1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 4 1997

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዉስጥ ብዛት ያሉት አባላትን ያካተተዉ የ53 አገራት ተወካዩ የአፍሪካ ህብረት በፀጥታዉ ምክር ቤት እንዲሰጠዉ ያቀረበዉን የሁለት ቋሚ መቀመጫ ጥያቄ ገፍቶበታል። እንደ አፍሪካ ህብረት ሁሉ ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት በመታገል ላይ የሚገኙት አራት አገራት ወንበሩን ካገኛችሁ ሌላ አትጠይቁ የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/E0jc
አንዳንድ የአፍሪካ አገራትም ይህን ሃሳብ ደግመዉ ለህብረቱ ቢያቀርቡም አቋሙን አለወጠም። ድምፅን በድምፅ የመሻር መብትን በፀጥታዉ ምክር ቤት ከሚኖረዉ ቋሚ መቀመጫ እኩል ይገባኛል በሚል።
ምንም እንኳን ድምፅን በድምፅ የመሻር ሃይልን የማግኘቱ ነገር ከወዲሁ ከባድ ተደርጎ ቢታይም የአፍሪካ ህብረት በፓለቲካ የብዙሃን ድምፅ ስልጣኑን ተጠቅሞ ጥያቄዉን አልተዉም ብሏል።
ይህን ቁርጠኛ አቋሙንም ያሳየዉም ባለፈዉ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ባካሄደዉ ሁለተኛ ጉባኤ ከጀርመን፤ ከጃፓን፤ ከህንድና ከብራዚል የቀረበለትን ቋሚ መቀመጫ እንጂ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት አትጠይቁ የሚለዉን ጥያቄ ዉድቅ በማድረግ ነዉ።
እነዚህ አገራት በፀጥታዉ ምክር ቤት ያለዉ የአባላት ቁጥር ከ15 በላይ ከፍ እንዲል ቅስቀሳ እያካሄዱ ያሉ ሲሆን በራሳቸዉ ላይ ከነባር ቋሚ አባላት የሚነሳባቸዉን ተቃዉሞ ለመከላከል ሲሉ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት የሚለዉን ጥያቄ አንስተዋል።
ምክንያቱም አምስቱ የጸጥታዉ ምክር ቤት አባላት ማለትም ዩናይትድ ስቴትስ፤ ፈረንሳይ፤ ብሪታንያ፤ ቻይናና ሩሲያ ይህን መሰሉን ሃይላቸዉን ያለተቀናቃኝ ይዘዉ መዝለቅ ይፈልጋሉ።
ከዚህም ሌላ አንድ አፍሪካዊ ዲፕሎማት እንደገለፁት ጉባኤዉ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በሆነችዉ ናይጀሪያም የቀረበዉን ቋሚ መቀመጫ ብቻ እንጠይቅ የሚል ሃሳብ አልተቀበለም።
ሆኖም የአፍሪካ ህብረት በራሱ ያወጣዉ መግለጫ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸዉ አገራት ተጨምረዉ የቋሚ አባላት ቁጥር ይቀነስ የሚለዉ ሃሳብ አሁን የሚለይለት ነጥብ ላይ በድጋሚ ደርሷል።
በአፍሪካ ህብረት የቀረበዉ ረቂቅ ሰነድ በምክር ቤቱ የሚገቡት አዲሶቹ ቋሚ አባላት እንደነባሮቹ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብትን ጨምሮ ተመሳሳይ የሆነ ስልጣንና ጥቅም ሊሰጣቸዉ ይገባል ይላል።
ይህ የአፍሪካ ህብረት መግለጫም በሐምሌ ወር በሊቢያ ዋና ከተማ በተካሄደዉ የመጀመሪያ ጉባኤዉ የደረሰበት ዉሳኔ ተከታይ መሆኑ ነዉ።
የአፍሪካ ህብረት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ለማግኘት የጀመረዉን ጥያቄ ሊገፋበት ይገባል የሚሉትም በርክተዋል።
