1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃና የጀርመን ወጣቶች ግጭት በምሥራቅ ጀርመን

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2000

ማግደንቡርግና አካባቢዋ በዉጪ ተወላጆች ላይ በሚሰነዘር ጥቃት ስም ሲያበጁ ባንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ያሁኑ ሁለተኛቸዉ ነዉ

https://p.dw.com/p/E87F
አፍቃሬ ናሲዎቹ
አፍቃሬ ናሲዎቹምስል PA/dpa

የአፍሪቃና የጀርመን ወጣቶች ግጭት በምሥራቅ ጀርመን

በምሥራቅ ጀርመናዊቷ ከተማ ማግደንቡርግ የአፍሪቃ ዝርያ ባላቸዉ ወጣቶችና በጀርመን ወጣቶች መካከል በተቀሰቀሰዉ ግጭት በትንሹ ሁለት ሰዎች ክፉኛ ቆሰለ።ለጥቃቱ ተጠያቂ የሆኑትን ሰዎች ለመለየት ፖሊስ የሚያደርገዉን ምርመራ እንደቀጠለ ነዉ።የዶቼ ቬለ የእንግለዘኛ ክፍል ባልደረባ ሐርዲ ግራዉፕነር እንደዘገበዉ የጠቡ መነሻ የዉጪ ተወላጆች መፍራትና መጥላት ያስከተለዉ ሳይሆን አይቀርም።ማግደንቡርግ እና አካባቢዋ ጥገኝነት የሚጠይቁና የሚሰሩ የዉጪ ተወላጆች ጥቃት ሲደርስባቸዉ ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም።ዝር ዝሩን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ማግደንቡርግና አካባቢዋ በዉጪ ተወላጆች ላይ በሚሰነዘር ጥቃት ስም ሲያበጁ ባንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ያሁኑ ሁለተኛቸዉ ነዉ።ካንድ ወር ነች ዘረኞች የአፍሪቃ እና የኢራቅ ተወላጆችን ደብድበዉ ነበር።ድበድባዉ በቀድሞዋ ኮሚስታዊት ግዛት ምሥራቅ ጀርመን ዘረኝነት ሥር እየሰደደ ለመምጣቱ ማረጋገጪያ ነዉ-አይደለም አካራክሮ ሳያበቃ-ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ድብደባዉ ተደገመ።አንድ የከተማይቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ እንደሚለዉ ያሁኑን ጠብ የጫሩት እንደከዚሕ ቀደሙ ጀርመኖቹ አይደሉም።እንድ አፍሪቃዊ ወጣት እንጂ።

ወጣቱ ሥብሰብ ብለዉ የነበሩ የጀርመን ወጣቶችን በነገር ለካከፋቸዉ።በቃ ነጩ ወጣት ጥቁሩን ጥቁሩ ነጩን እያሳደደ ይከታተኩ ገቡ።ጥቁሮቹን እያሰደዱ ይደበድቡ ከነበሩት መካካል ግን ቢያንስ አራቱ የዉጪ ዝርያዎችን የሚያንቋሽሽ መፍክር ያሰሙ ነበር።-ይላል ፖሊስ።እና በፖሊስ ግምት እነዚሕ አራቱ የቀኝ ፅንፈኞቹ የአፍቃሬ ናሲ ቡድን አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም።

ቀኝ ፅንፈኞቹ በሰዉና በንብረት ላይ ከሚያደርሱት ቀጥተኛ ጉዳት በተጨማሪ በምጣኔ ሐብት አቅሟ ከምዕራቡ ጋር ለመስተካከል የምትፍጨረጨረዉን የምሥራቅ ጀርመንን ግዛት መጉዳቱ አልቀረም።ባለሐብቶችን የሚያግባባና የሚያማክረዉ ኢቨስት ኢን ጀርመኒ የተሰኘዉ ድርጅት ባልደረባ ቤቲና ክናበ እንደሚሉት ግን ድርጅታቸዉ ዘረኝነትን የሚፈራ ባለሐብት አላጋጠመዉም።

