1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዳጊዎቹ ሀገሮችና ያውሮጳው ኅብረት ድርድር

ሰኞ፣ ጥር 3 1996
https://p.dw.com/p/E0g4
የአውሮጳው ኅብረት በመስከረምና በጥቅምት ከምዕራብና ከማዕከላይ አፍሪቃ ሀገሮች ጋር ስለ ኤኮኖሚ ትብብር ድርድሩን አንቀሳቅሷል። በኮቶኑው ስምምነት ሥር ከአፍሪቃ፣ ከከራይብና ከፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች ጋር የሚደረገው ድርድር ለአምስት ዓመታት እንደሚዘልቅ ነው የሚጠበቀው።

ባለፈው መስከረም በካንኩን/ሜክሲኮ የተካሄው የዓለም ንግድ ድርድር ለጊዜውም ቢሆን ከከሸፈም በኋላ ከአውሮጳው ኅብረት ጋር በንግድና በልማት ትብብር የተጣመሩት ፸፱ኙ የአፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ/በአሕጽሮት አከፓ/ሀገሮች የተሥፋ ምልክት አላጡም፥ አከፓ-ሀገሮች ከአውሮጳው ኅብረት ጋር የሚያካሂዱት የንግድ ድርድር በካንኩን/ሜክሲኮ ከደረሰው ከዓለም ንግድ ድርጅት የድርድር ክሽፈት እንዲላቀቅ ተደርጎ በሂደቱ ቀጥሏል። የአውሮጳው ኅብረትና አከፓ-ሀገሮች እ.ጎ.አ. በ፪ሺ ኮቶኑ/ቤኒን ውስጥ የደረሱት ስምምነት የንግድ ግንኙነታቸው እንዲፍታታና ነፃ እንዲሆን ያዋውላል። እንዲያውም፥ የአውሮጳው ኅብረት በዚሁ ስምምነት ሥር እጅግ ድሆች የሆኑት ተጣማሪዎቹ አዳጊ ሀገሮች ለሚልኳቸው ለመላው ሸቀጦቻቸው(ከጦር መሣሪያ በስተቀር) የገበያውን በር ክፍት ለማድረግም ነው ቃል የገባው።

ባለረው መፀው ነበር የአውሮጳው ኅብረትና አከፓ-ሀገሮች ስለኤኮኖሚያዊው የትብብር ስምምነት ይፋውን ድርድር የጀመሩት። ለልማት መርሕ ኃላፊ የሆኑት የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን ተጠሪ ፓውል ኒልሶን በዚህ ረገድ ብሩህ ተሥፋ ነው የሚታያቸው፣ በዓለም ንግድ ድርጅት ሥር ከሚካሄደው የንግድ ድርድር ይልቅ ከአውሮጳው ኅብረት ጋር የሚደረገው ንግግር ለመልካም ፍፃሜ የተሻለ የስኬት ዕድል ያለው ሆኖ ነው የሚታየው።

በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሃያ-አምስት የሚሆኑት የአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገሮችና ፸፱ኙ አከፓ-ሀገሮች እ.ጎ.አ. እስከ ፪ሺ፰ ድረስ የኤኮኖሚ ጥምረታቸውን ድርድር የሚያከናውኑት እንደሚሆኑ ነው የሚጠበቀው። በኮሚሲዮኑ የልማት ተጠሪ ፓል ኒልሶን አመለካከት መሠረት፣ በአውሮጳው ኅብረትና በአከፓ-ሀገሮች መካከል ባለው የንግድ ግንኙነት ረገድ ዋና እክል ሆኖ የሚታየው የንግዱ ግደባ ሳይሆን፣ በራሳቸው በአፍሪቃውያቱ ጎረቤት-ሀገሮች መካከል ያለው የንግዱ እንቅፋት ነው። ፓል ኒልሶን እንደሚሉት፣ አፍሪቃውያኑ መንግሥታት የሞኖፖል ኣቅዳቸውን በመጠበቅ፣ ለአካባቢያዊው ውድድር በራቸውን ይዘጋሉ። ይህ ነው ዋናው የትብብር እንቅፋት፥ ፖል ኒልሶን እንደሚያስገነዝቡት።

