1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍጋኒስታን ምርጫ ዝግጅት

ረቡዕ፣ መጋቢት 3 2006

የአፍጋኒስታን ምርጫ ከመካሄዱ አንድ ወር በፊት ታዛቢዎች በዚህ አጋጣሚ ለፉክክር የሚቀርቡ 11 እጩዎች ሶስቱ የሕዝቡን ቀልብ እንደያዙ ያመለክታሉ። የፕሬዝደንት ሃሚድ ኻርዛይ ወንድም ቃዩም ኻርዛይ ከፉክክሩ ራሳቸዉን አግልለዉ የቀድሞ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን ዛልማይ ራሶልን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/1BOhR
Schild der afghanischen Wahlkommission
ምስል DW

ራሶል የፕሬዝደንቱ ቀኝ እጅ ተደርገዉ ስለሚታዩ ኻርዛይ ከስልጣን ቢወርዱም ከጀርባ ተፅዕኗቸዉ እንዲቀጥል የማድረግ ስልት እየተጠቀሙ ነዉ የሚል ጥርጣሬን በዲፕሎማቶች ዘንድ አሳድሯል። በመጪዉ ምርጫ የመወዳደር ሕልማቸዉ በተደጋጋሚ የተጨናገፈባቸዉ ኻርዛይ ግን ይህን ያስተባብላሉ።

ከመነሻዉ ምናልባት የፕሬዝደንቱ ወንድም ቃዩም ኻርዛይ ከተፎካካሪዎቹ አንዱ ለመሆን አቅድዉ ይሆናል ። ሆኖም የቀድሞዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፕሬዝደንቱ የቅርብ ታማኝ ዛልማይ ራሶል በመጀመሪያዉ የምርጫ ዘመቻ ሳምንት በቂ ድምጽ ማግኘት እንደማይችሉ ስላመላከቷቸዉ ሊሆን ይችላል ከተፎካካሪነት ተርታ ገለል ማለቱን የወሰኑት፤ ይላሉ በካቡል የኮንራድ አደናዎር ተቋም ኃላፊ ኒልስ ቮርመር።

Bruder des afghanischen Präsidenten Qayum Karsai
የኻርዛይ ወንድም ቃዩም ኻርዛይምስል picture-alliance/ZUMA Press

«የመጀመሪያዉ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ቃዩም ኻርዛይ በቂ ድምፅ ማግኘት እንደማይችሉ ያሳያቸዉ ይመስለኛል። በመጀመሪያዉ ወር የምርጫ ዘመቻ ቃዩም ሳይደሰቱ ነዉ የተጠናቀቀዉ።»

ተንታኞች ከራሱል ቀጥሎ አብዱላ አብዱላ እና አሽራፍ ጋህኒ በሕዝቡ የሚመረጡ እጮዎች መሆናቸዉን እናገራሉ። በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉትና የተቃዋሚዎች ጥምረት መሪ አብዱላህ አብዱላህ፤ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2009ዓ,ም በተካሄደዉ ምርጫ በሁለተኛ ደረጃ የሕዝብ ድምፅ ያገኙ ተፎካካሪ ናቸዉ። ያኔ ኻርዛይ ማሸነፋቸዉ ሲገለፅ ምርጫዉን አጭበርብረዋል በማለት ከሰማቸዋል። ደጋፊዎቻቸዉ በሚያዛያዉ ምርጫ እዉነት ይለይልናል ማለት ጀምረዋል። እንዲያም ሆኖ የአፍጋኒስታን ተንታኞች ትብብር አባል ቶማስ ሩቲግ የአብዱላ ደጋፊዎች ስብጥር ስለሚጎድለዉ ይህ እንደአንድ ደካማ ጎን ይሆንባቸዋል ሲሉ ያስገነዝባሉ። በተቃራኒዉ የኤኮኖሚ ባለሙያዉና የቀድሞዉ የፋይናንስ ሚኒስትር አሽራፍ ጋህኒ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደጋፊዎቻቸዉን የማነቃነቅ ጽናት እንዳላቸዉም ያመለክታሉ።

«ሶስተኛዉ እጩ አሽራፍ ጋህኒ በአካባቢያቸዉና እሳቸዉ ካልተገኙበት ለምክትል ፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት እጩዎች ደጋፊዎች ካሉበት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍልሳይቀር በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠንካራ ቅስቀሳ እያካሄዱ ነዉ። በዚያ ላይ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቡድኖችን በጋራ በተቃራኒ እያካሄዱ ያሉትን ቅስቀሳም እያየን ነዉ። ጥያቄዉ ግን ምን ያህል ይህን ተቃራኒ እንቅስቃሴ ድል ማድረግ ይችላሉ የሚለዉ ነዉ።»

Grenze Tadschikistan Aghanistan
ምስል DW/G. Faskhutdinov

ኒልስ ቮርመር በበኩላቸዉ በሂዉማን ራይትስ ዎች የጦር ወንጀለኛ የተባለ ከእጩዎቹ መካከል ባለመኖሩ ለሚካሄደዉ ምርጫ አስተማማኝነት አንዱ ማመላከቻ እንደሆነ ነዉ የሚገልፁት፤

«በእርግጠኝነት ችግር ይሆን የነበረዉ በሂዉማን ራይትስ ዎች የጦር ወንጀለኛ ተብሎ የተፈረጀ ግለሰብ ፕሬዝደንት ለመሆን ቢቀርብ ነበር፤ ነገር ግን አብዱላ አብዱላ፤ ዛልማይ ራሶል እንዲሁም አሽራፍ ጋኒን ይህ አይመለከታቸዉም።»

የታሊባንን መዉደቅ ተከትሎ በዩናይትድ ስቴትስ ሃሚድ ኻርዛይ በፕሬዝደንትነት ሲሰየሙ ከዚያም ባልተጣራ ምርጫ በድጋሚ ሲመረጡ ምዕራቡ ዓለም ጣልቃ አልገባም። ታዛቢዎች የምርጫዉ ሁኔታ አዎንታዊ ነዉ ሲሉም አብዛኛዉ አፍጋናዊ ከነበረዉ ታሪክ በመነሳት እጅግም አልተዋጠለትም ነበር። ይህን ታሊባን ለፕሮፓጋንዳዉ ተጠቅሞበታል፤ የሀገሪቱ ምርጫ በምዕራቡ የተዘወረ ነዉ በሚል። በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያም ሕዝቡ ለምርጫ እንዳይወጣ ማስጠንቀቅ ጀምረዋል። የአፍጋኒታንን የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉ ታዛቢዎችም ዓለም ዓቀፍ ወታደሮች ከሃገሪቱ መዉጣት የመጀመራቸዉ ርምጃ ቁጥራቸዉን መቀነሱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለዉን አደጋ ታሳቢ ያደርጋሉ። እንዲያም ሆኖ የምርጫዉ ስኬት የሚረጋገጠዉ አደባባይ ወጥቶ ድምፁን የሕዝቡ ቀልብ ዉስጥ ገብተዋል ለተባሉት እጩዎች በመስጠት ነዉ።

ዋስላት ሃስራት ናዚም/ ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