የሚባል ነገር የለም። ሁሉም ሰልጥኖ አና ሕግ እና ደንቡን አክብሮ መሠለኝ የተቀጠረው» ሲሉ የተቋሙን ማብራሪያ ተችተዋል። ይቤ ጆናሕ ደግሞ «"የፖሊስ አባለቱ አዲስ እና በቅርቡ ሰራዊቱን የተቀላቀሉ መሆናቸውን" ብላችሁ ከወዲሁ ጉዳዩን ለማቅለል አትሞክሩ። የሕግ የበላይነት ይከበር። ሌላው ዜጋ ወንጀል ሲሰራ እንደሚጠየቀው ሁሉ ፖሊስም ሆነ ሌላው የጸጥታ አካል መጠየቅ አለበት። ከወዲሁ ተሸፋፍኖ እንዲያልፍ የሚደረገውን የትኛውንም ጥረት እንቃወማለን» ብለዋል። 

ክብሮም ጸጋይ «ይህ ምንም ማጣራት አያስፈልገውም። ሺ ጊዜ ወንጀለኛ ይሁን የሰው ልጅ በአደባባይ በፖሊስ ሲቀጠቀጥ ማየት መልካም ስምና ዝናችሁ ከድጥ ወደ ማጡ ያደርገዋል። እናም በቅርቡ የተወሰደባቸውን እርምጃ ይፋ እንደምታደርጉ ተስፋ እናደርጋለን» የሚል መልዕክት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስተላልፈዋል። 
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን «ለተፈጠረው ነገር» ይቅርታ ጠይቀዋል። 

ሲራክ አስፋው በሌላ አገር የተፈጠረ ተመሳሳይ ክስተት የሚያሳይ ቪዲዮ አያይዘው «ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሆላንድም ከፖሊስ ጋር እንደዚህ ግጭት ሊኖር ይችላል።ፖሊስ ኃይል የመጠቀም ህጋዊ መብት ስላለው ምክንያቱን ሳናውቅ ፖሊስም ሆነ ታሳሪ ላይ ከመፍረድ እንቆጠብ።እንደዚህ እየቀረጹ ማሳየቱ ግን ለህግ አስከባሪው ትምህርት ይሰጣል» የሚል አስተያየታቸውን አስፍረዋል። 

ዳዊት ተስፋዬ ግን «ፖሊስ ኃይል የመጠቀም ህጋዊ መብት አለው» በሚለው ጉዳይ ላይ የተለየ ሐሳብ አላቸው። ዳዊት «ፖሊስ ኃይል የመጠቀም ህጋዊ መብት ስላለው.. የሚል ከአውዱ ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ሀረግ በመጥቀስ የማይነፃፀሩ ሁኔታዎችን ነው ያነፃፀርከው። እዚህ ስላለው ሕግ-ዐልባ የፖሊስ ጭካኔ ጥቂት ግንዛቤ ካለህ ይሄንን አትልም ነበር» ሲሉ ለአቶ አስፋው ምላሽ ሰጥተዋል። 

ትዕግስት በቀለ በዚያው በትዊተር መንደር «ፖሊስ ህግ አስከባሪ እንጂ ህግ ጥሷል ያለውን ሰው እንደፈለገው ደብዳቢ መሆን የለበትም። ማንም ሰው ሕግን ቢጠስ ለሕግ ቀርቦ ቅጣቱን መቀበል አለበት እንጂ በፖሊስ መደብደብ ፈፅሞ የለበትም» ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል። 

አሉላ ኃይሉ «የኢትዮጵያ የፖሊስ ኃይሎች ቀን በቀን የሚያደርጉት ነገር ነው። እንዲህ አይነት ሕገ-ወጥ ጭካኔና የሰብዓዊ መብት መጣስ የተለመደ ነው። የበሰበሰ ባሕላዊ ችግር ነው። የኢትዮጵያ ፖሊስ በሙሉ ባሕላዊ ለውጥና የተሟላ ስልጠና ያስፈልገዋል» የሚል ጥቆማ ሰጥተዋል። 

ታደሰ ዘገየ «በኛ ሀገር የፖሊስ ሙያ ተመርጦ ወይም በፍላጎት የሚገባበት ስላልሆነ ከዚህ የተሻለ ነገር መጠበቅ የለብንም። በትምህርቱ ውጤት ያልመጣለት ወይም ስራ ስታጣ የምትገባበት ሙያ ፖሊስነት ነው።ሲመረቁ እንኳን ሕገ-መንግሥቱን ለመጠበቅ ብለው ነው እንጂ የሰውን ሰብዓዊ መብት ማክበር እንዳለባቸው አያስተምሯቸውም። ካኪውን ሲለብሱ ፍጥረት ሁሉ ከነሱ በታች መስሎ ነው የሚታያቸው። ለማንኛውም የሕዝብ አገልጋይ መሆናቸውን አስረግጣችሁ ብትነግሯቸው መልካም ነው» የሚል ጥቆማ ሰጥተዋል። 

