1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ወጣት እድል በ2018 ዓም

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 28 2010

በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓም በዚምባብዌ፣ ካሜሩን እና በጊኒ ምርጫዎች ይካሄዳሉ። ይህም ቢሆን ግን ምርጫዎቹ በስልጣን ደረጃ የትውልድ ለውጥ ያስገኛሉ ተብሎ የሚጠበቁ አይደለም።

https://p.dw.com/p/2qPd2
Nigeria Präsident Muhammadu Buhari und Paul Biya aus Kamerun
ምስል DW/Abuja

በዩኤስ አሜሪካ የቫሰር ኮሌጅ የአፍሪቃ ጥናትቶች መምህር ፕሮፌሰር ዛካሪያ ማምፒሊ እንደሚሉት፣ በዚምባብዌ ሆነ በካሜሩን ወይም በጊኒ ስልጣን ላይ የሚገኙት ርዕሳነ ብሔር ጡረታ የመውጣት እቅድ የላቸውም። የካሜሩን ፕሬዚደንት ፖል ቢያ 85 ፣ የጊኒ አቻቸው አልፋ ኮንዴ ደግሞ 80 ዓመታቸው ነው። የ75 ዓመቱ አዲሱ የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በሁለቱ ቻዎቻቸው አንፃር በዕድሜ ትንሹ ናቸው።  
«ባጠቃላይ አፍሪቃውያት ሀገራት በመሪዎቻቸው እና በወጣቶቻቸው መካከል ትልቅ የዕድሜ ልዩነት ይታይባቸዋል። የአመራሩን ተግባር በቅርቡ ለወጣቱ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ዓቢይ የተሀድሶ ለውጥ የማድረግ እቅድም በነዚህ ሀገራት ውስጥ ያለ አይመስለኝም።»
ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የመብት ተሟጋቿ ሊንዳ ማዜሪሬ « በዕድሙ በተዳከሙ መሪዎች ነው የምንተዳደረው » በማለት የርሳቸውን እና የአህጉሩን ወጣት ትውልድ ቅሬታ ገልጸዋል። የ35 ዓመቷ ማዚሪሬ የቀድሞ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ አምባገነን መንግሥት አንፃር ታግለዋል። ሙጋቤን የተኩት ምናንጋግዋም ቢሆኑ ግን ለተሟጋቿ ከሙጋቤ የተለዩ አይደሉም ነው የሚሉት።  በዕድሜ የገፉትአዲሶቹ የዚምባብዌ  ፖለቲከኞች የወጣት ዜጎቻቸውን ፍላጎት አገናዝበው ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ ፈንታ ችላ እንዳሉት ማዚሪሬ አስታውቀዋል።
«በሕይወታቸው አንድ ቀን እንኳን ስራ ሰርተው የማያውቁ ዕድሜአቸው  35፣ 37፣ 40 ዓመት የሆናቸው ዜጎች አሉን። እነዚህ ሰዎች የደሞዝ ወረቀት ተቀብለውም  ሆነ የማህበራዊ ኑሮ ድጎማ የማግኘት እድልም ኖሯቸው አያውቁም።  በ18 እና በ25 ዓመት መካከል ካሉት ወጣቶች መካከል  ብዙዎቹ  የአደንዛዥ እጾች እና ንጥረ ነገሮች ሱሰኞች ሆነዋል። ምክንያቱም ተስፋ ቆርጠዋል፣ የወደፊቱ እድላቸውም ፍሬ አልባ ሆኖ ነው የሚታያቸው። »
ለወጣቱ ትውልድ የወደፊቱ እድል ጨለማ የሆነበት ግን ዚምባብዌ ውስጥ ብቻ አይደለም።  በአህጉሩ በ15 እና 24 ዓመት መካከል የሚገኘው ወጣት ቁጥር 200 ሚልዮን ነው። ከዚሁ መካከል ግን 60% ስራ አጥ ነው። ስራ ካላቸውም መካከል ብዙዎቹ የሰራተኛ ድሀ እየተባለ የሚጠራው ቡድን ውስጥ ነው የሚመደቡት። በሚያገኙት ደሞዝ ኑሯቸውን እንኳን መምራት አይችሉም። 
ሊንዳ ማዚሪሬ ይህን ሁኔታ እንዳለ መቀበል አይፈልጉም። በሀገሯ ዚምባብዌ መስከረም 2018 ምርጫ ይደረጋል። በምርጫው በነፃ ተወዳዳሪ እጩነት መቅረብ ይፈልጋሉ።  ከአቻዎቻቸው ጋር በመሆን አንድ የወጣቶች ፓርቲ የማቋቋም እቅድ አላቸው። በአንፃራቸው ብዙዎቹ የዚምባብዌ ወጣቶች በፖለቲካው ተግባር መሳተፉን እንደሚፈሩት ማዚሪሬ አስታውቀዋል።