ለብዙዎቹ አከፓ-ሀገሮች የአውሮጳው ኅብረት ነው ዋነኛው የንግድ ጣምራ። የአውሮጳው ኅብረት ከውጭ ከሚያስመጣቸው ሸቀጦች መካከል የአከፓ-ሀገሮች ድርሻ 3.11 በመቶ ብቻ ነው፤ ዝንባሌው ይ’ብሱን የሚያንስም ነው የሚመስለው። የአውሮጳው ኅብረት ከአከፓ-ሀገሮች የሚያስመጣቸው ሸቀጦች ይዘት በሃያ-ኣምስት ዓመታት ውስት በግማሽ የተቀነሰ ሆኖ ነው የሚታየው። ከአውሮጳው ወደ አፍሪቃ ሀገሮች የሚሸጋገሪውም ውዒሎተንዋይ ጭምር ነው እየተቀነሰ የሄደው። ከሰባት ዓመታት በፊት በአፍሪቃ አኳያ 2.8 በመቶ የነበረው የውዒሎተንዋይ ሽግግሩ ድርሻ አሁን ወደ 1.5 በመቶ ነው ያሽቆለቆለው። ለዚሁ ተጠያቂ ሆኖ የሚታየው ጦርነት፣ የሙስና መስፋፋትና የመዋቅሮች ኋላቀርነት ነው። የልማት ትብብር ተጠሪው ፓል ኒልሶን አሁን እንደሚያስገነዝቡት፣ ባለወረቶችን ለማማለል ይቻል ዘንድ፣ የምዕራብና የማዕከላይ አፍሪቃ መንግሥታት አካባቢያዊ ገበያዎችን ማጠናከር ይኖርባቸዋል።

የአውሮጳው ኅብረት ድርድር በሚያደርግበት ጊዜ የኤኮኖሚ ኃይሉ ትንንሾችን እንዲጫን ያደርጋል በማለት መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶችና አንዳንድ አከፓ-ሀገሮች የሚያቀርቡትን ሂስ ዴንማርካዊው የልማት ኮሚሳር ፖል ኒልሶን ያስተባብላሉ። በእርሳቸው አመለካከት መሠረት የአውሮጳው ኅብረት ኤኮኖሚያዊ ኃይል ለሚደረጁት ሀገሮች ጠቃሚ ሆኖ ነው የሚታየው--ይኸው የኤኮኖሚ ላቂያ ባይኖር ኖሮ፣ ለሚደረጁት ሀገሮች የልማት ርዳታ መስጠት ባልተቻለም ነበር ይላል የፖል ኒልሶን ማስገንዘቢያ።

፲፭ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገሮች ከሚጣመሩበት አካባቢያዊ የኤኮኖሚ ማኅበር(ኤኮዋስ) ጋር ድርድር በተጀመረበት ወቅት አፍሪቃውያኑ ልዑካን ያቀረቡት ስሞታ የአውሮጳው ኅብረት ሐሳቦቹንና ጥቅሞቹን ያስፈጽማል--በተለይም በወጭ ድጎማ የሚረክሰው የአውሮጳው ኅብረት ሀገሮች ጥጥ ከምዕራብ አፍሪቃ የሚላከው ጥጥ አለአግባብ የገበያ ውድድር አቅም እንዲያጣ ያደርገዋል የሚል ነበር። አከፓ-ሀገሮች በጥጥ ብቻ ሳይሆን፣ በስኳሩም ገበያ ነው እክል የሚደቀነው። በአውሮጳው ኅብረት ዙሪያ የስኳርም ምርት በወጭ ድጎማ የሚደገፍበትና በዚህ አኳን የሚረክስበት ሁኔታ በአከፓ-ሀገሮች ውስጥ የሚመረተው ስኳር የገበያ ውድድር አቅም እንዲያጣ ያደርገዋል። በስኳር ምርት ረገድ ይኸው የድጎማ ተግባር ቀስበቀስ እንዲወገድ ለማድረግ ይቻል ዘንድ፣ የግብርና ሚኒስትሮች አሁን በመጭው ሚያዝያ አንድ ጉባኤ ከፍተው አዲስ መርሐግብር እንደሚዘረጉ ነው የሚጠበቀው።