1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃዊው ተገን ጠያቂ አሟሟትና የጀርመን ፖሊስ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 10 2001

በዚህ በጀርመን የሢየራሌዎኑ ተወላጅ ተገን ጠያቂ የኡሪ ጃሎህ አሟሟት ሁኔታ ከአራት ዓመታት በኋላም ፍቺ አጥቶ እንደቀጠለ ነው። ወጣቱ አፍሪቃዊ ሕይወቱን ያጣው በምሥራቃዊቱ የጀርመን ክፍለ-ሐገር በዛክሰን አንሃልት በፖሊስ ተይዞ በታሰረበት የወህኒቤት ክፍል ውስጥ በተነሣ ቃጠሎ ነበር።

https://p.dw.com/p/GJjm
ሣሉ ዲያሎ
ሣሉ ዲያሎምስል picture-alliance/ dpa

የአካባቢው ፍርድቤት ባለፈው ሰኞ ባካሄደው ችሎት ለወጣቱ ሞት በተጠያቂነት ከተከሰሱት ሁለት ፖሊሶች በአንዱ ላይ የገንዘብ መቀጮ ሲጥል ሌላውን ደግሞ ነጻ አድርጎ አሰናብቷል። ታዲያ ብያኔው በብዙዎች ዘንድ ቁጣን ማስከተሉ፤ ሕጋዊነቱንም አጠያያቂ ማድረጉ አልቀረም። የሟቹን የቅርብ ወገኖችና ተቆርቁዋሪዎችን በተለይ እጅግ ያስቆጣው በምሥክርነት ፍርድቤት የቀረቡ የፖሊስ ባልደረቦች የሃሰት ቃል መስጠታቸውና እንዲያም ሲል ክሱ በውል እንዳይጣራ መሰናክል መፍጠራቸው ነው። ችሎቱን በሊቀ-መንበርነት የመሩት ዳኛ የተከሳሹን ፖሊስ ነጻ መውጣት ሲያስታውቁ ፍርድቤቱ በምሬት ነበር የተናወጸው።

“ይህን ብያኔ ጨርሶ አልቀበልም። ነገሩ እስኪውጣጣ መከታተሌን እቀጥላለሁ”

ይህን ያለው የሟቹ ወንድም ሣሉ ዲያሎ በቦታው ተገኝተው በፍርድቤቱ ብያኔ ብሶታቸውን ከገለጹት በርካታ ተመልካቾች አንዱ ነበር። የዛክሰን አንሃልት ክፍለ-ሐገር አስተዳዳሪ ቮልፍጋንግ ቦህመርም ከብያኔው ሶሥት ቀን በኋላ በጉዳዩ የተሰማቸውን ሃፍረት በምክርቤት ገልጸዋል።

“ሰፊና ብዙ ጊዜ የወሰደው ምርመራ ሁኔታውን በማያሻማ ሁኔታ ያጠራል ብለን አስበን ነበር። ግን ይህ እስካሁን እንዳልተቻለ ግልጽ ነው”

በእርግጥም ፍርድቤቱ ኡሪ ጃሎህ ለሞት የበቃበትን ሁኔታ ማጣራቱ አልተሳካለትም። የ 23 ዓመቱ የሢየራሌዎን ተወላጅ የፖለቲካ ተገን ጠያቂ ሕይወቱን ካጣበት ወህኒቤት የተወረወረው እ.ጎ.አ. ጥር 7 ቀን. 2005 ዓ.ም. ዴሣው ውስጥ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ነበር። ፖሊስ ለእሥራቱ የሰጠው ምክንያት ወጣቱ አፍሪቃዊ በስካር መንፈስ ሁለት ሴቶችን አውኳል የሚል ነበር። ከዚያም ጃሎህ ወህኒቤት እንደገባ በአንድ የፖሊስ ክፍል ውስጥ ዕጁና እግሩን ታስሮ ፍራሽ ላይ እንዲጋደም ይደረጋል። ከጥቂት ሰዓታት በኋላም ክፍሉ ውስጥ በተነሣ የእሣት ቃጠሎ ሳቢያ ታፍኖ ይሞታል።

ለመሆኑ ቃጠሎው እንዴት ሊነሣ ቻለ? በጉዳዩ ያስቻለው ፍርድቤት በምርመራው መጨረሻም ምላሽ ያላገኘለት ነገር ነው። ሆኖም የጊዜው የዴሣው ፖሊስ ጣቢያ ተረኛ ሃላፊ ቀደም ብሎ ዕርምጃ በመውሰድ አደጋውን ለማስወገድ በቻለ እንደነበር ተመልክቷል። ግን ይሄው ግለሰብ ሃላፊነቱን ላለመወጣቱ የገንዘብ መቀጮ ብቻ ነው የተበየነበት። ሌላው ቃጠሎው ከመነሣቱ ጥቂት ቀደም ሲል በወህኒቤቱ ክፍሎች የቁጥጥር ዙር ያደረገው ባልደረባው እንዲያውም ነጻ ተለቁዋል።

