1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት፤ ዕድገቱና እንቅፋቱ

ሰኞ፣ ሰኔ 9 2006

ሚንስትር ደ ኤታ ዚልበርሆርን እንደሚሉት ደግሞ የአፍሪቃ ዕድገት እንዲቀጥል ዕድገቱ የአፍሪቃዉያን በሙሉ መሆን አለበት።የሕዝቡን የምግብ፤የጤና እና የትምሕርት ፍላጎት ማሟላት-አንድ።መልካም አስተዳድር እና የመሠረተ-ልማት አዉታርን ማስፋፋት-ሰወስት።

https://p.dw.com/p/1CGlS
ምስል imago/Xinhua

የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት እያደገ ነዉ።በቅርቡ ይፋ የሆነዉ «African Economic Outlook» የተሰኘዉ የጥናት ዘገባ እንዳመለከተዉ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ዕድገት በመጪዎቹ ዓመታትም ማደጉን ይቀጥላል። የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ድርጅት (OECD)፤የአፍሪቃ ልማት ባንክ (AfDB) እና የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐ-ግብር (UNDP) በጋራ ያስጠኑት ዘገባ እንደሚያመለክተዉ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት በያዝነዉ የጎርጎሮሳዉያኑ ዓመት 2014 4.8 በመቶ፤ በሚቀጥለዉ ዓመት ደግሞ በ5.7 በመቶ ያድጋል።ይሁንና የመሠረተ-ልማት አዉታሮች ችግር፤ የመልካም አስተዳድር እጦትና ሙስና ለዕድገቱ ጋሬጣ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ። ዛቢነ ኪንካርትስ የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የዕድገት ተስፋዉ ተጨባጭ ምልክት አሳይቷል። ምልክቱ ይበልጥ ይደምቃል-የሚል ሌላ ተስፋም አጭሯል።«ተስፋ-የለሺቱ አሁጉር» ይላሉ-በአፍሪቃ ልማት ባንክ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዉ አንቶንይ ሙሶንዳ ሲምፓሳ «አሁን የተስፋ ምድር ሆናለች።»

«ሥለ አፍሪቃ ዕድገት ይተረክ የነበረዉ አሁን አፍሪቃ እያኮበኮበች ወደ መሆኗ ተቀይሯል።ከጥቂት ዓመታት በፊት «ተስፋቢስ» የነበረችዉ አፍሪቃ አሁን ወደ ተስፋ ክፍለ-ዓለም ተለዉጣለች።ይሕ እዉነት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታትም መስፋፋትና መጠናከሩ ይቀጥላል።»

Infografik Afrikas wichtigste Ölproduzenten 2012

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአፍሪቃ አጠቃላይ የሐገር ዉስጥ ምርት በ3,9 በመቶ አድጓል።ዕድገቱ ጎልቶ የሚታየዉ ደግሞ ከሠሐራ-በስተደቡብ በሚገኙ ሐገራት ነዉ።የዕድገቱ ዋና ሞተር-ናጄሪያ።ግን የቦኩ ሐራም ጥቃት፤ የመሪዎችዋ ዝርክርክነት፤ የባለሥልጣናቷ መረን የለሽ ሙሰኝነት-ሞተሯን በሚዘዉረዉ ነዳጅ ዘይቷ አንድዶት- ባፍጢሟ እንዳይደፋት ማስጋቱ አልቀረም።

ኢትዮጵያ፤ሩዋንዳ፤ታንዛኒያ፤ዩጋንዳ፤ ኮትዲቯር እና ሴራሊዮንም ቀና ዕድገት ያሥመዘገቡ ሐገራት ናቸዉ። የነዚሕም ይሁን የሌሎቹ አፍሪቃዉያን የዕድገት ምንጭ የጥሬ አላባ ሽያጭ፤ ከዚሕ ካለፈም ንግድ ነዉ።የተሻሻሉ የግብርና ዉጤቶችን እና የተቀላጠፉ አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረቡ ረገድ ግን፤ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት (OECD) እንደሚለዉ አፍሪቃዉያን ማቅረብ የሚችሉትን ያክል አያቀርቡም።

እስካሁን ያለዉ የአፍሪቃ ዕድገትም ባብዛኛዉ ከቻይና ጋር የተቆራኘ ነዉ።ባለፈዉ የጎርጎሮሳዉያን ዓመት 2013 ሕዝባዊት ቻይና ከአፍሪቃ ጋር ያደረገችዉ የንግድ ልዉዉጥ 200 ቢሊዮን ዶላር ነዉ።ቤጂንግ እስከ 2020 ድረስ የንግድ ልዉዉጡን በእጥፍ ለማሳደግ አቅዳለች።

