1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ተግባራዊነት እና ቀሪ ጉዳዮች

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 14 2013

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ሥምምነቱን ባጸደቁ 34 አገሮች ገቢራዊ ይሆናል። ተግባራዊነቱ በኮሮና ወረርሽኝ እና በድርድሮች መጓተት ምክንያት ዘግይቷል። አሁንም ቀረጥ እና ሸቀጦች የተመረቱበትን አገር ለይቶ ለግብይት የሚፈቅድ ሥርዓት ማበጀትን ጨምሮ በርካታ ውስብስብ ድርድሮች የሚሹ ጉዳዮች አሉ

https://p.dw.com/p/3nA7m
Äthiopien Addis Ababa - Neuer Zug verbindet Hafen und Stadtzentrum
ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና

አፍሪካውያን ትልቅ ተስፋ የጣሉበት አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. ከሳምንት በኋላ አንድ ተብሎ ሲጀመር ተግባራዊ ይሆናል። የንግድ ቀጣና የሚመሠርተውን ሥምምነት ከኤርትራ በቀር 54 የአፍሪካ አገሮች ፈርመዋል። በየአገሮቻቸው ሕግ አውጪ ተቋማት ያጸደቁት ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ 34 አገሮች ብቻ ናቸው። የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና በተግባር ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ሥራ የሚጀምረው በእነዚህ 34 አገሮች ብቻ ነው።   

ሥምምነቱ ከወራት በፊት ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የነበረ ቢሆንም አንድም በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ አንድም በድርድሮቹ ዘገምተኝነት ተጓቷል። የሥምምነት ሰነዱን ካረቀቁ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት በዩናይትድ ኪንግደም የሌስተር ደ ሞንትፎርት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ኤኮኖሚና የሕግ ፕሮፌሰሩ መላኩ ደስታ "ማጽደቁ አንድ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ሆኖ ከዚያ አልፎ እንደገና ቀረጦችን በተመለከተ ሁሉን በሚያስማማ ደረጃ እያንዳንዱ አገር አዘጋጅቶ ማቅረብ ይጠበቅበታል። እስካሁን ድረስ 34ቱም አላቀረቡም። ከእነሱ ውስጥ በጣም ጥቂቶች ናቸው ያቀረቡት" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በጸጥታ ጥናት ተቋም የአፍሪካ ፊውቸርስ እና ኢኖቬሽንስ ፕሮጀክት ኃላፊ ያኪ ሲሊየ ግን አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ ታሪፎችን እና ሌሎች የንግድ እንቅፋቶችን ማስወገድ እንዲህ በቀላሉ የሚከወን እንዳልሆነ ያስጠነቅቃሉ።

44 afrikanische Staaten unterschreiben Freihandelsabkommen in Kigali
የአኅጉሪቱ መሪዎች የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሥምምነትን የፈረሙት መጋቢት 2010 ዓ.ም በርዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ነበርምስል Reuters/J. Bizimana

"አሁንም በተለያዩ አገሮች መካከል ስምምነት የሚሹ በርካታ የታሪፍ መስፈርቶች አሉ" የሚሉት ያኪ ሲሊየ በጎርጎሮሳዊው 2034 ዓ.ም. እስከ 97 በመቶ ገደማ የታሪፍ ሥርዓቶች የማስወገድ ሐሳብ እንዳለ አስረድተዋል። እንደ ያኪ ሲሊየ ከሆነ በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ50 በላይ የአፍሪካ አገራት ገበያዎችን ማጣጣም ፈታኝ ነው። ለዚህ ሥምምነቱን መፈረም እና በየሕግ አውጪዎቻቸው ማጽደቅ ብቻ ለአፍሪካ አገራት በቂ አይደለም።

ያኪ ሲሊየ "አገሮች ሥምምነቱን ማጽደቅ አለባቸው። ነገር ግን ገና በርካታ ድርድሮች መካሔድ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያክል የንግድ መረጃዎችን የሚያሰባስበው እና ዋና መሥሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ የሚያደርገው የአፍሪካ የንግድ ታዛቢ መቋቋም ይኖርበታል። የንግድ ድርድሮች ደግሞ እጅግ ውስብስብ ናቸው። እያንዳንዱ ታሪፍ ድርድር ተደርጎበት ሥምምነት ሊፈጸም ይገባል" ሲሉ ከፕሮፌሰር መላኩ የተስማማ አስተያየት ይሰጣሉ።

