1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ የኢኮኖሚ እድገት እና ዘላቂነቱ

ሰኞ፣ ሐምሌ 28 2006

ያለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለአፍሪቃ ጠቃሚ ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ ካሏቸው 500 ወጣት አፍሪቃውያን ጋር ተነጋግረዋል። ዛሬ ደግሞ 50 ከሚሆኑ አፍሪቃውያን መሪዎች ጋር ለሶስት ቀናት ሊወያዩ ሌላ ጉባኤ ከፍተዋል።

https://p.dw.com/p/1Coje
Kenia Kaffee Ernte Arbeiter
ምስል TONY KARUMBA/AFP/Getty Images

በጉባኤውም ከሰላም እና ልማት ጥያቄዎች ባለፈ አንድ ትልቅ መወያያ ርዕስ ተይዟል። የምጣኔ ሀብት! ለመሆኑ የአፍሪቃ የኢኮኖሚ እድገት ምን ያህል ዘላቂነት አለው?«የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ጣራ እየነካ ነው»፣«ለባለወረቶች የአፍሪቃ አህጉር ትልቅ እድል ከፋች ናት» የሚሉ ርዕሶች ካለፉት ዓመታት አንስቶ ምዕራባውያን ለአፍሪቃ ያላቸውን አመለካከት ይቀይሩ ዘንድ በየቦታው ይነበባሉ። በርግጥ እድገቱን የሚያመላክቱት አሀዞች ቀልብ የሚስቡ ናቸዉ። ባለፈው ዓመት 4 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለዘንድሮው እና የሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 5 ከመቶ ግድም እና እስከ 5.7 ከመቶ ሊደርስ እንደሚችል ምሁራን ይተነብያሉ። እንደ የአፍሪቃ የልማት ባንክ ከሆነማ ከዛሬ 14 ዓመት በፊት ከነበረዉ በአራት እጥፍ የሚልቅ መዋዕለ ንዋይ በያዝነው ዓመት ወደ አፍሪቃ ይፈሳል ብሎ ያምናል። የማያያልቅ የነዳጅ ዘይት ሐብት እና ለእርሻ የሚሆን ሰፊ መሬት ለዚህ መስብ ምክንያት ነው።

መቼም ባራክ ኦባማ ዛሬ ያገኟቸውን 50 የአፍሪቃ መሪዎች እና የመንግስት ተወካዮችን ሲጋብዙ ይህን ሁሉ ከግምት አስገብተው ነው። ከዚህ ትልቅ ጉባኤ የአፍሪቃውያኑም ቢሆኑ ትልቅ ነገር ይጠብቃሉ ይላል የአሜሪካ ነዋሪ የሆነዉ ሴራሊዎናዊው አዮ ጆንሰን። ጋዜጠኛ እና « ቪውፖይንት አፍሪቃ» የተሰኘው የአፍሪቃ ድረ ገፅ መሥራች ነው።« ከ50 የሀገር ተወካዮች ውስጥ በርካቶቹ በዚህ ጉባኤ ከዮናይትድ ስቴትስ ጋር ጥብቅ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንደሚፈጥሩ፤ ተስፋ ያደርጋሉ። ሊጠቀሙባቸዉ የሚችሉ እንዴት ያሉ እድሎች እንዳሉም ይመረምራሉ፤ አፍሪቃዉያኑ የተለያዩ ባለሃብቶችን መምረጥ የሚችሉበት አጋጣሚ አድርገዉም ያዩታል።»

Obama in Tansania
ፕሬዚዳንት ኦባማ በታንዛንያምስል Reuters

አፍሪቃ ውስጥ እስካሁን በሰፊዉ ሃብትን ሥራ ላይ በማዋል ረገድ ጎልታ የምትታየዉ አንድ ሀገር ናት። የቻይና። ቻይና መንገድ ትገነባለች፣ የአገልግሎት ሸቀጦችን ትሸጣለች፤ እንዲሁም ቻይና ጥሬ ሀብትም ትገዛለች። ሀገሪቷ የአፍሪቃ ትልቅ የንግድ አጋር በመሆንም አሜሪካን ታስከነዳለች።

የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ከፍ ብሎ እንዲያድግ ዋና ምክንያት የሆነው ጥሬ ሀብት ነው። የነጃድም ይሁን የማዕድናት፤ የግብርና ውጤቶች የሆኑት የነቡና፣ ካካኦ ፤ ሻይቅጠል እና ሌሎችም ምርቶች ዋጋ በዓለም ገበያ ከፍ እንዳለ ነው። ይህ ብቻ አይደለም ይላሉ በጎቲንገን ዮኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሽቴፈን ክላስን። እንደ መምህሩ በርካታ የአፍሪቃ መንግስታት ባለፉት ዓመታት ኢኮኖሚያቸውን በአግባቡ መርተዋል። ይሁንና በዘይት ሀብቷ የተነሳ ትልቅ እድገት ባስመዘገበችው ናይጄሪያ እድገቱ ጎልቶ አይታይም። በደሀ እና በሀብታሙ መካከል ያለው ልዩነትም ሰፊ ነው ይላሉ።«ይህ ከእድገቱ መንስኤ ጋር የተያያዘ ነው። ጥሬ ሀብት ላይ የተመሠረተ ከሆነና አንዳንድ ጥሬ ሀብቶች ደግሞ በጥቂቶች ቁጥጥር ስር እስከሆኑ ድረስ ብዙ የሥራ እድል አይፈጥሩም። በዚህም የተነሳ ከደሀው እጅ አይደርስም። ይልቁንም እንደ ቡና እና ካካኦ ያሉ ጥሬ ሀብቶች ግን የበለጠ ለህብረተሰቡ ጥቅም ይፈጥራሉ።»

Öl in Nigeria
የነዳጅ ምርት በናይጄሪያምስል picture-alliance/dpa

ነገር ግን የነዳጅ ዘይት እና ቡና የመሳሰሉት ጥሬ ሀብቶች ዋጋ የቀነሰ ጊዜ ወደላይ የሚመጥቀው የአፍሪቃ የኢኮኖሚ እድገት መልሶ ወደ ታች ሊያሽቆለቁል ይችላል። ምክንያቱም በጥሬ ሀብት ላይ ብቻ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ዘላቂነት የሚኖረው በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ነውና። ለዚህ ቦትሱዋና ጥሩ ምሳሌ ልትሆን ትችላለች። የሀገሪቱ የአልማዝ ሀብት ያላትን ትንሽ ህዝብ ለማስተዳደር አጥጋቢ ሊሆን ይችላል። ለተቀሩት የአፍሪቃ ሃገራት ግን ኢኮኖሚያቸው በየጊዜው ከሚጨምረው ህዝባቸው ጋ ዘላቂነት ኖሮት እንዲቀጥል ጥሬ ሀብቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለኅብረተሰቡ ሥራ የሚፈጥር ኢንዱስትሪም መክፈት ወሳኝ ነው። ለዚህ ሂደት ደግሞ ዮናይትድ ስቴትስ ወሳኝ ሚና ልትጫወት ትችላለች ይላሉ የዮኒቨርሲቲ መምህሩ ክላስን።

50 የሚሆኑት የአፍሪቃ ሃገራት እንግዲህ በአህጉራቸው የኢኮኖሚ እድገትና ከዩናይትድ ስቴትስን ጋ በሚኖራቸዉ ትስስር ላይ እስከ ረቡዕ ድረስ ከዮናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር ለመወያየት ዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተዋል። የዩ ኤስ የልማት ኃላፊዎች አስቀድመው እንደተናገሩት ከሆነም ደግሞ አሜሪካ የንግድና መሰል ስምምነቶችን ለማድረግ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር መድባለች።

ሂልከ ፊሸር/ ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