የአፍሪቃ ዕድገት አማላይነትን ጀርመኖችም ከቻይኖች እኩል ያዉቁታል።እንዲያዉም የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚንስትር ደኤታ ቶማስ ዚልበርሆርን አፍሪቃን «የመጪዉ ዘመን ክፍለ-ዓለም» ብለዋታል።

«አፍሪቃ በምጣኔ ሐብቱ፤በማሕበራዊ ኑሮ እና በፖለቲካዉ መስክ እየተለወጠች ነዉ።ምስሪያ ቤታችን አፍሪቃ የመጪዉ ዘመን ክፍለ-ዓለም ናት ብሎ ያምናል።በሚቀጥለዉ አስርት አፍሪቃ ለልማት ከፍተኛ ዕድል ትሰጣለች።የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ከአዉሮጳ ብቻ ሳይሆን ከደቡብ አሜሪካና ከመካከለኛዉ ምሥራቅም ይበልጥ እያደገ ነዉ።»

ይበሉ እንጂ ጀርመን አፍሪቃ ዉስጥ ያላት ተሳትፎ ኢምንት ነዉ።በ2013 የጀርመን ኩባንዮች የ1.1 ትሪሊዮን ዩሮ ሸቀጥ ወደ ዉጪ ልከዋል።አፍሪቃ የገባዉ ግን ሁለት ከመቶዉ ብቻ ነዉ።ከዚችዉ አቅም ከግማሽ የሚበልጠዉ ደብብ አፍሪቃ ነዉ-ያረፈዉ። ጀርመን አፍሪቃ ዉስጥ ያላት የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ዘጠኝ ቢሊዮን ዩሮ ነዉ።ከዚሕ ዉስጥ አምስት ቢሊዮኑ ሥራ ላይ የዋለዉ ደቡብ አፍሪቃ፤ ሰወስት ቢሊዮኑ ሰሜን አፍሪቃ ነዉ።ለተቀሩት የቀረዉ አንድ ቢሊዩን ብቻ ነዉ።

የጀርምንም ሆነ የሌሎቹ የምዕራባዉያን ሐገራት የአፍሪቃ ተሳትፎ ባለሙያዎች እንደሚሉት አሁን ባለበት አይቀጥልም።ያድጋል። ተሳትፎዉ-በተለይም የአፍሪቃ ዕድገት እዲቀጥል የመሠረተ ልማት አዉታር መስፋፋት፤ ቀልጣፋ የሥልክና የኢንተርኔት አገልግሎት፤ ቀልጣፋ ቢሮክራሲና የገንዘብ ልዉዉጥ መኖር አለበት።ከሁሉም በላይ ሙስና መጥፋት ይገባዋል።

Sanusi Lamido Sanusi Gouverneur Zentralbank Nigeria
ምስል Aminu Abubakar/AFP/Getty Images

በአንዳድ የአፍሪቃ ሐገራት የተጭበረበረ መድሐኒት ሳይቀር የአጭበርባሪዎች መክበሪያ ሆኗል።የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የትብብር ማሕረሰብ (GIZ) አማካሪና ቤይሪንገር ኤንግል ሐይም የተሰኘዉ መድሐኒት አምራች ኩባንያ ሥራ-እስኪያጅ ሚካኤል ራቦዉ «በሕይወት መቀለድ» ይሉታል።

«የመድሐኒት ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ለቤሪግ ኤንግልሐይም---የሕይወት ጉዳይ ነዉ።የሰዉም የእንስሳትም ሕይወት።ባጭር ቃላት፤ በመድሐኒት ጥራት ላይ ድርድር የለም።ሁለተኛና ሰወስተኛ የሚባል የመድሐኒት የጥራት ደረጃ ሊኖር አይገባም።»

ሚንስትር ደ ኤታ ዚልበርሆርን እንደሚሉት ደግሞ የአፍሪቃ ዕድገት እንዲቀጥል ዕድገቱ የአፍሪቃዉያን በሙሉ መሆን አለበት።የሕዝቡን የምግብ፤የጤና እና የትምሕርት ፍላጎት ማሟላት-አንድ።መልካም አስተዳድር እና የመሠረተ-ልማት አዉታርን ማስፋፋት-ሰወስት።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