ሸቀጦች የተመረቱበትን አገር በማረጋገጥ በነፃ የንግድ ቀጠናው ለግብይት የሚቀርቡበትን ሥልት የሚደነግገው ሥርዓት (Rules of origin) በድርድር ከሥምምነት ያልተደረሰበት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ፕሮፌሰር መላኩ ይኸ "ያልተጠናቀቀ አንድ ትልቅ ጉዳይ" እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ፕሮፌሰር መላኩ "አንድ ዕቃ የተሠራበትን መወሰን የሚቻለው እንዴት ነው? ለሚለው የሚወጣ ሕግ አለ። አፍሪካ እሱ ላይ ገና ድርድር ላይ ነው ያለችው። 34 የአፍሪካ አገሮች ሥምምነቱን አጽድቀዋል ስንል ምን ማለታችን ነው? ከእነዚህ ከ34 አገሮች የመጡ ዕቃዎች ከሌላ አገር ከመጡ ዕቃዎች በተሻለ ሁኔታ ይስተናገዳሉ ማለታችን ነው። ግን ከሌላ አገር ከመጡት ዕቃዎች በተለየ እንዲስተናገዱ ከተፈለገ ከእነዚህ ከ34 አገሮች ለመምጣታቸው ማረጋገጫ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ክፍለ-አኅጉራዊ የኤኮኖሚ ቀጠናዎች እና ዓለም አቀፍ የንግድ ሥምምነቶች

ሌላው ፈተና የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናን የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ከመሳሰሉ ክፍለ-አኅጉራዊ ተቋማት የማጣጣሙ ነገር ነው። ክፍለ-አኅጉራዊ ተቋማት "እያንዳንዳቸው የራሳቸው የነጻ ንግድ ገበያ እና የየራሳቸው የጉምሩክ ሕብረት ኖሯቸው" ወደ አፍሪካ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ እንዲያድጉ የተያዘው ዕቅድ አለመሳካቱን የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር መላኩ አሁን ግን የአኅጉሪቱ አገራት በቀጥታ አባል የሚሆኑበት የአፍሪካ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ የመፍጠር መንገድ መመረጡን ያስረዳሉ።

ክፍለ አኅጉራዊዎቹ ተቋማት "በተቀናጀ መንገድ ወደ አንድ አቅጣጫ ሔደው የአፍሪካን የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ መፍጠር ስላልቻሉ እነዚህን አልፎ በቀጥታ አገሮች አባል የሚሆኑበት የአፍሪካ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ነው እየተንቀሳቀስን ያለንው" የሚሉት ፕሮፌሰር መላኩ እነ የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ገሸሽ እንደማይደረጉ ገልጸዋል።

Äthiopien |Äthiopischer Händler auf einem traditionellen Markt in Debre Markos
እንደ ያኪ ሲሊየ ከሆነ በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ50 በላይ የአፍሪካ አገራት ገበያዎችን ማጣጣም ፈታኝ ነውምስል DW/E. Bekele

"እነዚህ ቀጠናዊ ማሕበረሰቦች ቦታ የላቸውም ማለት አይደለም።  የተወሰነ ጊዜ ቦታ ይዘው ይቀጥላሉ። በሒደት ግን ንግድን በተመለከተ በአፍሪካ የንግድ ቀጠና መዋጥ ይኖርባቸዋል። ይኸ በአሁኑ ሰዓት ስሱ ጉዳይ ነው። በጣም ከባድ የሆነ ፖለቲከኞቹ ሊናገሩ የማይፈልጉት አይነት ነገር ነው ያለው። ምክንያቱም ብዙዎቹ እነዚህ ማሕበረሰቦች እንዲፈርሱ አይፈልጉም። የንግድ ጉዳይን ሁሉ ይዘው እንዲቀጥሉ ይፈልጋሉ። በቀጣናዊ የኤኮኖሚ ማሕበረሰቦች እና በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና መካከል ያለው ግንኙነት ገና ብዙ ፈተና የሚጋርጥ፤ እስካሁን ድረስ መፍትሔ፤ ግልፅ የሆነ አቅጣጫ ያልተሰጠው ሁኔታ ላይ ነው ያለው" ብለዋል።

