1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ ህብረት ኃይል ተልዕኮ በዳርፉር

ረቡዕ፣ ሰኔ 21 1998

በጦርነት በተዳከመችዉ የሱዳን ምዕራባዊ ግዛት ዳርፉር ሰላም ለማስከበር የተሰማራዉ የአፍሪካ ህብረት ኃይል በገጠመ የበጀት እጥረት ሳቢያ ተግባሩን ሊያቋርጥ እንደሚችል ተዘገበ።

https://p.dw.com/p/E0iV
የህብረቱ ወታደር ከስፍራዉ
የህብረቱ ወታደር ከስፍራዉምስል AP

በተዳከመ ሁኔታ እንደተደራጀ የሚነገርለት በዳርፉር የሚገኘዉ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይል የገንዘብ አቅም ስላጠረ በመስከረም ወር መጨረሻ ተልዕኮዉ ሊያበቃ እንደሚችል ነዉ የአፍሪካ ህብረት የፀጥታ ዘርፍ በይፋ ያሳወቀዉ።

የአህጉሪቱ መሪዎች ጉባኤ ከመካሄዱ አንድ ሳምንት አስቀድሞ የደቡብ አፍሪካ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ናኮሳዛና ዳህሊሚኒ ዙማ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤን በሊቀመንበርነት ሲመሩ «ምንም ነገር ቢሆን አዲስ ነገር ካልመጣ በቀር በስፍራዉ የመቆየት ስልጣንና ሃላፊነታችን በመስከረም 21ቀን 1999ዓ.ም ላይ ያበቃል። ለመቀጠል ብንፈልግም እንኳ ከዚያች ቀን በላይ የሚያላዉሰን ገንዘብ የለንም። ምናልባት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚሰጠንን ድጋፍ አራዝሞ ካልጨመረልን» ነዉ ያሉት።

ሱዳን በተደጋጋሚ በዳርፉር የሰላም ማስከበሩን ተግባር የአፍሪካ ህብረት ለዓለም ዓቀፍ ኃይል አሳልፎ ይስጥ የሚለዉን ሃሳብ ስትቃወም ቆይታለች።

ዘግየት ብላ ከዋነኛዉ የአማፂ ቡድን ጋር የሰላም ዉል ከተፈራረመች በኋላ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ፈቃደኛነት አሳይታም ነበር።

ያም ሆኖ ፕሬዝደንት ዖማር አልበሺር ባለፈዉ እሁድ በዳርፉር ያለዉን ሁኔታ ለማረጋጋት የአፍሪካ ህብረት ከስፍራዉ ሲለቅ የሱዳን ወታደሮች ሃላፊነቱን ለመቀበል ዝግጁ ነዉ ብለዉ አዲስ ዉዝግብ ቀስቅሰዋል።

እንደዉም ደጋግመዉ የምዕራባዉያን ወታደሮች የዳርፉርን መሬት ቢረግጡ አካባቢዉ የመቃብር ስፍራ ይሆናል በማለት ምዕራቡ ሱዳንን መልሶ ቅኝ ለመግዛት ፈልጓል ሲሉ ከሰዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ኮፊ አናን ደግሞ የአልበሽርን ተቃዉሞና ክስ ወደጎን በመተዉ ዳርፉር የመንግስታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ያስፈልጋታል ነዉ ያሉት።

የተባበሩት መንግስታት የገንዘብም ሆነ የትጥቅ ችግር ያለበት የአፍሪካ ህብረት 7,000 የሰላም አስከባሪ ኃይል የታለመዉን ሰላምም ሆነ መረጋጋት በዳርፉር ላለፉት ሁለት ዓመታት ማስፈን አልቻለም ባይ ነዉ።

በመንግስታቱ ድርጅት ግምገማ መሰረትም የተጠናከረዉ የሰላም አስከባሪ ኃይሉን ወደስፍራዉ ማንቀሳቀሱ በዳርፉር በተጎሳቆለ ሁኔታ ለሚገኙት ወገኖች ደህንነት ወሳኝ ነዉ።

በስፍራዉ ከሚገኙት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እነዚህ ወገኖች የሚገኙበትን ሁኔታ ይገልፃሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህፃናት መርጃ ድርጅት ማለትም UNICIF
«የዳርፉር አጠቃላይ ግዛት የተረጋጋ አይደለም። በዚያም ላይ ረዳት የሌለዉ የአካባቢዉ ሰላማዊ ህዝብ ከሚገባዉ በላይ በተስፋ መቁረጥ የተጎዳ ሆኗል። በሰላም ለመንቀሳቀስ እርግጠኛ መሆን አይችልም። እኔ እስከማየዉ ድረስ የዚህን 3ሚሉዮን ህዝብ ነፍስ ቀጥ አድርጎ ያቆየዉ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ማለትም እንደUNICIF እና ሌሎች ድርጅቶች የሚሰጡት የመሰረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦት ነዉ። ግልፅ ማድረግ የምንፈልገዉ ከሚያሰጋዉ የደህንነት ሁኔታ ባሻገር ሰዎጭ ዉሃና ምግብ ለማግኘት ይሰቃያሉ የሚለዉን ነዉ።»

ሂዉማን ራይትስ ዎች ከትናንት በስተያ ለዓለም ዓቀፉ ለጋሽ ህብረተሰብ የአፍሪካ ህብረት የዳርፊር ተልዕኮ እንዲጠናከር የሚረዳ ወታደራዊም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

የድርጅቱ ዳይሬክተር ፔተር ታኪራምቡድ የአፍሪካ መሪዎች የካርቱም መንግስት የመንግስታቱን ድርጅት ኃይል እንዲቀበል የበኩላቸዉን እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

ጨምረዉም ቡሩንዲና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የነበረዉ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ተግባሩን ለመንግስታቱ ድርጅት ያስተላለፈበት ሁኔታ እንደነበር አስታዉሰዉ ሱዳን በምን ትለያለች ሲሉም ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ሀገራት መንግስታት መሪዎች ጉባኤ በሚቀጥለዉ ሳምንት እንደሚካሄድ ይጠበቃል። የዳርፉርን ሁኔታ አስመልክቶ የሚወስደዉ አቋም ካለም ያኔ የሚታይ ይሆናል።