1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍጋኒስታኑ የስላም ጅርጋ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 3 1999

በአፍጋኒስታን በባህላዊ ዘዴ የግጭት ማስወጋጃነቱ የሚታወቀዉ የሰላም ጅርጋ ማለትም ጉባኤ ተጀመረ።

https://p.dw.com/p/E87p
የአሜሪካ ወታደሮች በአፍጋኒስታን
የአሜሪካ ወታደሮች በአፍጋኒስታንምስል AP

በዚህም ከፓኪስታንና አፍጋኒስታን የተዉጣጡ ወገኖች ተሰባስበዉ በአዋሳኝ ድንበራቸዉ ላይ ይዘቱን አጠናክሮ ስለሚገኘዉ የታሊባን ኃይል ይነጋገራሉ። ለወትሮዉ ካለዉ የመኪና ጭንቅንቅ ባሻገር በጉባኤዉ ምክንያት በመዲናይቱ ካቡል የፀጥታዉ ይዘት ጠብቋል። አፍጋኒስታኖችንና ፓኪስታኖችን በተለየ መልኩ ያሰባሰበዉ የሰላም ጉባኤ ይዘቱ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነዉ። የፓኪስታኑ ፕሬዝደንት ፔርቬዝ ሙሻረፍ ባለቀ ሰዓት እንደማይሳተፉ በመናገራቸዉም በጠቅላይ ሚኒስትር ሻዉካት አዚዝ ተወክለዋል። ለሶስት ቀናት በሚዘልቀዉ በአገሬዉ አጠራር ጅርጋ በተሰኘዉ የሰላም ጉባኤ አዚዝን ጨምሮ ከፓኪስታን 175የመንግስትና የጎሳ ተጠሪዎች ናቸዉ የሚሳተፉት። በጉባኤዉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት ፕሬዝደንት ሃሚድ ካርዛይ 700 ተወካዮች የተገኙበት ጅርጋ ለፓኪስታንና ለአፍጋኒስታን የወደፊት የሰላም ህይወት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ያላቸዉን ተስፋ ገልፀዋል። የጉባኤዉ ትኩረት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለዉን ድንበር ነዉ። ስፍራዉ የሁለቱም ወገን ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ የሚቆጣጠሩት ባለመሆኑ ለፅንፈኛ ሙስሊም ታጣቂዎቹ የምድር ገነት ሆኖላቸዋል እየተባለ ነዉ። ዉስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት አልቃ-ኢዳና ታሊባን በአዋሳኙ ምድር ላይ የዕዝ ማዕከል አላቸዉ። ከዚያም አፍጋኒስታን ዉስጥ የት ቦታ ጥቃት እንደሚጣል ይነድፋሉ፤ ጥቃቱን ያደርሳሉ። ባለፈዉ ሰኔ ወር በፓኪስታን ኢዝላማባድ በቀዩ መስጊድ ተፈጥሮ በነበረዉ ቀዉስም የፅንፈኞቹ ችግርነት ለፓኪስታንም እንደማይቀር በመታየቱ ለሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ስጋት መሆኑንም አፍጋኒስታናዊዉ የደህነት ጉዳይ አዋቂ ሃሩን ሚር ያስረዳሉ፤
«አፍጋኒስታንና ፓኪስታንን የሚያሳስባቸዉ የደህንነትና የሽብርተኝነት ችግር አለ፤ ለአፍጋኒስታንም ሆነ ፓኪስታን የጋራ ስጋት ነዉ።»
የጎሳ መሪዎች፣ የምክር ቤት አባላት፤ የሁለቱም ሀገራት የእምነት አባቶችን ያካተተዉ የካቡሉ ጅርጋ በሚካሄድበት በዚህ ወቅት በከተማዋ የአፍጋኒስታንና የፓኪስታን ባንዲራዎች ይዉለበለባሉ። ኗሪዎቹም በተጎራባች አገራቱ መካከል የሚካሄደዉ የሰላም ዉይይት ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤
«አፍጋኒስታንና ፓኪስታን ሊነጋገሩ ይገባል፤ የሁለቱም ባንዲራ ደግሞ እንዲህ ከፍ ማለት አለበት።» ይላሉ እኝህ ሰዉ። ሌላኛዉ ደግሞ
«በዚህ በጅርጋዉ ምን እንደሚነጋገሩ እኔ የማዉቀዉ ነገር የለም። ሆኖም እያንዳንዱ አፍጋኒስታናዊና ፓኪስታናዊ እንደሚደሰት አዉቃለሁ።» ነዉ ያሉት።
በዚህ ጉባኤ ግን ፅንፈኞቹ ታሊባኖች እንዲሳተፉ ሃሳብ ያቀረበም የለም እነሱንም የሚወክል አልተገኘም። ይልቁንም ጉባኤዉን የገንዘብና የሰዓት ማባከኛ ሲሉ አጣጥለዋል። በአንጻሩ ታዛቢዎች ይህ የሰላም ጉባኤ መልካም ጅምር ነዉ ይላሉ። ካቡል ከሚገኘዉ ፍሬደሪሽ ኤበርት ሽቲፍቱንግ ዑርሳላ ኮችላዉግቪትዝ፣
«በአንድ ላይ ተቀምጠዉ ሁለቱንም ሀገራት በጋራ ችግራቸዉ ላይ ለረዥም ጊዜ በተነጋገሩ መጠን ማንም ቢሆን አዎንታዊ ነገርን ተስፋ ያደርጋል። ጦርነት በሚያስከትል ሁኔታ ዉስጥ ደግሞ በተለመደዉ መንገድ የግድ በወታደራዊ ኃይል ችግሩን ለመፍታት መሞከር የለበትም፤ በዉይይትም መሆን ይኖርበታል።»
በሰላሙ ጅርጋ የሚሳተፈዉ ጋዜጠኛ አብዱል አህመድ ሙባሬዝም ይህንን ሃሳብ ይጋራል፤
«የሰላሙ ጅርጋ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተወካዮች ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ችግሮቻቸዉ ዙሪያ ለመነጋገር አንድ ላይ እንዲቀመጡ ያደረገ አጋጣሚ ነዉ። ያንን ደግሞ እስከዛሬ ፓኪስታን ስታጣጥለዉ ቆይታ ነበር።»
እንደተሳታፊዎቹ እምነት ከሆነ ከጉባኤዉ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የተጣጣመ እርምጃ ይወስዳሉ። ምክንያቱም ድርጊቱ የአፍጋኒስታንም ሆነ የፓኪስታን መለያ አይደለምና። ታዛቢዎች ግን ለግጭት ማስወገጃ መፍትሄ ሆኖ የኖረዉ ባህላዊዉ ጅርጋ በሽብርተኝነት ተግባር ላይ ምን ለዉጥ እንደሚያስከትል ለመናገር ጊዜዉ ገናነዉ ባይ ናቸዉ።