1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢህአዴግ ንብረት ክፍፍል፣የኮሮና ቫይረስ ስጋት፣የሞዕመናንና የፀጥታ ሀይሎች ዉዝግብ

ዓርብ፣ ጥር 29 2012

ሰሞኑን በማኅበራዊ መጘናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ሆነዉ ከሰነበቱ ጉዳዮች መካከል የኮሮና ቫይረስ ስጋትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የንብረት ክፍፍልና በአዲስ አበባ ከተማ ከቤተክርስቲያን ግንባታ ጋር ተያይዞ ለሁለት ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነዉ የምዕመናንና የፀጥታ ሀይሎች ዉዝግብ አነጋጋሪ ጉዳዮች ነበሩ።

https://p.dw.com/p/3XQUB
Symbolbild Twitter
ምስል imago/xim.gs

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


አንዳች መነጋገሪያ የማያጡት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በዚህ ሳምንትም የኮሮና ቫይረስ ስጋትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ የቻይና የሚያደርገዉ በረራ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል  የንብረት ክፍፍል እንዲደረግ ያሳለፈዉ ዉሳኔና በሳምንቱ አጋማሽ በአዲስ አበባ ከተማ ከቤተክርስቲያን  ግንባታ ጋር ተያይዞ በተከሰተ ዉዝግብ የሁለት ንፁሃን ሰዎች መገደል  በዚህ ሳምንት አነጋጋሪ ሆነዉ የሰነበቱ ጉዳዮች ነበሩ። 
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያለፈዉ ማክሰኞ የኢህአዴግን መፍረስ በይፋ ያሳወቀ ሲሆን ይህን ተከትሎ በአባል ድርጅቶቹ መካከል የንብረት ክፍፍል እንዲካሄድ ወስኗል።በዚህም መሰረት ብልጽግና ፓርቲና ህወሃት የኢህአዴግን ንብረትና ሂሳብ  አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ ፣በኢህአዴግ ስም ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣ከእዳ  ቀሪ የሆነዉን ሀብት ደግሞ  ሃብት  ሶስት እጁ ለብልጽግና ፓርቲ  ሩቡ ደግሞ የህወሃት ድርሻ መሆኑ ን ቦርዱ ገልጿል። በዚህ መሰረት የንብረት ክፍፍሉ  በህጉ መሰረት በ6 ወራት ዉስጥ አጠናቀዉ ፓርቲዎቹ  ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተወስኗል።
የንስር ዓይን በሚል ስም የሰፈረዉ አስተያየት «የምትከፋፈሉት ንብረት እኮ የሀገሪቷ እና የህዝቡ ነው። ኢህአዲግ ከየት ይዞት የመጣው የግል ሀብቱ ነው ። የህዝቡ ንብረት ነው የሚከፋፈሉት? ሲሉ ጠይቀዋል።
ዳንኤል ባልቻ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ «ይገርማል የድሀው መሬት እየተነጠቀ ለሀብታም በመሸጥና በኢትዬጲያ ህዝብ ስም በመጣ ብድር የኔ ነው የኔ ነው እሰጥ አገባ መግባት።ንብረትነቱ የኢትዬጲያ ህዝብ ነው ። ግን ያለአግባብ ያባከኑት የደበቁት የወሰዱት ብድር ያላግባብ  ያካበቱት ሀብት ቢጠና እንኳን ንብረት ሊኖራቸው ባለዕዳዎች  ይሆናሉ ።» ብለዋል።
አረዶ ሀሰንም   የንብረት ክፍፍሉ ተገቢ አይደለም ይላሉ።«አራቱ የ ፖለቲካ ድርጅቶች ንብረት እንከፋፈል ሲሉ ትንሽ እፍረት የላቸውም እንዴ? ከየት ያመጡትን ንብረት ነው የሚከፋፈሉት? አለን የሚሉት ንብረት  ከኢትዮጵያ ህዝብ የወሰዱት አይደል ።  ቦርዱ  ትክክለኛ ፈራጅና ዳኛ ቢሆን ኑሮ የነዚህ ፓርቲዎች ንብረትና ገንዘብ ለህዝባችን ማከፋፈል ነበረበት።ብለዋል።
አምበሉ አጥናፍ ደግሞ «መጋባት ያለነው መፋታትም እንዲሁ። ይህ ሲሆን ደግሞ  ንብረት  ክፍፍልም ያለና የነበረ ነዉ። ስልጣን ላይ ሲወጡ ገንዘብ መዝረፍ እንደሁ በኢትዮጵያም እንዲሁም በአፍሪቃ  ያለና የነበረ ባህል ነዉ።ምንም አዲስ ነገር የለም።ኢህአዴግየን ለቀቅ ።ሞታም ማረፊያ ትጣ» ሲሉ ነገሩን ወደ ቀልድ መልሰዉታል። 
ጌታሁን ዓሊ በዚሁ በፌስክ «የቀድሞው ኢህአደግ የተዋቀረው በአራቱ ፓርቲዎች ብቻ ነዉ? እያንዳንዳቸው 25% ስደርደርሳቸው አጋር ሲባሉ የነበሩት እነ አፋር፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉልና ሀረሪ ክልሎች ድርሻቸው ምንድን ነው? ሀብት ያፈሩት ብቻቸውን ነበር?» ሲሉ ጠይቀዋል። 
ትርሲት  ግዛቸዉ  የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ትክክል ብለሀል ወንድሜ 5 አጋር ድርጅቶች ለሃያ ምናምን ዓመት ያወጡት ገንዘብ ተበላ ማለት ነው። » በማለት አስተያየቱን ደግፈዋል።
