1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም የአፈር ካርታ፣

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 2005

በዓለማችን አንድ ቢሊዮን ያህል ህዝብ በካባድ ድህነት የሚማቅቅ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ነው የሚነገረው። ችግሩን ለመቅረፍ፤ ከተቻለም ለማስወገድ ዓለም አቀፍ ርብርቦሽ ካልተደረገ አሁን ከሚነገረው የከፋ ሁኔታ ነው ሊያጋጥም የሚችለው። ረሃብ ፤ ድህነትን

https://p.dw.com/p/18QEE
ምስል Fatoumata Diabate/Oxfam

መቋቋሚያው አንዱ መንገድ፣  የእህልን ምርት መጨመርና ግብርናው በክብካቤ ፣ ቀጣይነት እንዲኖረው ማብቃት ነው። ይህን ለማሻሻልም ፣  ሳይንሳዊ  ምርምርና ሥነ ቴክኒካዊ ድጋፍ የግድ ይላል።

የአውሮፓው ኅብረት፤ የአፍሪቃ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት  የምግብና የግብርና ድርጅት (FAO) በኅብረት  ያወጡትን የአፍሪቃ የአፈር ካርታ(አትላስ) በበረሃ መስፋፋት፣ በድርቅና በጎርፍ ፣ አፈር ብርቱ  የመሸርሸር አደጋ የተደቀነበት መሆኑን ያስረዳል።

Karte Afrika Sahelzone englisch Flash-Galerie

እርግጥ ነው በሳሔል መቀነት የሚገኙ አገሮች፤ ለዚህ አስከፊ አደጋ መጋለጣቸውና የሰሃራ ምድረበዳ በያመቱ እየሰፋ ወደ ምድር ሰቅ የሚያመራ ነው የሚመስለው።

ባለፈው ዓርብ፤ የአውሮፓ ኅብረት የምርምር ኮሚሽን ዋና ኀላፊ፤ ሜ ር  ጊዎግሄጋን -ኪን ፣ አዲስ አበባ ውስጥ አዲሱን የአፍሪቃን የአፈር ካርታ ይፋ አድርገዋል።  አዲሱ ካርታ እንደሚጠቁመው ከሳሄል አገሮች ውጭ  የትኞቹ አገሮች ናቸው የአፈር መቅኖ ማጣት ችግር ያስከተለባቸው? በአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የምርምር ማእከል፣ የአፈር  ክብካቤ ክፍል፣ በተለይ የአፍሪቃ የአፈር ምርምር ክፍል ኀላፊ የሆኑትን ማርቪን ጆንስን ጠይቄአቸው ነበር።

«የበረሃ የመስፋፋት ሂደት ፣ አሁን የጠቀስከው አደጋ በተለይ በረሃው ጫፍ ወይም አዋሳኝ  ያለውን አካባቢ የሚመለከት ነው። ይሁን እንጂ፣ ሌሎች ለአፍሪቃ ምድር አፈር ፣ ችግር የደቀኑ ሁኔታዎች አሉ። ዋናው የአፈር ለምነት መክሰም ነው። ይህ ደግሞ በተለይ በማእከላዊው ሞቃት የአፍሪቃ ክፍልም በመከሠት ላይ ያለ ችግር ነው።  ምክንያቱም ፣ አፈሩ፣ ያረጀ፣ የተሸረሸረ፣ በተንሠራፋ የገጠር ድህነት ሳቢያ በተደጋጋሚ እየታረሰ ለምነቱን ያጣ አፈርም ነው።

አብዛኞቹ አነስተኛ ይዞታ ወይም ትንንሽ ማሳዎች ያሏቸው አፍሪቃውያን አርሶ አደሮች፣ የአፈሩን ለምነት ለመጠበቅ፤ በማዳበሪያ ማገዝ የሚያስችል አቅም የላቸውም። አፈሩ፣ ያለክብካቤ መታረሱ፣ ሲበዛበት አካባቢው በአፋጣኝ የማዕድናት እጦት ያጋጥመውና እህል ማብቀል ይሳነዋል።

ይህ  በሰፊው፤ በማዕከላዊውና በምድረ ሰቅ አካባቢ የአፍሪቃ ክፍል የተዛመተ ችግር ነው። ይህ እንደእውነቱ ከሆነ የምድረ በዳ አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች ፤ በሳሔል አገሮች ፣ ሰፋ ባለው የኢትዮጵያ ክፍል፣ እንዲሁም ከካላሃሪ ምድረ በዳ  በሚዋሰነው ሰፋ ባለው የደቡባዊው የአፍሪቃ ክፍል ፣ እንዲሁም ከፊል ሞዛምቢክ የዚህ ችግር ተጠቂዎች  ናቸው። »

(ይቀጥላል)

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