1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ቀንድ ስደተኞችና ጀርመን

ዓርብ፣ ግንቦት 12 2008

ጀርመን ከሱዳንና ከኤርትራ መንግስታት ጋር በልማት ተራድኦዉ የማትተባበረዉ መንግሥታቱ ሰብአዊ መብት ይረግጣሉ በሚል ምክንያት ነበር።ስደተኞችን እንዲያግዱ መተባበሩ ግን ሠብአዊ መብትን ማስከበር-ይሆን?-የግራዎቹ ፖለቲከኞች ጥያቄ።

https://p.dw.com/p/1Is2m
Schweden Ankunft Flüchtlinge aus Eritrea
ምስል picture-alliance/dpa/R. Nyholm

[No title]

የተለያዩ ሐገራት ስደተኞች ወደ አዉሮጳ መግባታቸዉን ለመግታት የአዉሮጳ ሕብረት ከወሰደና ሊወስድ ካቀዳቸዉ እርምጃዎች አንዱ ከአፍሪቃ ቀንድ መንግስታት ጋር ተባብሮ መስራት ነዉ።የሕብረቱን የለያዩ ዕቅዶች እና እርምጃዎች በግንባር ቀደምትነት ከሚያስፈፅሙ አባል ሐገራት አንዷ ጀርመን ናት።ይሁንና የስደተኞችን ፍልሰት ለመግታት ሕብረቱም ሆነ ጀርመን የሱዳንና የኤርትራን ከመሳሰሉ ጨቋኝ መንግሥታት ጋር ለመተባበር መወሰናቸዉ ብዙ ጥያቄዎችን አጭሯል።ጥያቄዉን ካነሱት መሐል የጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲ ግራዎቹ፤ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያና መልስ እንዲሰጥበት ጠይቋል።ሉድገር ሻዶምስኪ በጀርመን ምክር ቤት የግራዎቹን እንደራሴ ኒኤማ ሞቫሳትን አነጋግራቸዋል። ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የአፍሪቃ ቀንድን ያክል ሕዝብ የተሰደደ ወይም የተፈናቀለ፤ ስደተኛና ተፈናቃይ የሚያስተናግድም አካባቢ የለም።ስደተኛ-8.9 ሚሊዮን ።ተፈናቃይ-6.5 ሚሊዮን።የአዉሮጳ ሕብረት ሰዎችን ከሚያሰድደዉ መሠረታዊ ምክንያት ከመፍታት ይልቅ ስደተኛዉ አዉሮጳ እንዳይገባ ለመግታት ማቀዱ ብዙ አነጋግሮ፤ አስወቅሶትም ሊሆን ይችላል።የአፍሪቃ ቀንድን ኢላማ ማድረጉ ግን በርግጥ ያስደነቀዉ የለም።

ለዕቅዱ ስኬት ለመላዉ አፍሪቃ ከመደበዉ 1,8 ቢሊዮን ዩሮ ሰባት መቶ ሚሊዮኑ ለአፍሪቃ ቀንድ ነዉ-የተመደበዉ።አብዛኛዉ ገንዘብ ሥራ ለመፍጠር ወይም ሰዉ አሸጋጋሪዎችን ለመቆጣጠር በሚል ምክንያት ስደተኞች ለሚነሱባቸዉ ሐገራት መንግሥታት ተስጥቷል።ይሰጣልም።ይሕ ነዉ እንደ ብዙዎቹ ተቺዎች ሁሉ የግራዎቹን ፓርቲ ያሰደነቀ፤ያስደመመ፤ለጥያቄ ያነሳሳዉም።

Zum Thema - Pflegenotstand und zur Anwerbung von Pflegekräften aus Entwicklungsländern
ምስል Imago/Metodi Popow

«ከአካባቢዉ ሰዎች እንደምንሰማዉ በስደተኖች ላይ የሚደረገዉ ቁጥጥር እየተጠናከረ፤ እድማሱም እየሰፋ ነዉ።መያዶችም ይሕን ማረጋገጣቸዉ ጉዳዩን በጥልቀት እንድናያዉ እና እኔም አዉነታዉ ምን እንደሆነ ለማወቅ ሁለቱን ጥያቄዎች እንዳነሳ አድርጓኛል።»

