1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ ኅብረት ሽምግልና ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይቀጥላል

ቅዳሜ፣ ሰኔ 20 2012

ለሶስቱ አገሮች ልዩነቶች መፍትሔ ለማፈላለግ የተቋቋመው ኮሚቴ በአንድ ሳምንት የደረሰበትን ለፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እንደሚያቀርብ የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል። የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ አባላት፣ የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መሪዎች በድርድሩ ውጤት ላይ ለመምከር ከሁለት ሳምንት በኋላ ሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደገና ይገናኛሉ

https://p.dw.com/p/3eRWl
BG Grand Renaissance Dam |  Treffen zwischen Äthiopiens Premierminister Abiy Ahmed Ali und Südafrikas Präsident Cyril Ramaphosa
ምስል AFP/P. Magakoe

በደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሰብሳቢነት በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የተጀመረው ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳንን የማሸማገል ጥረት ከሁለት ሳምንታት በኋላ እንደሚቀጥል የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ። ጉባኤው መግለጫ ከማውጣት እና በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ ላሏቸው ልዩነቶች መፍትሔ ለማግኘት በአፍሪካ ኅብረት የተጀመረውን ሒደት የሚያደናቅፍ ወይም የሚያወሳስብ እርምጃ ከመውሰድ ለመቆጠብ ሶስቱ አገሮች ተስማምተዋል ብሏል። 

የአፍሪካ ኅብረት ይፋ ባደረገው መግለጫ በሶስትዮሽ ድርድሩ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በ90 በመቶ ልዩነቶቻቸው መስማማት ላይ ስለመድረሳቸው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ሪፖርት ማቅረባቸው ተገልጿል።

መግለጫው እንደሚለው አርብ ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሔደው የቪዲዮ ኮንፍረንስ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታኅ አል ሲሲ፣ የሱዳኑ ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የየአገሮቻቸውን አቋም አስረድተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ ውይይቱ «አዎንታዊ እና ገንቢ» ነበር ቢልም ማሳሰቢያ ከመስጠት አልተቆጠበም። ሶስቱ አገሮች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች እና ለአፍሪካ ኅብረት መመሥረት ላቅ ያለ ሚና የነበራቸው መሆኑን አስታውሶ ለቴክኒካዊ እና ሕጋዊ ልዩነቶቻቸው «በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት የሚኖረው የወዳጅነት» መፍትሔ ለማግኘት በብርታት እንዲጥሩ ጠይቋል።

ሶስቱ አገሮች «ምንም አይነት መግለጫ ከመስጠት እና ለሁሉም ልዩነቶቻቸው ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ለማግኘት በአፍሪካ ኅብረት የተጀመረውን ሒደት የሚያደናቅፍ ወይም የሚያወሳስብ እርምጃ ከመውሰድ ለመቆጠብ መስማማታቸውን የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ በይሁንታ ይቀበላል» ብሏል።

መግለጫው ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች በዕለተ አርቡ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ከስምምነት ተደርሶባቸዋል ብለው ስለጠቀሷቸው ጉዳዮች ምንም ማብራሪያ አልሰጠም።

የሱዳኑ ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ አርብ ማምሻውን "የግድቡ የውኃ ሙሌት ስምምነት እስኪፈጸም እንዲዘገይ ከስምምነት ተደርሷል" የሚል መግለጫ አውጥተዋል። የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከመሩት የቪዲዮ ኮንፍረንስ በኋላ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታኅ አል ሲሲ ጽህፈት ቤት በወገኑ «ሁሉም ወገኖች ስምምነት ሳይደረስ ግድቡን ውኃ መሙላትን ጨምሮ ምንም አይነት የተናጠል እርምጃ ላለመውሰድ ወስነዋል» የሚል መግለጫ አውጥቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ቅዳሜ ማለዳ ያወጣው መግለጫ ግን የተለየ ነው።

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት የታላቁ የኅዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለመጀመር በያዘችው ውጥን ኢትዮጵያ እንደጸናች መሆኑን አስታወቋል። ቀሪ የግንባታ ሥራዎች በሚከናወኑባቸው መጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ለልዩነቶቻቸው መፍትሔ ለመፈለግ እንደተስማሙ የጠቅላይ ምኒስትሩ ጽህፈት ቤት መግለጫ ይጠቁማል።

"ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ የግንባታ ሥራዎች በማጠናቀቅ ሙሌት ትጀምራለች። በእነዚህ ሁለት ሳምንታትም ሀገራቱ ከስምምነት ለመድረስ ወስነዋል" ብሏል።

የአፍሪካ ኅብረት ሶስቱን አገሮች ለማሸማገል የሚኖረው ጊዜ ሁለት ሳምንታት ብቻ ነው። የሶስቱ አገሮች ተወካዮች፣ ደቡብ አፍሪካ እና የአፍሪካ ኅብረት ባለሙያዎች የተካተቱበት ኮሚቴ ለልዩነቶቹ መፍትሔ ለመፈለግ በጥምረት እንደሚሰሩ የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል። ይኸው ኮሚቴ በአንድ ሳምንት ውስጥ የደረሰበትን ለአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ያቀርባል። የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ አባላት፣ የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መሪዎች በድርድሩ ውጤት ላይ ለመምከር ከሁለት ሳምንት በኋላ በመጪው ሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደገና ይገናኛሉ።    

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቴሽኬዲ፣ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታኅ አል ሲሲ፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ፣ የማሊው ፕሬዝዳንት ኢብራሒም ቦባካር ኪየታ ባለፈው አርብ በተካሔደው የቪዲዮ ኮንፈረንስ የተሳተፉ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ አባላት ናቸው።

 

እሸቴ በቀለ