« በስም አራቱ ድርጅቶች ይባል እንጅ የኢአድግ ንብረት የሁሉም አጋር ድርጅቶች ንብረት ነዉ እንዴት ለአራቱ ብቻ ይካፈላል። ደግሞ መከፋፈል ከለባቸዉ እንደየ አባላቱ ብዛት መሆን አለበት።«ያሉት ደግሞ ታረቀኝ ቡልቻ ናቸዉ።
ማቻሬ ሜዳ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረዉ ሀሳብ ደግሞ «የኔ ሀሳብ ግን ገንዘቡ ኢህአዴግ  ሃያ ሰባት ዓመት ላንገላታዉ ህዝብ ካሳ እንዲከፈል ነዉ።»
ዘዉዱ ፈቃዱ  «ደግነቱ ያለብን ብድር በቢሊዮን ስለሚቆጠር እንኳን በ6 ወር ክፍፍሉ በ60 ዓመትም አይካሄድ። ምርጫ ቦርድ የወሰነው  ዉሳኔ ተገቢ ነው ምክኒያቱም ከዕዳ ክፍያ ተርፎ ለህዋትም ሆነ ለብልፅግና የሚሰጥ ንብረት የለም አንጨቃጨቅ ጎበዝ።»ብለዋል። 
ከቻይና ዉሃን ግዛት የተነሳዉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎችና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣት  የዓለም ሀገራትን እያሳሰበ ነዉ።በኢትዮጵያም ሁለት ጊዜ ያህል በቫይረሱ ተይዘዋል ተብለዉ የተጠረጠሩ ሰዎች  መገኜታቸዉን ይፋ የተደረገ ሲሆን ቆይቶ ግን ነፃ መሆናቸዉ ተገልጿል።ያም ሆኖ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለዉ  ስጋት አሁንም ከፍተኛ ነዉ።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገዉ በረራ ደግሞ ስጋቱን እጥፍ አድርጎታል። የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅትን  የጉዞ እገዳ ማድረግ እንደማይገባ ማስታወቁን ተከትሎ- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር ተያይዞ ወደ ቻይና በረራ ማቆም ዋስትና አይሰጥም።መፍትሄው ለደንበኞች እና ሰራተኞች ጤንነት ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው ብለዋል።ይህንን ተከትሎ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮች ስጋታቸዉን ሲገልፁ ነዉ የሰነበቱት። 
ሚካአኤል አረጋ  የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ እንደ መንግስት ጭካኔ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ቸርነት ከኮሮና ይጠብቀን አንጅ ሌላ ምን ይባላል ብለዋል። አሸቱ ታደሰ  ደግሞ «ሁለቴም ተጠረጠሩ የተባሉ ሰዎች አራት ብቻ ናቸዉ።አኔ የምለዉ አዉሮፕላኑ አራት ሰው ብቻ ጭኖ ነው የመጣው? የተጠረጠሩት ሰዎች አራት ብቻ የሚባሉት።ሙሉ ተሳፋሪ ባለበት አዉሮፕላን መጥተዉ የሌሎቹ ጤንነት አስተማማኝ ይሆናል?»  ሲሉ ጠይቀዋል.። በለጥሻቸዉ አደም የተባሉ የፌስ ቡከ ተከታታይ ደግሞ ኑሮው እራሱ ኮሮና ሆኖብናል እንኩዋን በሽታው ተጨምሮብን ።በማለት ጽፈዋል።
በሃይሉ ግርማ  «ወድም ወንድሙን በሚገልበት  ሀገር  የኮሮና በሽታ ምን ያስፈራል።» ሲሉ ፤ ሄርሚላ ፍቅር የተባሉ  አስተያየት ሰጪ ደግሞ« ልክ ነሀ ወንደሜ ከመታገትና ከመገደል አንድ ፊቱን ወረርሽኝ ሳይሻል አይቀርም» ብለዋል።  
ሀይለማርያም መዝገቡ ደግሞ «አየር መንገዱ ይዘጋ ማለት አንድ ነገር ነው.።ግን የኢትዮጰያ አየር መንገድ በረራ ቢያቆም ፤ሌሎቹ አየር መንገዶቸ ሰው ያመጡ የለም እንዴ ? ሲሉ፤ መሀመድ ሰዒድ«የበረራዉ መቆም በሽታዉን ባያቆመዉም ተጋላጭነትን ይቀንሳል»ሲሉ ተቃዉመዋል።
መሲ አባድር የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ የቻይናን ብድር በኮሮና መንዝረን ልንከፍል ነዉ እንዴ? እረ በፈጠራችሁ በረራዉን አቁሙልን።ብለዋል። «ከሰዉ ህይወት ገንዘብ የሚበልጥባት ሀገር አይ ኢትዮጵያ።»ያሉት ደግሞ መሳይ ወልዴ ናቸዉ።
የቃጅማዉ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረዉ አስተያየት ደግሞ «ህዝብን የሚታደግ አምላክ ይታደገን እንጂ ፣ ምንም አስተያየት ማቅረብ አይቻልም ፣ሌሎች ሃያላን አገሮች ያቋረጡትን በረራ ከዚህ እጅግ አስፈሪ ከሆነ ምጣት ጋራ ግብግብ መግጠምና በምርመራ እናገኘዋለን ማለት ምን ማለት ነው ፣ ምን ይሻለናል ጎበዝ ? ሲሉ ጠይቀዋል
«ከቻይና በረራ የሚመጣዉ  ዶላር ከህዝብ ህይወት ጋር እንዴት ይተመናል ?በድህነታችን ላይ ይህ በሽታ ከገባ ከባድ ነዉ። በአንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ይሏል አንዲህ ነዉ።»ያሉት ደግሞ አባድር ሰአኢድ ናቸዉ።
 ሊሊ ተስፋዬ «አረ እባካቹ መጀመሪያ በፖለቲከኞችና በአክቲቪስቶች የገባዉን ