1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ስደተኞችና የአውሮፓ የልማት እርዳታ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 17 2008

የአውሮፓ ህብረት ፣ አፍሪቃውያን ስደተኞች ወደ አውሮፓ እንዳይመጡ ለመግታት ለአፍሪቃ ሃገራት የሚሰጠውን እርዳታ ለማጠናከር እንደሚሻ አስታውቋል ።የህብረቱ የልማት ጉዳዮች ክፍል ይህን ቢልም እስካሁን የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ አይደሉም ሲሉ የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተችተዋል ።

https://p.dw.com/p/1GvwP
Grenze Dschibuti Äthiopien Flüchtlinge IOM
ምስል IOM/Alemayehu Seifeselassie

[No title]

ምዩለር ህብረቱ ጉዳዩን አጥብቆ ይዞት ቢሆን ኖሮ ችግሩ አሁን ባልተባባሠ ነበር ብለዋል ።
የአውሮፓ ህብረት፣ ስደተኞች ወደ ክፍለ ዓለሙ እንዳይመጡ ለመግታት ሰዎችን ለስደት የሚያበቁ መሠረታዊ ምክንያቶችን በየሃገራቸው መዋጋት የሚል መፈክር ማስተጋባት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል ።ይህን ለማሳካትም በተለይ ዜጎቻቸው በብዛት በሚሰደዱባቸው ሃገራት ህብረቱ የሚሰጠውን የልማት እርዳታ በማሳደግ ፣ችግሩን በየሃገራቸው የመከላከል ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠው ቃል ተገብቶ ነበር ። ይሁንና በዚህ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት በቂ እንዳይደሉ ነው የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር ለዶቼቬለ የተናገሩት ።
«ይህን ጉዳይ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ትኩረት ሰጥተነው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ችግሮቻችን ጥቂት በሆኑ ነበር ።አሁን በእውነት የአሠራር ለውጥ እናደርጋለን ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ ። እንደመረብ ስለተሳሰረ የልማት ሥራ ፣ ስለ ውጭ እና የፀጥታ መርሆች ከመናገር ይልቅ እነዚህን ተግባራዊ ማድረግም ይገባል ።ያ ካልሆነ ችግሩ ለዓመታት ለብዙ አሥርት ዓመታት የአውሮፓ ችግር ሆኖ መዝለቁ አይቀርም ።»
ምዩለር እንዳብራሩት በአሁኑ ጊዜ በብዛት ወደ ጀርመን ከገቡት ስደተኞች አብዛኛዎቹ የባልካን ሃገራት ዜጎች ናቸው ።ከነርሱ የሚቀጥለውን ደረጃ የሚይዙት ደግሞ ሶሪያውያን ናቸው ። ከአፍሪቃ ሃገራት የተሰደዱት በመቶና ሲሰላ ከአጠቃላዩ ስደተኛ ከ10 እስከ 12 በመቶ የሚሆኑ ናቸው ።ሆኖም በምዩለር አባባል ጀርመን ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ከዚህ የተለየ ነው ። ከአፍሪቃ የመጡት 50 በመቶ ይሆናሉ የተባለው ስህተት ነው ሲሉም አስረድተዋል ።በሌላ በኩል በጦርነት የደቀቁ ሃገራት ቶሎ እንዲያንሰራሩ የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል ። ለዚህም በምሳሌነት ያነሱት የተረጋጋ መንግሥት ማቋቋም በተሳናት በሰሜን አፍሪቃዊቷ ሃገር ሊቢያ የሆነውን ነው ።
«ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊቢያ በቦምብ እንድተደበደብ አድርጎ በልማት እርዳታው ግን አልገፋበትም የጋዳፊን ሥርዓት በጦር ኃይል ከማስወገድ ባለፍ መሠራት የነበረባቸውን የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን አላከናወነም ።በጋዳፊ ዘመን የተከማቹ የጦር መሣሪያዎች እንደተበተኑ ነው ።ሚሊሽያዎችና ቱዋሬጎች መሣሪያዎቹን ወስደው ማሊ እንዳትረጋጋ አድርገዋል ።አሁን ይህ 4 ዓመት ሆኖታል ።በዚያ ትላልቅ ተቋማት ስላልተገነቡ አሁን ትልቅ ችግር እየተጋፈጥን ነው ።የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሊቢያ ተቋማቷን መልሳ እንድትገነባ እርዳታ ያደርጋል ።የሃገሪቱን የባህር ጠረፍ አካባቢ ቁጥጥር ማጠናከር አለብን ።»
በአሁኑ ጊዜ ሊቢያ ውስጥ ወደ አውሮፓ ለመምጣት የሚጠባበቁ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ይገኛሉ ። እነዚህ ስደተኞች ግልብጥ ብለው ወደ አውሮፓ መንገድ ይጀምራሉ የሚል ስጋት አለ ።በሌላ በኩል በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ በጉዞ ላይ የሚሞቱ ስደተኖች ቁጥር እየጨመረ በሄደበት በአሁኑ ወቅት ለአፍሪቃ የ10 ቢሊዮን ዩሮ የእርዳታ ገንዘብ ለመስጠት ቃል ተገብቶ ነበር ።ሆኖም ያ ቃል በተግባር አልታየም ።ይህን አሳፋሪ ያሉት ምዩለር ችግሩን ለመፍታት በህብረቱ አባል ሃገራት መካከል ህብረት መጥፋቱ አሳዛኝ ነው ብለዋል ። ከቅርብ ወራት ወዲህ ህብረቱ አሁን የሚሰራባቸውን መርሃ ግብሮች 5 ቢሊዮን ዩሮ በማውጣት እንዲጠናከሩ አድርጓል ።በሁለት ሳምንታት ውስጥ የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች ጋር በማልታ ዋና ከተማ ቫሌታ ጉባኤ ያካሂዳል ።በዚህ ጉባኤ ላይ ምዩለር ከአፍሪቃ መንግሥታ ብዙ ይጠበቃል ይላሉ ።
«ቫሌታ በሚካሄደው የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ጉባኤ በአፍሪቃ ሃገራት ለመስጠት ከታሰበው ሥልጠና ጋር አብሮ የሚሄድ የአፍሪቃውያን ተነሳሽነት ሊኖር ይገባል ።በዚህ ረገድ ጀርመን ከፍተኛ ድጋፍ ታደርጋለች ። በሌላ በኩል በክፍለ ዓለሙ የሚገኙ ህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችን የመዋጋት ሃላፊነት የአፍሪቃ መንግሥታት መሆኑን ማስገንዘብ ይኖርብናል ።»
በምዩለር አባባል ከአፍሪቃ በተለይም ከሰሜን አፍሪቃ ሃገራት ጋር በልማት ተራድኦ መተባበር ብቻ ሳይሆን የኤኮኖሚ ትብብርም መጠናከሩ መኖሩ ለጋራ ተጠቃሚነት አስፈላጊ ነው ።

EU-Afrika Gipfel in Lissabon, Portugal Flaggen der europäischen und afrikanischen Nationen, die bei dem Gipfel vertreten sind Symbolbild
ምስል AP
EU Afrika Gipfel Merkel 02.04.2014 Brüssel
ምስል Reuters

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