«በዚምባብዌ  በፖለቲካ ፓርቲዎቻችን  ውስጥ ፣ በገዢው ፓርቲ  ይሁን በተቃዋሚው ጎራ፣  ብዙ ጥቃት እና የኃይል ርምጃ ይታያል።   በተለይ ብዙዎቹ ወጣት ሴቶች ይህን ሁኔታ፣ ማለትም፣ የሚደርስባቸውን ብዙ ትንኮሳ  እና መሰል ጥቃት  መቋቋም አይችሉም።   በዚህም የተነሳ ብዙ የዚምባብዌ ወጣቶች  በሀገራቸው የፖለቲካ ውሳኔ አሰጣጥ ቦታም ሆነ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከፍተኛው የአመራር ደረጃ ላይ የመድረስ ዕድል የላቸውም። »   
የናሚቢያ ዜጋ የሆነኑት ጆብ ሺፑሉሎ አሙፓንዳ በዚሁ ረገድ ጥሩ ተሞክሮ የላቸውም። የ30 ዓመቱ የፖለቲካ ሳይንስ  ምሁር ቀደም ባለ ጊዜ የገዢው የ የስዋፖ ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ሊቀ መንበር ነብረ ዛሬ ከቡድኑ ጋር ባንድነት በድህነት እና በሙስና አንፃር፣ እንዲሁም እኩልነት እንዲኖር በመጠየቅ አደባባይ በመውጣት ትግላቸውን ቀጥለዋል። የሺፑሊሎ አፑማንዳም  ተቃውሞው በራሳቸው ፓርቲም ላይ ያነጣጠረ ነው። በዚህ የተነሳም ከገዚው ፓርቲ ብርቱ ተቃውሞ የገጠማቸው ሺፑሊሎ አፑማንዳ  በፍርድ ቤት ብይን ባይሆን ኖሮ የፓርቲው አባል ሆነው መቀጠል ባልቻሉ ነበር። በስዋፖ ውስጥ ወጣቶች አዳዲስ ሀሳቦችን ይዘው የሚመጡበት እና ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ድርጊት ብዙም እንደማይደገፍ ነው ሺፑሊሎ አፑማንዳ ያመለከቱት።  
«ወጣቶች በፖለቲካው መድረክ ላይ ደፈር ብለው መናገር ሲጀምሩ የፓርቲ አባላቱ ብዙ ጊዜ  «እኛ ለነፃነት ስንታገል አንተ የት ነበርክ?» ብለው ይጠይቋቸዋል። የትምህርት ደረጃህ፣ ግልጽነትህ ወይም ለመስራት የምትፈልገውን ወደጎን በመተው በትግሉ ውስጥ የተጫወትከውን  ሚና ይጠይቁኃል።»
ብዙ አፍሪቃውያን ወጣቶች የፓርቲዎች ዴሞክራሲ ብዙም ትርጉም የለውም። አፍሮባሮሜትር የተባለው የፓንአፍሪካ ምርምር መረብ  በ2016 ዓም ባወጣው የወጣቱ ፍላጎት መመዘኛ መዘርዝር መሰረት፣ ከ18 እስከ 35 ዓመት ከሆናቸው ወጣቶች መካከል 65% ብቻ ነበሩ በሀገራቸው በመጨረሻ በተካሄደ ምርጫ ላይ ድምጻቸውን የሰጡት።  
በ2015 እና 2016 ዓም በብዙ አፍሪቃውያት ሀገራት ውስጥ ተቃውሞ ተካሂዷል። በዚምባብዌ እና በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ወጣቶች በተጠሉት ፕሬዚደንቶቻቸው አንፃር በተደጋጋሚ ተቃውሞ አድርገዋል ። በሴኔጋል እና በቡርኪና ፋሶም ተቃዋሚዎች አምባገነን መሪዎቻቸውን ከስልጣን አባረዋል። በሌሎች አፍሪቃውያትሀገራት ግን ተቃውሞዎቹ ያን ያህል አልተሳኩም ይላሉ ፕሮፌሰር ዛካሪያ ማምፒሌ።
«ወጣቶቹ  ምርጫ ማካሄድ ብቻውን  በቂ ሆኖ አላገኙትም። ለዚህም ጥሩ ምክንያት አላቸው። ይሁን እንጂ፣ ይህ ነገሮችን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ አያደርጋቸውም። በዚህ ፈንታ ድምፃቸውን ለማሰማት ሌላ አማራጭ ያፈላልጋሉ ማለት ነው። በዚህም ወቅት ተቃውሞ ማካሄድን እንደ አንድ ዘዴ ይጠቀሙበታል።  ትልቁ አደጋ ግን ተቃውሞው እንዴት እንደሚካሄድ እና ምን እንደሚያስከትል መተንበይ አለመቻሉ ነው። እነዚህ ትልቅ ተሰጥዖ ያላቸው ፣ ተስፈኞቹ ወጣቶች አደባባይ በሚወጡበት ጊዜ   አዘውትረው ተመጣጣኝ ካልሆነ  የጦር ኃይል ርምጃ  ጋር  ሲጋፈጡ ማየት ልብ ሰባሪ ነው።» 

