1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ፍፃሜ

ረቡዕ፣ ጥር 17 1998

የአፍሪቃ ኅብረት የዘንድሮ ፕሬዚደንትነት ጉዳይ

https://p.dw.com/p/E0j7
የአፍሪቃ ኅብረት ምልክት
የአፍሪቃ ኅብረት ምልክት

በሱዳን መዲና ካርቱም የተካሄደው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአስተናጋጅዋ ሱዳን ፈንታ ኮንጎ ብራዛቪል የዘንድሮውን የኅብረቱን ሊቀ መንበርነት ሥልጣን እንድትይዝ በመስማማት ትናንት ተጠናቀቀ። መሪዎቹ የኅብረቱን የሊቀመንበርነት ሥልጣን እንደታቀደው ለሱዳን ያልሰጡት የሱዳን መንግሥት በዳርፉር ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ያካሂዳል በሚል ከያቅጣጫው ብርቱ ወቀሳ በመፈራረቁ ነው። የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ኤል በሺር ከብዙ ክርክር በኋላ ነበር ባለፈው ሰኞ ለሊቀመንበርነቱ ሥልጣን ያስገቡትን ማመልከቻቸውን የሳቡት።
ለነገሩ፡ ኅብረቱ ጊዜውን በክርክር የሚያጠፋበት ሂደት ያለፈ ታሪክ መሆን ነበረበት። ለአፍሪቃውያን ችግሮች አፍሪቃውያን መፍትሔዎች የሚል መፈክር ይዞ ነበር የአፍሪቃ ኅብረት እአአ በ 2002 ዓም የተቋቋመው። ነገር ግን በካርቱም፡ ሱዳን ትናንት የተጠናቀቀው ዓቢይ ጉባዔ ይህን የኅብረቱን ዓላማ አላሟላም። በኅብረቱ ፕሬዚደንትነት ሥልጣን ዙርያ የተነሳው ክርክር ጉባዔውን በዋነኝነት ያነጋገረ ጉዳይ ነበርና።
ኅብረቱ አሁን የየኮንጎ ብራዚቭል ፕሬዚደንት ዴኒ ሳሱ ንጌሶን ሊቀ መንበሩ አድርጎ በመረጠበት ውሳኔው ታማኝ እና ችሎታ ያለው ግለሰብ ማግኘቱን ያንፀባረቅ መስሎዋል። በተለይ፡ የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ኤል በሺርን ለዚሁ ሥልጣን ያልመረጠበት ውሳኔው እንደ ትልቅ ስኬት ተቆጥሮለታል። ይኸው ጉዳይ የኅብረቱን ታማኝነትና የአህጉሩን ውዝግቦች የመሸምገል አቅሙን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎ ነበርና።
በምዕራብ ሱዳን በሚገኘው የዳርፉር ግዛት ከብዙ ዓመታት ወዲህ ለሚታየው አስከፊ የሰብዓዊ መቅሠፍት ተጠያቂ ናቸው በሚል ምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን « የዳርፉር አራጅ » የሚሉዋቸው ኦማር ኤል በሺር ለዚሁ ሥልጣን እንደማይበቁ የኅብረቱ ውሳኔ አጉልቶዋል።
ዳርፉር ለአፍሪቃ ኅብረት የሰላም ጥረቶች መለኪያ ሆኖ ነው የሚታየው። ሰባት ሺህ የአፍሪቃ ኅብረት ወታደሮች በዳርፉር ሰላም የማውረድ ተልዕኮ ቢጀምሩም፡ እስካሁን አካባቢው ሰላም አላገኘም። የአፍሪቃ ኅብረት በታሪኩ ውስት ለመጀመሪያ ጊዜ የላከው እና በዳርፉር የተሠማራው ሰላም አስከባሪ ጓድ ተልዕኮ በወቅቱ ከሞላ ጎደል እንደከሸፈ ነው የታየው። ጃንጃዌድ በመባል የሚታወቁት እና ከካርቱም መንግሥት ይፋ ያልሆነ የገንዘብ፡ የትጥቅና የስንቅ ድጋፍ የሚያገኙት ዐረባውያን ሚሊሲያዎች እአአ ከ 2003 ዓም ወዲህ በዳርፉር ጥንታዊ ነዋሪ በሆነው ሲቭል ሕዝብ አንፃር ተመሳሳይ የሌለው ውጊያና ጭፍጨፋ ማካሄዱን እንደቀጠሉ ነው። በውዝግቡ ከአንድ መቶ ሰማንያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጡም ስደት መግባት ተገደዋል። ዓለም አቀፉ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤትም በዳርፉር በየቀኑ የቀጠለው ጭፍጨፋ የጦር ወንጀል መሆን አለመሆኑን በማጣራት ላይ ይገኛል። እንዲያውም፡ ዩኤስ አሜሪካ የዳርፉር ሁኔታ በሱዳን መንግሥት የሚደገፍ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እንደሆነ ነው የምትናገረው።
በዚህ ሁሉ መሀል መነሳት የነበረባቸው ለምሳሌ፡ በአይቨሪ ኮስት የሚታየው አለመረጋጋት፡ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ምርጫን እንዴት በዓለም አቀፍ ርዳታ ማረጋገጥ የሚቻልበት ጉዳይ፡ በቻድና በሱዳን መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ፡ የቀድሞው የቻድ አምባገነን መሪ ሂስኔ ሀብሬ በቤልጅየም ለፍርድ ይቅረቡ የተባለበት ጥያቄ እና የዳርፉር አሳሳቢ ሁኔታን የመሳሰሉ የአህጉሩ አንገብጋቢ ጉዳዮጭ ትኩረት ሳያገኙ ቀርተዋል።
ይህ ሲታሰብ ታድያ፡ በአህጉሩ መፍትሔ የሚጠብቁ ብዙ ችግሮች መኖራቸው ይጎላል። የአፍሪቃ ኅብረት ከሦስት ዓመት በፊት የተካው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የፈፀመውን ዓይነት ስህተት እንዳይሰራና የባዶ ክርክር ክበብ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል። ኅብረቱ ለአፍሪቃ ችግሮች አፍሪቃውያን መፍትሔዎች የሚሰኘውን ዓላማ ይዞ ቢነሳም፡ ይኸው ዓላማው በካርቱም በተጠናቀቀው የመሪዎች ጉባዔ ላይ የሚፈለገውን ትኩረት አላገኘም።