ይላሉ በጀርመን ሕግ መምሪያ ምክር ቤት (ቡንደስ ታግ) የግራዎቹ እንደራሴ ኒኤማ ሞቫሳት።ለጀርመን ፌደራላዊ መንግሥት ያቀረቧቸዉን ጥያቄዎች «ትንሽ» ይሏቸዋል።«ባሁኑ ወቅት እዚያ ያለዉ ተጨባጭ ሁኔታ ምን እንደሆነ እና ፌደራላዊዉ መንግሥት ከነዚያ አምባገነን ሥርዓቶች ጋር ተባብሮ ለመስረት የወሰነበትን ምክንያትን ለመረዳት።»

እንደራሴዉ እንደሚሉት የአዉሮጳ ሕብረትም ሆነ የጀርመን መንግሥት መርሕ ከሰብአዊ መብት ጥበቃ ጋር የሚጋጭ፤ እርስ በርሱም የሚጣረስ ነዉ።

«ይሕ ከሰብአዊ መብት ጥበቃ ጋር የሚጣጣም አይደለም።ከልማት ተራድኦ ትብብር ጋርም አይሰናኝም።ምክንያቱም ከሱዳንም ይሁን ከኤርትራ ጋር የልማት ተራድኦ ትብብር የለንምና። አሁን ስደተኞችን ለመቆጣጠር ግን አብሮ እየተሰራ ነዉ።እርግጥ ነዉ ይሕ የአዉሮጳ ሕብረት ፕሮጀክት በመሆኑ ከልማት ትብብር ጋር ግንኙነት የለዉም የሚል ግልብ ምክንያት መቅረቡ አልቀረም።ዞሮ ዞሮ ግን ከጨቋኝ ሥርዓቶች ጋር እየተባበርን ነዉ።»

Eritrea Mädchen im Flüchtlingslager in der Region Tigrai Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri

ጀርመን ከሱዳንና ከኤርትራ መንግስታት ጋር በልማት ተራድኦዉ የማትተባበረዉ መንግሥታቱ ሰብአዊ መብት ይረግጣሉ በሚል ምክንያት ነበር።ስደተኞችን እንዲያግዱ መተባበሩ ግን ሠብአዊ መብትን ማስከበር-ይሆን?-የግራዎቹ ፖለቲከኞች ጥያቄ።

«ለጥያቄዉ የተሰጠዉ መልስ እዉነት ይመስላል።ትንሽ ከመሽሞንሞኑ በስተቀር በአካባቢዉ ከፍተኛ የሠብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን ፌደራላዊ መንግሥት ይቀበለዋል።ምንም አልተከራከረም።ቢሆንም ይሕን ፕሮጄክት እንቀጥላለን የሚል አይነት ነዉ።»

ከመንግሥት ያገኙት ሁለተኛዉን መልስ ግን እንደራሴዉ «ልዩ» ይሉታል፤ እና «አስገራሚም»

«ሌላዉ አስገራሚዉ፤ የተመደበዉ 1,8 ቢሊዮን፤ ለአፍሪቃ ቀንድ 700 ዩሮ አዲስ ገንዘብ አይደለም።ለልማት ተራድኦ የተመደበዉ ነዉ። ይሕ ገንዘብ ድሕነትና ረሐብን ከመዋጋት፤ ትምሕርትን ከማስፋፋት ይልቅ የነዚያን ሥርዓቶች የፀጥታ ሐይል ለማጠናከር ይዉላል ማለት ነዉ።»

ሞቫሴት እንደሚሉት የኤርትራ ባለሥልጣናት ዜጎቻቸዉን እንደሚጨቁኑ፤ እንደሚያንገላቱ እና እንደሚበድሉ የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚንስትር ሳይቀሩ በቅርቡ አረጋግጠዋል።ግን በተቃራኒዉ ጀርመን ከዚሁ የኤርትራ መንግሥት ጋር ተባብሮ ለመስራት መወሰኗ ለእንደራሴ ሞቫሴት «ግራ-አጋቢ» ነዉ።

Jungle Calais Frankreich Flüchtlinge Camp Slum
ምስል Getty Images/AFP/P.Huguena

አፍሪቃ ቀንድ ሰዉ የማይሰደድበት፤ሰዉ የማይረገጥበት ሐገር የለም።ኢትዮጵያ አንዷ ናት።የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃዋሚዎች፤ በጋዜጠኞችና በመብት ተሟጋቾች ላይ የሚፈፅመዉ ጭቆና፤ እስራትና እንግልትን፤ የጀርመኑ እንደራሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ «የተባባሰ፤አሳሳቢ» ይሉታል።ጀርመንን ጨምሮ ምራባዉያን መንግሥታት የኢትዮጵያ መንግሥትን እርምጃን በቸልታ ማለፋቸዉን እንደራሴዉ ይተቻሉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