ዋሽንግተን የሚገኘዉ ትራንዝአፍሪካ የተባለዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፕሬዝደንት ቢል ፍሌትሸር ቁጥራቸዉ ወደአንድ ቢሊየን የሚጠጉ ህብዝቦችን የሚወክለዉ የአፍሪካዉ ህብረት ይህን መሰል ስልጣን ከሌለዉ ሊጠቅመዉ አይችልም ይላሉ።
ጨምረዉ ሲያብራሩም በፀጥታዉ ምክር ቤት መሳተፍ ማለት ለሁሉም አባላት በተመሳሳይ ደረጃ መሆን ይኖርበታል ወይም ደግሞ የሚሰራዉ ሁሉ ተዉኔት ነዉ ተብሎ ቢተዉ ይሻላል።
ባለፈዉ ወር አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጣ ስማቸዉን ያልገለፀዉን የአገሪቱን ባለስልጣን ጠቅሶ እንደዘገበዉ አገራቸዉ ለአዲስ አባላት ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን በመስጠቱ ላይ የራሷ ስጋት አላት።
ይህም ምናልባት የፀጥታ ምክር ቤቱን አሰራር ያሽመደምደዋል ከሚልና በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዉስጥ ያላትን አቅም ይጋፋል ብሎ ከማሰብ የመነጨ ነዉ።
የአፍሪካ የልማት ተቋም ዳይሬክተር ኩዋሜ አክኖር በበኩላቸዉ የፀጥታ ምክር ቤቱን የማስተካከሉ ነገር መሰታዊ የሆነዉን የስልጣን መዋቅር የማይነካ ከሆነ ምን ትርጉም አለዉ? ሲሉ ይጠይቃሉ።
አያይዘዉም ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ለዓለም ዓቀፍ ፓለቲካ ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ከገለፁ በኋላ የአፍሪካ ህብረት ይህን ስልጣን አዲስ አባላት እንዲጋሩ ያቀረበዉን ጥያቄ ሊገፋበት ይገባል ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ ኮፊ አናን ባለፈዉ ወር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ይህን እናደርጋለን ብሎ ማለት ከሃሳብ እንደማይዘል ግልፅ አድርገዋል።
ምክንያቱንም ሲያብራሩ በርካታ አባልት ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ያላቸዉ አገራት ቁጥር እንዲበረክት ይሻሉ ግን የሚቻል አይደለም።
ለምን ቢባል እነዛ ይህን ስልጣን የተቆጣጠሩት አገራት ሌላ ተጨማሪ እንዲመጣባቸዉ ስለማይፈልጉ ሲሉ ነገሩን ግልፅ አድርገዉታል።
የሚሻለዉ በፀጥታዉ ምክር ቤት ዉስጥ የሌሎች አህጉራትን ድምፅ ማሰማት የሚችሉ ጠንካራ ተወካዮችን በማስገባት የበለጠ ዲሞክራሲያዊ አሰራር እንዲኖር ማድረግ ነዉ ይላሉ አናን።
የዓለም ፌደራሊስት ንቅናቄ ዋና ፀሃፊ የሆኑት ቢል ፔስ ደግሞ የፀጥታ ምክር ቤቱን ማስፋት ህጋዊነቱንና ዉክልናዉን ለማመቻቸት ቢጠቅምም የእኔ ድርጅት አይደግፈዉም ባይ ናቸዉ።
እንደእሳቸዉ ድርጅት እምነት እንኳን አዲስ ሊጨመር ከዚህ በፊት የነበረዉ ቋሚ አባልነት ያመጣዉ ቢኖር መምታታትና ይህ ነዉ የሚባል ችሎታ ማጣትን ነዉ።
ዓለም ዲሞክራቲክ እየሆነች በሄደች ቁጥርም ይህ ጊዜ ያለፈበት ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ራሱ መሻር አለበት።