1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ተጠባባቂ ጦር ምሥረታ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 25 2007

አፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ክፍል አዲስ ስለሚቋቋመው የአፍሪካ ተጠባባቂ ጦር ሃይል በዚምባብዌ ዋና ከተማ ሃራሬ ስልጠና እየሰጠ ነው።

https://p.dw.com/p/1Dgj1
Eastern Africa Standby Force
ምስል DW/L. Ndinda

ክፍሉ የቡርኪና ፋሶን ነባራዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን እና የምዕራብ አፍሪካዋ ሃገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ዴሞክራሲያዊ መንግስታዊ ሥርዓት ትመለሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል። በቡርኪና ፋሶ የ27 ዓመታት የብሌዝ ኮምፓዎሬ አገዛዝ አብቅቶ የሃገሪቱ ጦር ስልጣን ጨብጧል። በሚቀጥለው ሚያዝያ ወር ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን የአፍሪካ ተጠባባቂ ጦር ሃይል (African Standby Force) የምስረታ ሂደት በበላይነት የሚመሩት ጄኔራል ሳማይላ ኢሊያ የአፍሪካ ህብረት ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ይናገራሉ።
''የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ህብረት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ትክክለኛው መንገድ ብዙ ተጉዟል። ለውጥ መፍጠርም ችሏል።ሰ ዎች ይህንን ሊጠራጠሩ ይችላሉ። ነገር ግን በጣም ግልጽ ነው። በቡርኪና ፋሶ ያለው ሁኔታ እንደተፈጠረ ሃገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመለስ እንዳለባት አቋም ወስዷል።''
ናይጄሪያዊው ጄኔራል ሳማይላ ኢላይ በሃራሬ እየተሰጠ ያለው ስልጠና የ 'አማኒ' እቅድ አንድ አካል መሆኑን ይናገራሉ። አማኒ የሚለው ቃል በኬንያ፤ ታንዛኒያ፤ እንዲሁም በከፊል ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ዉስጥ በሚነገረው የኪ ስዋሂሊ ቋንቋ ሰላም ማለት ነው። ጄኔራል ሳማይላ ኢላይ የአፍሪካ ተጠባባቂ ጦር በአህጉሪቱ ሊፈጠሩ ለሚችሉ የሰላምና ደህንነት ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት ታስቦ እንደተዘጋጀ ይናገራሉ።
''የአፍሪካ ተጠባባቂ ጦር የሰላምና ደህንነት መዋቅር አንድ አካል ነው። የደህንነት መዋቅሩ የቅድመ ማስጠንቀቂያ፤ የአማካሪዎች መድረክ እና የጦር መኮንኖች ኮሚቴ ይኖረዋል። የአፍሪካውያን ባለቤትነት የሚመራው ይህ መዋቅር እነዚህና ሌሎች መንገዶችም ይኖሩታል። በአህጉሪቱ የሰላምና የደህንነት ስጋት ቢፈጠር ይህን አቅም ይጠቀማል።''
የአፍሪካ ተጠባባቂ ጦር በአህጉሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ዝግጁ ሃይሎች ይኖሩታል። የአውሮፓ ህብረት የተጠባባቂ ጦሩን ምስረታ እውን ለማድረግ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። የአውሮፓ ህብረት ተወካይ የሆኑት ኮሎኔል አንቶን ጋሽ ተጠባባቂ ጦሩ አፍሪካ ለውስጥ ችግሮቿ አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት ያስችላታል ብለው ያምናሉ።
''የአፍሪካ ተጠባባቂ ጦር የማቋቋሙ ሃሳብ ጠቃሚ እንደሆነ እናምናለን። ተልዕኮን በሙሉ ብቃት ሊፈጽም የሚችል ሃይል መዘጋጀቱ አፍሪካ የራሷን ውሳኔ እንድትወስን እና ለውስጣዊ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት ስለሚያስችል ታሪካዊ ነው። የአፍሪካ ተጠባባቂ ጦር ሲኖር ቀሪው አለም እገዛ ማድረጉን ያቆማል ማለት አይደለም። ነገር ግን በራስ ጉዳይ ላይ በነጻነት የመወሰን ነጻነት እና በፍጥነት ምላሽ የመስጠት ተጨማሪ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ማለት ነው።''
ከዚህ ቀደም አይቮሪኮስትን የመሳሰሉ ሃገሮች ውስጣዊ ችግሮች ሲገጥሟቸው የቀድሞ ቅኝ ገዢዎቻቸውን እገዛ ለመጠየቅ ተገደዋል። ከአመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እውን ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪካ ተጠባባቂ ጦር ይህን አሳፋሪ ውሳኔ ታሪክ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

Eastern Africa Standby Force
ምስል DW/L. Ndinda
Südafrika Township Regenfälle Überschwemmung Hunger Armut Afrika
ምስል Ap

ኮሎምበስ ማቩንጋ/እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