«እንደ እድል ሆኖ ኢንቨርስት ኢን ጀርመኒ፣ በዉጪ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት በመፍራት መዋዕለ ንዋያቸዉንን ጀርመን ዉስጥ አናዉልም ያሉ ሰዎች አጋጥመዉት አያዉቁም።ኢንቨስት ኢን ጀርመኒ ከሚያማክራቸዉ ባለሐብቶች መካካል እንዲሕ አይነት ችግር የደረሰበት ሥለመኖሩ የደረን መረጃ የለም።»

ይሁንና ለሥራ አጦች ሥራ ለማስገኘት፤ ምጣኔ ሐብቷን ለማሻሻል፣ ከተቻለም ከምዕራባዊዉ ግዛት እኩል ለማደግ አበክራ በምትፍጨረጨረዉ ምሥራቃዊ ጀርመን በዉጪ ዜጎች ላይ የሚፈፀመዉ ጥቃት መደጋጋም ግዛቲቱ የምትፈልገዉን አሁን ባያሳጣ ለወደፊቱ ማስጋቱ አልቀረም።-በክናበ እምነት፤-

«ለወደፊቱ ሁኔታዉ በዚሁ ለመቀጠለ ምንም አይነት ዋስትና የለም።እንዲሕ አይነቶቹ አጋጣሚዎች የጀርመንን ስም ማጉደፉ፣ መዋዕለ ንዋይን ለማሰራት ለሚያስፈልገዉ ምቹ ሁኔታን ማጥፋቱ አይቀርም።»

ማግደቡርግ የናትሲን መርሕ-የሚቃነቅኑ አንድ መቶ ቀኝ ፅንፈኞች እንዳሉባት ይታወቃል።የከተማይቱ አስተዳደር ባለሥልጣናት እንደሚሉት ደግሞ የዘረኞቹ ቁጥር-ከመቶም ይበልጣል።በዚሕም ምክንያት ሌላ ቦታ ለመሔድ አማራጭ አጥቶ በከተማይቱ የሚኖረዉ የዉጪ ተወላጅ ሁሉ በሥጋትና ፍራት እንደተሸማቀቀ ነዉ።ከማግደልቡርግ ወጣ ብላ በምትገኝ አነስተኛ አነስተኛ ከተማ በአንድ የብራታ ብረታ ፋብሪካ የሚሰራዉ ሕንዳዊዉ ዲፓ ጉብታ እንደሚለዉ ግን እሱ በሚኖርበት ሁኔታዉ የተለየ ነዉ።

«እዚሕ እኛ ያለን ተሞክሮ ፍፁም የተለየ ነዉ።በጣም ሠላማዊ ሥፍራ፣ በጥሩ አካባቢ እንዳለን ነዉ-የሚሰማን።እና እስካሁን ድረስ እኛ መጥፎ ይገጥመናል የሚል ሥጋት አድሮብን አያዉቅም።»

ጉብታን መሰሉ የዉጪ ተወላጅ በርግጥ እድለኛ ነዉ።ባለሐብቶች ወረታቸዉን ምሥራቅ ጀርመን በስራ-ላይ እንዲያዉሉ የሚያግባባዉ ድርጅት ደንበኞች ጥቃት ፍራቻ አለመሸሻቸዉም ጥሩ እንጂ መጥፎ አይደለም።ግን የዚሁ ድርጅት ባልደረባ ቤቲና ክናበ እንደሚሉት አካባቢዉ ጥሩ ሥም ከሌለዉ ባለወረቱ መጀመሪያዉኑ ወደዚያ ሊሔድ አይችልም።

«አንዲት ሐገር ሁሉን ተቀባይ-ግልፅ፣ ሁሉን አቻችላ የምታኖር-ታጋሽ፤ እና አስተማማኝ ፀጥታ የሰፈነባት ከሆነች፣ ባለወረቶችን በቀላሉ ትስባለች።»

ምሥራቃዊ ጀርመን ይሕን እንዳታጣ ነዉ-ያሁኑ ሥጋት።