1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የአገረ-ሰብ ዝርያዎች ላይ ጥገኛ የሆነው ዶሮ እርባታ

ረቡዕ፣ ግንቦት 15 2010

በኢትዮጵያ የሚገኙ ተመራማሪዎች በሽታ እና የአየር ጠባይ ለውጥን መቋቋም የሚችሉ የዶሮ ዝርያዎች ለማዳቀል ጥረት ላይ ናቸው። ውጤቱ የአገረ-ሰብ ዝርያዎች ላይ ጥገኛ ለሆነው ዶሮ እርባታ መፍትሔ እንደሚሆን ባለሙያዎች እምነት አላቸው።

https://p.dw.com/p/2yDDQ
Vogelgrippe in den Niederlanden (Symbolbild)
ምስል picture-alliance/dpa/J. Stratenschulte

ተመራማሪዎች በሽታ እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋሙ የዶሮ ዝርያዎች ለማዳቀል እየጣሩ ነው

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው ዓለም አቀፉ የእንስሳት ጥናት ተቋም (ILRI) የአየር ጠባይ ለውጥ እና በሽታዎችን የሚቋቋም የዶሮ ዝርያ በማዳቀል አርቢዎችን የማገዝ ውጥን ሰንቋል። የተቋሙ ተማራማሪዎች የአገረ ሰብ ዶሮዎችን ዘረ-መል በማጥናት ላይ ይገኛሉ። አላማቸው ጠንካራ የዶሮ ዝርያዎችን ማዳቀል መሆኑን የዘረ-መል ተመራማሪው ፕሮፌሰር ኦሊቨር ሐኖቴ ይናገራሉ።

"ዶሮ እና የቀንድ ከብት ለመሳሰሉ እንስሳት የዝርያ ብዛት ለምርት መጨመር ወሳኝ ነው። እንስሳት እና ዶሮዎች በፍጥነት እንዲያድጉ፣ ብዙ እንቁላል እንዲጥሉ፣ በሽታ እና ተለዋዋጩን የአየር ጠባይ እንዲቋቋሙ ከፈለግን ከበርካታ ዝርያዎች መካከል መምረጥ ይኖርብናል። ካለ ዝርያ ብዝኃነት የእርባታ መሻሻል አይኖርም "

ተቋሙ በቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ የግብረ-ሰናይ ድርጅት የሚደገፈው እና በአፍሪቃ የዶሮ ዘረ-መል ላይ የሚደረገው ሰፊ ጥናትና ምርምር አንድ አካል ነው። እጅግ በርካታ ከሚባለው የዶሮ ዘረ-መል አማራጭ የተሻለውን በገጠራማ አካባቢ ለሚገኙ የዶሮ አርቢዎች ማቅረብ የዚህ ሥራ ዋንኛ ዓላማ ነው። ከተመራማሪዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ታደለ ደሴ "በዚህ ቅጥር ግቢ የዶሮ ዝርያዎችን እና ምርታማነት ለማሳደግ የምንሠራው ሥራ በኢትዮጵያ እና በሌሎች አካባቢዎች ወደ ሚገኙ አነስተኛ ገበሬዎች ወርዶ ተጠቃሚ ያደርጋል" ሲሉ ተስፋቸውን ተናግረዋል።

ይኸ እቅድ ትኩረቱ የዘረ-መል ጥናት ብቻ ላይ አይደለም። ማዕከሉ ከየአካባቢው የአየር ጠባይ አኳያ ዘላቂነት ያላቸው ባህላዊ የእንስሳት እርባታ ዘዴዎችን ያበረታታል። ዶ/ር ኃይሉ መለሰ እንዲህ አይነት ዘዴ ሕንድ እና ብራዚልን በመሳሰሉ አገራት ተግባራዊ ሆኖ ውጤት ማስገኘቱን ይናገራሉ። የምርምር ሥራው ረዥም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ለመሳካቱ ግን እርጠኛ አይደሉም።

በተለምዶ የሐበሻ ተብለው የሚታወቁት የዶሮ ዝርያዎች ጣዕም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተወደደ መሆኑ ሌላው ፈተና ነው። በርካቶች ለተዳቀሉ የዶሮ ዝርያዎች ሥጋም ይሁን ለእንቁላሎቻቸው ያለው ፍላጎት አናሳ ነው። ይህ ችግር ለረዥም ጊዜ ፈተና እንደነበር ራሔል ታስታውሳለች። በሂደት ግን ኢትዮጵያውያን ሸማቾች ፊታቸውን ወደ ተዳቀሉ የዶሮ ሥጋዎች እና እንቁላሎች ማዞር መጀመራቸውንም ታዝባለች። ዶ/ር ኃይሉ ኢትዮጵያውያን የዶሮ ሥጋ ዝግጅታቸውን ቢፈትሹ መልካም ነው የሚል ዕምነት አላቸው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