Burkina Faso Proteste und Gewalt
ምስል Getty Images/AFP/S. Kambou
Namibia Wahlen Ministerpräsident Hage Geingob Wahlkampf in Windhoek
ምስል picture-alliance/AP Photo/Themba Hadebe
Afrika junge Männer arbeitslos
ምስል picture-alliance/dpa/N. Bothma

የችግሩን አሳሳቢነት በይፋ ያስታወቀው የአፍሪቃ ህብረት በጎርጎሪዮሳዊው 2006 ዓም የአፍሪቃ ወጣቶች ሰነድ አውጥቷል፣ ከጎርጎሪዮሳዊው 2009 እስከ 2018 ዓም የሚዘልቅ የአፍሪቃ ወጣቶች የአስር ዓመት የተግባር እቅድም አውጥቷል። እቅዱ በአፍሪቃ የወጣቶች ሰነድ የተቀመጡትን ዓላማዎች  ከግብ የማድረስ እና የወጣቱንም አቅም በፖለቲካው እና በልማቱ ዘርፍ የማጎልበት ዓላማ ይዞ ተነስቷል። ይሁን እንጂ፣ የዚምባብዌ ተወላጇ የመብት ተሟጋች ሊንዳ ማዜሪሬ በሰነዱ ስለተቀመጡት አማላይ ቃላት መስማት አትፈልግም። ማዜሪሬ እንደምትለው፣ የአፍሪቃ ወጣት ችሎታ የሌላቸውን መሪዎቹን  የመጠየቅ  እና በተፈጥሮ ሀብት የታደለውንም አህጉር ወደፊት ማራመድ በሚችሉ ብቁ መሪዎች የመተካት ኃላፊነት አለበት።  

 አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

እሸቴ በቀለ