1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤና ንግድ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 3 2004

አፍሪቃዉያን እርስ በርስ ካላቸዉ የንግድ ግንኙነት ይልቅ ከሌሎች ጋር ያላቸዉ ይበልጣል።የአፍሪቃዉያንን ሁለንተናዊ መቀራረብ ለመፍጠር ደግሞ አምባሳደር ኦሉሴጉን ኦኪንሳንያ እንደሚሉት ነፃ የንግድ ቀጠናን መመሠርት በጣም አስፈላጊ ነዉ

https://p.dw.com/p/15UwD
Das neu erbaute Hauptquartier der der Afrikanischen Union (AU) in Addis Abeba, aufgenommen vor der offiziellen Eröffnung am Samstag (28.01.2012). Der 100 Meter hohe Turm mit angrenzendem Konferenzzentrum ist derzeit das höchste Gebäude der äthiopischen Hauptstadt. Hier wird am Sonntag und Montag das 18. Gipfeltreffen der Staatengemeinschaft abgehalten. Nach dreijähriger Bauzeit wurde das 200 Millionen Dollar (152 Millionen Euro) teure Projekt erst kürzlich fertiggestellt. Die Kosten für den vom chinesischen Tongji Design Institut entworfene Bau übernahm komplett die Regierung in Peking. Foto: Carola Frentzen dpa (zu dpa 0231 am 28.01.2012) +++(c) dpa - Bildfunk+++
አዲሱ ሕንፃምስል picture-alliance/dpa



አስራ-ዘጠነኛዉ የአፍሪቃ ሕብረት የአምባሳደሮች መደበኛ ሥብሰባ ትናንት አዲስ አበባ ዉስጥ ተጀመረ።በሕብረቱ የሥብሰባ ሥርዓት መሠረት ከአምባሳደሮቹ ሥብሰባ ቀጥሎ የሚንስትሮች፥ ከሚንስትሮቹ ቀጥሎ ደግሞ የመሪዎቹ ጉባኤ በሳምንቱ ማብቂያ ይሰየማል።የሕብረቱ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት የዘንድሮዉ ጉባኤ አብይ ትኩረት የአፍሪቃን የንግድ ትሥሥር ማጠናከር ነዉ።የሕብረቱን ኮሚሽን ፕሬዝዳት የመምረጥ ልዩነት፥ ከማሊ እስከ ሶማሊያ ያለዉ ፖለቲካዊ ቀዉስና የፀጥታ ችግር ያጠላበት ጉባኤ በዋና ርዕሡ ላይ ማተኮር መቻሉ ግን ብዙ እያነጋገረ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።


አስራ-ዘጠነኛዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ የአፍሪቃን የርስ-በርስ ንግድ በማጠናከሩ ላይ መክሮ እንዲወስን የወሰነዉ ቀዳሚዉ ጉባኤ ነበር።ባለፈዉ ጥር አዲስ አበባ ተደርጎ የነበረዉ አስራ-ስምተኛዉ ጉባኤ።የሕብረቱ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ኤራስተስ ምዌንቻ ትናንት የአምባሳደሮቹን ስብሰባ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግርም የሠሞኑ ጉባኤ፥ ያለፈዉ ጉባኤ በወሰነለት ርዕሥ እንደሚፀና አስታዉቀዋል ።ንግድ።

የዓለም አቀፉ የስልት ጥናት ተቋም (ISS) የአዲስ አበባ ቢሮ ሐላፊ አምባሳደር ኦሉሴጉን ኦኪንሳንያ እንደሚሉት ደግሞ ነፃ የንግድ ቀጠና የመሠመሥረቱን አስፈላጊነት ያለፈዉ ጉባኤ ተወያይቶ፥ መግለጫም አዉጥቶ ነበር።

«ይሕ ጉዳይ በአስራ-ሥምንተኛዉ ጉባኤ በጥልቀት ዉይይት ተደርጎበት ነበር።የዚያ ሥብሰባ ጭብጥ የአፍሪቃን የርሥ በርሥ ንግድ ማጠናከር የሚል የነበር።በዚያ ሥብሰባ በመሪዎች ጉባኤ ደረጃም ብዙ ዉይይቶች ነበሩ።በዉይይቱ ማብቂያ የጋራ መግለጫም ወጥቷል።መግለጫዉ ከያዛቸዉ ነጥቦች አንዱ በ2017 አሐጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መመሥረት ነዉ።»

ያሁኑ ጉባኤ ዋና ትኩረት እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2017 የአፍሪቃ ነፃ የንግድ ቀጠና የሚመሠረትበትን ሥልት መቀየስ ነዉ።ሌላኛዉ የISS አጥኚ ዶክተር ጄደ ማርትየንስ ኦኬኬ እንደሚሉት ሥልቱ ካለፈዉ ጉባኤ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሞ መስተካከል ያለበትን መወሰንን ያካትታል ተብሎ ነዉ-የሚጠበቀዉ።

