1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍቃኒስታን ዉጊያና የኔቶ ሥልት

ሐሙስ፣ መስከረም 28 2002

የሕብረ-ብሔሩ ጦር ብዛትና የዉጊያ ሥልት፥ የተሻራኪ ሐገራት ባለሥልጣናትን ሲያከራክር የአፍቃኒስታን ደፈጣ ተዋጊዎችና የአሸባሪዎች ጥቃት እየተደጋጋመ ነዉ

https://p.dw.com/p/K27G
ራስሙስን ከኦባማ ጋርምስል AP

08 10 09

የአፍቃኒስታኑን ጦርነት በድል ለመወጣት አዲስ ሥልት ይቀየስ የሚለዉ ሐሳብ የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ሐገራትን እያከራከረ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ወደ አፍቃኒስታን ተጨማሪ ጦር እንዲያዘምቱ ተቃዋሚዎቻቸዉ ሲጠይቁ ፕሬዝዳንቱ አጠቃላዩን የዉጊያ ሥልት እያጤኑት መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።ተጨማሪ ጦር ይዝመት የሚለዉን ሐሳብ የአዉሮጳ ሐገራትም የሚደግፉት መስለዋል።በክርክር ዉይይቱ መሐል የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ድርጅት (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ ጉዳዩ ገና እልባት አለማግኘቱን ገልፀዋል።ሚሻኤል ገትሸንበርግ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮቷል።

የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ፀሐፊ አንደረስ ፍግሕ ራስሙሰን እንደሚሉት እስካሁን ድረስ በርግጥ የተወሰነ ነገር የለም።የድርጅታቸዉም የእሳቸዉም አቋም ተጨማሪ ጦር ይላክ ወደሚለዉ ማዘንበሉን ግን ዋና ፀሐፊዉ አልካዱም።
«ወደ ፊት ብዙ እንዳንለፋ አሁን አበክረን መስራት አለብን»
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣዉን የደፈጣ ተዋጊዎችና የአሸባሪዎች ጥቃት ለመግታት የአለም አቀፉ ጦር ቁጥር እንዲጨምር፥ የዘመቻ፥ ሥልቱም እንዲጠናከር ሲጠየቅ ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም።የዚያኑ ያክል በተለይ አዉሮጳ ዉስጥ የአፍቃኒስታኑ ዘመቻ የሚያበቃባት ጊዜ እንዲቆጠረጥ የሚደረገዉ ግፊትና ጥሪ እየደመቀም ነዉ።

ከትላንቲክ ባሕር ማዶ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ለአፍቃኒስታኑ ዉጊያ ሁነኛ ሥልት ይቀየስ የሚለዉ ክርክር እየተጋጋመ ነዉ።የክርክር-ዉይይቱ ግመት ተጨማሪ-ጦር ይዝመት ወይስ ካለዉ ተቀንሶ ዘመቻዉ በተመረጡ የሽብር ተቋማት ላይ ያነጣጥር የሚል ጥያቄ አጭሯል።ዋና ፀሐፊ ራስሙስን ለአሻሚዉ ጥያቄ የማያሻማ መልስ አላቸዉ።
«አፍቃኒስታን የሠፈሩት ወታደሮች ቁጥር ይቀንስ-የሚለዉ ሐሳብ በርግጠኝነት የመነጋገሪያ ርዕሠ- ጉዳይ አካል አይደለም።»

ይሁንና የጦር ሐይሉ ቁጥር ይቀነስ-የሚለዉ ሐሳብ ከሎች አልፎ የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝዳት ጆ ባይደን የሚጋሩት አይነት ነዉ።ባይደን እንደሚያምኑት ጦሩን በመላዉ አፍቃኒስታን የመሸጉትን ታሊባን እና ሌሎች ሐይላትን እንዲወጋ ከመለጠጥ ይልቅ በአል-ቃኢዳ ምሽግች ላይ እንዲያነጣጥር ማድረጉ ዉጤታማ ነዉ።

በተለይ ደግሞ አሁን እንደተያዘዉ ዘመቻዉ አፍቃኒስታንና ፓኪስታን አዋሳኝ ድንበር ላይ ማነጣጠር አለበት ባይ ናቸዉ።-ምክትል ፕሬዝዳንቱ።አፍቃኒስታን የሰፈረዉ የኔቶ ጦር አዛዥ አሜሪካዊዉ ጄኔራል ስታንሌይ ማክ ክርይስታል ግን የምክትል ፕሬዝዳንታቸዉን ሐሳብ አይቀበሉትም።ጄራሉ በታሊባን ላይ የተከፈተዉ ዘመቻ በድል-እንዲጠናቀቅ ነዉ-የሚሹት። ለዚሕ ደግሞ ተጨማሪ ጦር መዝመት አለበት።

የኔቶ ዋና ፀሐፊ ራስሙሰን የጄኔራል ማክክርይስታልን አቋም እንደሚጋሩ አልሸሸጉም።ግን ደግሞ አሜሪካኖች የተሸከሙትን ጫና ሌሎቹ የጦር ተሻራኪዎቻቸዉ ሊጋሯቸዉ ይገባል-እንደ ራስሙስን።
«ዩናይትድ ስቴትስ በምታደርገዉና ሌሎቹ ተሻራኪዎች ለዚሕ ጥረት ስኬት በሚያበረክቱት አስተዋፅኦ መካከል ሚዛኑን የጠበቀ መመጣጠን እንዲኖር የሚደረገዉ ሙከራ መቀጠል አለበት።»

የኔቶ ተሻካሪዎች ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ አፍቃኒስታን እንዲያዘምቱ የዩናይትድ ስቴትሱ መከላከያ ሚንስትር ሮበርት ጌትስ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።ጌትንስን የመሳሰሉት የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት የአዉሮጳ ተሻራኪዎቻቸዉ በቂ መልስ አልሰጡም ብለዉ ያምናሉ።

የሕብረ-ብሔሩ ጦር ብዛትና የዉጊያ ሥልት፥ የተሻራኪ ሐገራት ባለሥልጣናትን ሲያከራክር የአፍቃኒስታን ደፈጣ ተዋጊዎችና የአሸባሪዎች ጥቃት እየተደጋጋመ ነዉ።ዛሬ ርዕሠ-ከተማ ካቡል ዉስጥ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳዉ የመኪና ላይ ቦምብ በትንሹ አስራ-ሁለት ሰዉ ገድሎ-ሌሎች በርካታ አቁስሏል።

Michael Götschenberg

ነጋሽ መሐመድ፣

ተክሌ የኋላ፣