ብያኔው ምርመራው ከናካቴው ሕጋዊ መስመርን ተከትሎ መካሄዱን አጠራጣሪ ነው ያደረገው። አንዳንድ ምሥክሮች፤ ፖሊሶችን ጨምሮ ተከሳሾቹን የሚጫን ቃላቸውን መልሰው ሲያጥፉ ሌሎቹ ደግሞ እርስበርሱ የሚቃረን ቃል በመስጠት የፍርድቤቱን ምርመራ ቃላል አላደረጉትም። የዛክሰን አንሃልት ፖሊስ ሃይል የበላይ አዛዥ፤ የአገር አስተዳደር ሚኒስትሩ ሆልገር ሁፈልማን እንዳሉት እርግጥ በፖሊሶች ሙያ ላይ የባልደረብነት መንፈስ ለሥራው አስፈላጊና ጠቃሚም ጉዳይ ነው። ገደብ እስካለው ድረስ!

“ሁሌም ችግር የሚፈጠረው የባልደረብነትና የጓደኝነት ወሰን የሚጣስበትን ደረጃ በተናጠል ሁኔታዎች የመለየቱ ጉዳይ ሲመጣ ነው። የባልደረብነቱ መንፈስ ወደ አድመኝነት ከተሻገረ በሕግ ረገድ ጥርጣሬን ነው የሚያስከትለው”

ለማንኛውም ፍርድቤቱ አንዳንድ የሃሰት ቃል በመስጠት የሚጠረጠሩ የፖሊስ ባልደረቦችን በቃለ መሃላ ለመመርመር ያቅዳል። ይሁንና ለኡሪ ጃሎህ ሞት ተጠያቂው ማነው? በምሥክሮች ቃል ሽፍንፍንነት የተነሣ እንደተድበሰበሰ መቀጠሉ ነው። በዚህ በጀርመን ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ሲነጻጸር ፖሊሶች የሚከሰሱትም ሆነ ከፍርድቤት የሚቀርቡት ከስንት አንዴ ቢሆን ነው። የዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአምነስቲይ ኢንተርናሺናል የጀርመን ዘርፍ ባልደረባ ካታሪና ሽፒስ እንደሚሉት ምክንያቱም ብዙ ግልጽ አይደለም።

“ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለ የምናውቀው ነገር የለም። ለምን አዘውትሮ ከመጠን ያለፈ የፖሊስ ሃይል ተግባር ላይ እንደሚውልም አስተማማኝ መረጃ የለንም። ከአውሮፓ ሸንጎ ኮሚቴና ከኛም በኩል ደጋግሞ ጥያቄ ይቅረብ እንጂ በፖሊስ ዓመጽ ላይ ሰንጥረዥ እንዲቀርብ አልተደረገም። እኔ እንደሚመስለኝ ሃይሉ የሚመነጨው ችግሩ ከአቅም በላይ በመሆኑ ነው። ከዚህ በተጨመሪ ፖሊሶች የውጭ ሰዎችን በተመለከተ የሥልጠና ጉድለት አለባቸው”

በሌላ በኩል የአመራር ሰዎችን የሚያሰለጥኑት የጀርመን ፖሊስ ከፍተኛ የትምሕርት ተቁዋም ፕሬዚደንት ክላውስ ናይድሃርድት ፖሊስ ችግሩን ተረድቶ በባሕላት መካከል ላለው ግንኙነት ክብደት እየሰጠ ነው ባይ ናቸው። በወቅቱ ይሄው የሥልጠናው አንድ አካል መሆኑንም ይናገራሉ። የሆነው ሆኖ ብዙ የስርዓት ለውጥ ማስፈለጉ የሚቀር አይመስልም። የኡሪ ጃሎህን ሞት በተመለከተ አሁን ጉዳዩ ወደ ከፍተኛ ችሎት፤ ወደ ፌደራሉ የፍርድ ሸንጎ ይሸጋገራል። ግን የከፍተኛው ሸንጎ ተግባር ክሱን በአዲስ መልክ መመርመር ሣይሆን የእስካሁኑን ሂደት ሕጋዊነት ብቻ ማጣራት ነው የሚሆነው። የሟቹ ቤተሰቦች በበኩላቸው ነገሩ ሙሉ በሙሉ እንዲጣራ ይጠይቃሉ። የሚቀጥለው የተቃውሞ ሰልፍም ከአሁኑ ለጃሎህ አራተኛ የሙት ዓመት ዕለት ለፊታችን ጥር 7 ቀን. 2009 ታቅዷል።