«የጉባኤዉ ዉይይት የአፍሪቃን የርስ በርስ ንግድ ማጠናከር ሁለተኛ ዙር ሊባል ይችላል።ሥለዚሕ አሁን አስፈላጊ ነዉ ብዬ የማምነዉ ባለፈዉ ጥር የፀደቀዉን የድርጊት መርሐ-ግብር ገምግሞ ጥንካሬዎቹን ከክፍተቶቹ መለየትና ክፍተቶቹን ለመድፈን በሚቀጥሉት ወራት መደረግ ያለበትን መወሰን ነዉ።»

አፍሪቃዉያን እርስ በርስ ካላቸዉ የንግድ ግንኙነት ይልቅ ከሌሎች አሐጉራት ጋር ያላቸዉ ይበልጣል።ይሕ ደግሞ አፍሪቃን ለማቀራረብ ብዙዎች እንደሚሉት አይጠቅምም።የአፍሪቃዉያንን ሁለንተናዊ መቀራረብ ለመፍጠር ደግሞ አምባሳደር ኦሉሴጉን ኦኪንሳንያ እንደሚሉት ነፃ የንግድ ቀጠናን መመሠርት በጣም አስፈላጊ ነዉ።

የጥሩ ጉባኤ በወሰነዉ መሠረት፥ አምባሳደር ኦኪንሳንያ በጣም አስፈላጊ ያሉትን፥ የአፍሪቃ ነፃ የንግድ ቀጠናን ለመመሥረት እንደ ጥንስስ የሚያገልግሉት አካባቢያዊ የንግድ ማሕበራት ናቸዉ። የሰሜን አፍሪቃዉ የመግሬብ የንግድ ማሕበር፥ የምሥራቅ አፍሪቃዉ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ፥ የደቡባዊ አፍሪቃዉ የልማት ማሕበረሰብ እና የምዕራብ አፍሪቃዉ የምጣኔ ሐብት ማሕበር።

«የአፍሪቃን የርስ በርስ ንግድን ለማጠናከር የየካባቢዉ የምጣኔ ሐብት ማሕበራት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ አለ።ሐገራት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ አለ።ይሕ ጉዳይ አፍሪቃ ባሁኑ ወቅት የሚያስፈልጋትን መቀራረብ ለመፍጠር በጣም አስፈላጊ ነዉ።»

አስራ-ስምንተኛዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ባለፈዉ ጥር ከተደረገ ወዲሕ የሶማሊያ፥ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ግጭት-ዉዝግቦች ሲያንስ በነበሩበት፥ሲበዛ ብሰዉ ቀጥለዋል።የሱዳኖች ዉዝግብ ወደ ጦርነት ንሮ-ነበር።የጊኒ ቢሳዉ መፈንቅለ መንግሥት፥ የማሊ መፈንቅለ መንግሥትና የርስ በርስ ጦርነት በአፍሪቃ ችግሮች ላይ አዳዲስ ተጨምረዋል።

የሕብረቱን ኮሚሽን የወደፊት ፕሬዝዳት ለምረጠም በሕብረቱ ጠንካራ አባላት መካከል የተፈጠረዉ ልዩነት አግባቢ መፍትሔ አላገኘም።በፖለቲካና በፀጥታዉ ምሥቅልቅል፥ በምርጫ ልዩነቱ መሐል የአፍሪቃ መሪዎች አፍሪቃን ለማቀራረብ ጠቃሚ የተባለዉን የንግድ ቀጠና ለመመሥረት በረጋ መንፈስ መክረዉ፥ መወሰን-ይችላሉ ወይ ነዉ ጥያቄዉ።

ጠየኩ-አምባሳደሩን።መልሳቸዉ ከተንታኝ ይልቅ ዲፕሎማሲያዊ ነበር።

«አስፈላጊዉ ነገር ይሕ ጉዳይ (የንግድ ቀጠናዉ) በርዕሥነት ተይዟል።ዋና ጭብጥ ነዉ።አንተ ያነሳኸዉ ጥያቄ ሌሎች ጉዳዮች ናችዉ።ይሕ ማለት አንዱ ሌላዉን በልጦ ቅድሚያ ያገኛል ማለት ነዉ።አዎ ልክ ነሕ! የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርን መምረጥ በጣም አስፈላጊ ርዕሥ ነዉ።ካንተጋር እስማማለሁ ሌሎች በርካታ የሠላምና የፀጥታ ጉዳዮች አሉ፥ብዙ ጉዳዮች አሉ።እነዚሕ ጉዳዮች እንዴት ይነሳሉ ይሕ ሌላ ጥያቄ ነዉ።»

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ

African leaders pose for a group photograph with U.N. Secretary-General Ban Ki-moon during the 18th African Union (AU) summit in Ethiopia's capital Addis Ababa January 29, 2012. REUTERS/Noor Khamis (ETHIOPIA - Tags: POLITICS)
የ18ተኛዉ ጉባኤተኞችምስል Reuters
epa03084113 A handout image made available by the South African Government Communication and Information System (GCIS) shows a general view of the the new African Union building where the present 26th meeting of the NEPAD Heads of State and Government Orientation Committee (HSGOC) is being held, Addis Ababa, Ethiopia, 29 January 2012. EPA/Jacoline Prinsloo / GCIS / HANDOUT HANDOUT EDITORIAL USE ONLY/NO SALES
ያለፈዉ ጉባኤምስል picture-alliance/dpa