አማኑኤል «ይሄ በአጋጣሚ ስለተቀረፀ እንጂ በየቦታው በስመ-ሕግ ማስከበር የሚደበድቡ ወገኖቻችን ብዙ ናቸው። ደግሞም ሕዝብ እንዳይጠላን ብላችሁ የተጠቀማችሁበት ዘዴ እንጂ ፖሊሱ አይቀጣም። የሚያሳዝነው ደግሞ የፖሊስ ባልደረባው ጓደኛው በደምብ እንዲደበድብለት ጥይት እየተኮሰ ይከላከልለታል። አይ አገሬ ኢትዮጵያ» ብለዋል። 
 

መቋጫ ያላገኘው የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው ጉዳይ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የኢትዮጵያ መንግሥት ያዘጋጀውን የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ አጥብቆ በመተቸት ከተቃወሙት ጎራ ተቀላቅሏል። ኦነግ በትናንትናው ዕለት በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ «እንደ አዲስ ተቀረጸ የተባለዉ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ከአንድ ወገን በተሰባሰቡ ግለሰቦች ምክረ ሀሳብ የተነደፈ ከመሆኑም ባሻገር አገሪቱን ሃምሳ ዓመትና ከዚያ በላይ ወደ ኋላ በመመለስ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ለዘመናት ባደረጉት መራራ ትግልና በከፈሉት መስዋዕትነት ቢያንስ የተጎናጸፉዋቸው የተወሰኑ መብቶችን እንኳ ለመግፈፍ ሆን ተብሎ የተጠነሰሰ ሴራ ነው ብለን እናምናለን» ብሏል። 

በፍኖተ-ካርታው ከፍተኛ ውዝግብ ካስነሱ ጉዳዮች መካከል የፌድራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት አይነት ሊሰጥ ይገባል የሚለው ሐሳብ ይገኝበታል።  ኦነግ ታዲያ «ሕጻናትን ከምርጫቸው፣ ከፍላጎታቸውና ፈቃዳቸው ዉጪ የራሳቸው ያልሆነውን ቋንቋ እንዲማሩ ማስገደድ የብሄሮችን ነፃነት መግፈፍ በመሆኑ» በጽኑ እንደሚቃወመው አስታውቋል። 

Symbolbild: Pinterest
ምስል picture alliance/X. Gs

ምስክር ቢራቱ «የስምንተኛ ክፍል ፈተና ብሔራዊ መሆኑ ትክክል ነው። ከዛ ባሻገር ግን ከቋንቋ ጋር ተያይዞ የተነሳው እና በብዙዎች ዘንድ ቅሬታን ያስነሳው የፌድራል የስራ ቋንቋ(አማርኛ ቋንቋ) እንደ አንድ የትምህርት አይነት ይሰጥ የተባለው ምክረ-ሃሳብ በእኔ ግምት ተግባራዊ ቢሆን እና ክልሎች እንደ አንድ የትምህርት አይነት ከ3ኛም ይሁን ከ5ኛም ክፍል ጀምሮ ቢሰጡ ለህዝባችን ጠቀሜታው የጎላ ነው በቅንነት ካሰብን። በመሆኑም እንደ ደቡብ ክልል ይህ የአማርኛ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት አይነት ቢሰጥ ምርጫዬ ነው» ብለዋል። 

የትምህርት ሚኒስቴር ባለስጣናት በሳምንቱ በሰጡት መግለጫ የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው የክልል መንግሥታት የፌድራል የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ ማስተማር የሚጀምሩበትን ደረጃ አልወሰነም ሲሉ እየከረረ የሔደን ተቃውሞ ለማለዘብ የታቀደ የሚመስል ማብራሪያ ሰጥተዋል። የኦሮሚያ እና የትግራይ ክልላዊ መንግሥታት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ካነሱ መካከል ይገኙበታል። የትምህርት ምኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ታዲያ የክልል መንግሥታት ግልፅ መሆን በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ መስጠታቸውን ገልጸው «ፍኖተ-ካርታውን እንቀበላለን፤ አንቀበልም የሚል አልሰማሁም» ብለዋል። 

የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታው ዓላማዎች «በምንም ዓይነት ተዓምር የፌድራል ሥርዓታችንን የሚፈታተኑ» አይደሉም ያሉት የትምህርት ሚኒስቴር ምኒስትር ድዔታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ «የፌድራል የሥራ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት አይነት ይሰጥ የሚለው የፍኖተ-ካርታው ምክረ-ሐሳብ ነው» የሚል ማብራሪያ በትናንትናው ሰጥተዋል። «በምን ደረጃ ልስጥ የሚለው የክልሎች ሥልጣን ነው። ክልሎች ከአምስተኛ ክፍል ፤ ከሰባተኛ ክፍል [ጀምሮ ለማስተማር] ሊወስኑ ይችላሉ። አይጠቅመንም ካሉ ሊተዉ ይችላሉ» ብለዋል።  

እሸቴ በቀለ
ተስፋለም ወልደየስ