1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኡሁሩ ኬንያታ በአለ ሲመት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 1 2005

ዛሬ ቃለ መሃላ የፈፀሙት ፕሬዝዳንት ኬንያታና ምክትል ፕሬዝዳንት ሩቶ ከዛሬ 5 አመቱ ምርጫ በኋላ የተከተሰተውን ግጭት በማሴር በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል ።

https://p.dw.com/p/18CZk
ምስል Reuters

የአዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት የኡሁሩ ኬንያታ በአለ ሲመት ዛሬ በዋና ከተማይቱ ናይሮቢ በርካታ ኬንያውያን ና ታጋባዥ የአፍሪቃ መሪዎች እንዲሁም ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት ተከናወነ ።  በስነስርዓቱ ላይ ቁጥጥሩ ከ 10 ሺህ በላይ የተገመተ ህዝብ የተገኘ ሲሆን የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ ና  ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎችም የአበአሉ ታዳሚዎች ነበሩ ። ኡሁሩ ኬንያታ በበአለ ሲመታቸው ላያ ባሰሙት ንግግር ቻይናን ከመሳሰሉ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ካሉ ሃገራት ጋር ጥብቅ ግንኙነት መመስረት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል 
መላውን አለም በእጅጉ ሲያሳስብ የከረመው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂደት በዛሬው እለት ከፍፃሜ ደርሷል ።  « እኔ ኡሑሩ ኬንያታ፥ የተጣለብኝን ሐላፊነት በመገንዘብ፥ የኬንያ ሪፐብሊክን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል፥ የኬንያን ሕገ-መንግሥትና ሌሎች የሪፐብሊኪቱን ሕግጋትን በመሉ ለማክበር፥ ለመጠበቅና፥ ለመከላከል፥የኬንያን ሕዝብን ሉዓላዊነት፥ አንድነትና ክብሩን ለማስጠበቅና ለመከላከል ቃል እገባለሁ።ለዚሕም ፈጣሪ ይርዳኝ። የ4 ተኛው የኬንያ ፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ  ።

Kenia Uhuru Kenyatta Vereidigung
ኡሁሩ ኬንያታምስል Reuters

ናይሮቢ በሚገኘው የስፖርት ማዕከል ዛሬ በተከናወነው በአለ ሲመት ላይ የ46 አመቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሮቶም ተመሳሳይ ቃል መሃላ ፈፅመዋል ። ከ 1200 በላይ ሰዎች በተገደሉበት ከዛሬ 5 አመቱ ምርጫ በኋላ በተከተለው  ብጥብጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማድረግ የተከሰሱት ፕሬዝዳንት ኬንያታ በአሁኑ ምርጫ መሰል ቀውስ እንዳይከተል ያደረጉት ጥረት የተሳካ ይመስላል ። አሁን ህዝቡ ወዳኋላው ሳይሆን ወደፊት ሆኗል ትኩረቱ ። ከአሁን በኋላም ከኬንያታ ብዙ ይጠበቃል  ።  የጀርመኑ የፍሬድሪሽ ኤበርት ተቋም የኬንያ ተጠሪ ፔተር ኦስተርዲክሆፍ እንደሚሉት የኬንያታ ፓርቲ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ቃል የገባባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ ። ከነዚህም መካከል ድህነትን መከላከል ፣ የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ ፣ መሠረተ ልማትን ማስፋፋትና የመሳሳሉት ይገኙበታል ። እነዚህ ሁሉ ቃል የተገቡ ጉዳዮች ገቢራዊ መሆናቸው ን ኦስተር ዲክሆፍ ይጠራጠራሉ ። ሆኖም አንዳንድ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ለውጦችም  አልጠፉም ። በአዲሱ የኬንያ ህገ መንግሥት መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ 47 የአውራጃ መስተዳድሮች ተመርጠዋል ።  እንደ ኦሰተርዲክሆፍ ይህ በምስራቅ አፍሪቃዊቷ አገር የሥልጣን ሚዛንን የመለወጥ እድል ይሰጣል ።

Kenia Vereidigung neuer Präsident Uhuru Kenyatta Nairobi
ምስል picture-alliance/dpa


« በህገ መንግሥታዊው ማሻሻያ ሥልጣንን ማከፋፈል ህዝቡ ሁሌም ቅድሚያ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ነበር ። ይህ ግን የፓርላማው ሚና ና የሥልጣን ሽኩቻውን ብዙም አይቀንስም  ። ህዝቡ በየአመቱ በየአካባቢው ስለሚከናወኑ ሥራዎች አስተያየት የመመሥጠት እድል ይኖረዋል ። በአካባቢው ኢንቬስት በማድረግም ተጠቃሚ ይሆናል ።»
የእነዚህ መስተዳድሮች ጥንካሬ ግን አሁንም ማከራከሩ አልቀረም ። እነዚህ መስተዳድሮች ከሚመለከቷቸው ጉዳዮች በአንዳንዳንድ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የግጭት መንስኤ የሆኑት የመሬት ባለቤትነትና አጠቃቀም ይገኙበታል ። በነዚህ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ የመሬት ይዞታ ኮሚሽን በነዚህ ጉዳዮች ጣልቃ ሊገባም ይችላል ።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር መሐመድ ስዋዙሪ ግን ህጉ እስከተከበረ ድረስ አያሳስብም ይላሉ ።
« የምንከተለው ህግ አለን ። የምንመራበት ህገ መንግሥትም አለን ። እንደሚመስለኝ ከህግ ውጭ የሚሆን ነገር ካለ ችግር ሊከተል ይችላል ። ግን ህጉን እስከተከተሉና በህጉም እስከሰሩ ድረስ ግጭት የሚከሰት አይመስለኝም >»
ዛሬ ቃለ መሃላ የፈፀሙት ፕሬዝዳንት ኬንያታና ምክትል ፕሬዝዳንት ሮቶ ከዛሬ 5 አመቱ ምርጫ በኋላ የተከተሰተውን ግጭት በማሴር በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል ።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