የአፍሪካ አገሮች ወጥ የገበያ ሥርዓት የሚፈጥረው ሥምምነት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ከአውሮፓ፣ ቻይና እና አሜሪካ በተናጠል የተፈራረሟቸው የንግድ ሥምምነቶች እና ወደፊት የሚያበጇቸው ተመሳሳይ ግንኙነቶች ምን መልክ እንደሚኖራቸው መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ ባሻገር ከታሪፍ የማይገናኙ ጉዳዮች እና ፖለቲካዊ እንቅፋቶችም ፈተና መጋረጣቸው አይቀርም። "የባለሥልጣናት ሙስና በድንበር አካባቢዎች ሕጋዊ ሰነድ የማግኘት ሒደትን ሊያዘገይ ይችላል" የሚሉት ያኪ ሲሊየ  የአቅም ማነስ እና የክህሎት ጉዳይ ፈተና መሆናቸው እንደማይቀር ያስረዳሉ። "አንዴ የታሪፍ ክፍያ ሥርዓት ወጥ ከሆነ በኋላ ሙስና የመፈጸም ዕድሉ ይቀንሳል። ነገር ግን የአቅም ማጣት እና የክህሎት ጉድለት የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናን የወደፊት ተግባራዊነት እና ስኬታማነት የሚገዳደሩ ፈተናዎች ሆነው ይቀጥላሉ" ብለዋል።  

"አፍሪካ በቅኝ ግዛት የንግድ ሞዴል ተጠምዳለች" የሚሉት የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ሥምምነቱን "በእልህ" ገቢራዊ ማድረግ ይገባታል የሚል አቋም አላቸው። አፍሪካ ከዓለም ምጣኔ ሐብት ያላት ድርሻ 3 በመቶ ብቻ መሆኑን የሚያስታውሱት ያኪ ሲሊየ በዚያ ላይ ወደ 55 ኤኮኖሚዎች መበጣጠሱ ለፈጣን አኅጉራዊ የኤኮኖሚ ዕድገት ግዙፍ ፈተና ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል። ያኪ ሲሊየ እንዳሉት "ጥሩ ግንኙነት የሌላቸው፤ አንዱ በሌላው ላይ ድንበሮቻቸውን የዘጉ አገሮች ከአንዳች ውሳኔ መድረስ አለባቸው።"

COVID-19 I Stau im Grenzgebiet Kenia und Uganda
"አፍሪካ በቅኝ ግዛት የንግድ ሞዴል ተጠምዳለች" የሚሉት የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ሥምምነቱን "በእልህ" ገቢራዊ ማድረግ ይገባታል የሚል አቋም አላቸው። ምስል Getty Images/AFP/B. Ongoro

ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና እንዲህ ውስብስብ ድርድሮች የሚሹ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩትም ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ተግባራዊ በመሆኑ የተቆረጠ ይመስላል። "ወደ ተግባር በምንገባበት ጊዜ ብዙ እንቅፋቶች ይኖራሉ" የሚሉት ፕሮፌሰር መላኩ የአፍሪካን ውስብስብ ችግሮች እየነቀሱ ለመሔድ ኹነኛው መፍትሔ እንደሆነ እምነታቸው ነው።

"በጣም ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሥምምነት ነው። በትክክል ከሰራ ሊፈጥር የሚችለው ገበያ፤ ሊኖረው የሚችለው አንድምታ ከኤኮኖሚም ያለፈ ነው። ፖለቲካዊም አንድምታ ይኖረዋል" የሚሉት ፕሮፌሰር መላኩ ጦርነት እና ግጭትን የማስወገድ ሚና ሊኖረው ይችላል ብለው ተስፋ አድርገዋል።  

"በሚፈጠረው አዲስ የሥራ ዕድል ብቻ፤ ከድሕነት በሚወጡ ሰዎች ብቻ፤ በሚጨምረው አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን (GDP) ብቻ የሚወሰን ነገር አይደለም። በኤኮኖሚ ይበልጥ እየተሳሰርን በሔድን ቁጥር እንደ አፍሪካ አንድ የመሆናችን፤ በአንድ ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ቆመን ለመብታችን የመሟገት ጥንካሬያችን ለሁሉም የአፍሪካ አገሮች በሚጠቅም መንገድ ሥራ ላይ ለማዋል ይረዳል የሚል ተስፋ ነው የፈጠረው" ብለዋል።

ይኸ የንግድ ቀጠና አብዛኞቹን ታሪፎች በማስቀረት የአፍሪካውያንን የርስ በርስ ንግድ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2034 ዓ.ም. 60 በመቶ በማሳደግ የ3.4 ትሪሊዮን ዶላር ገበያ የመፍጠር ውጥን ነው። ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ከሆነ በዓለም ባንክ ስሌት መሠረት 30 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ከከፋ ድሕነት፤ 70 ሚሊዮን የአኅጉሪቱን ዜጎች ደግሞ ከመካከለኛ ድሕነት መንጭቆ ያወጣል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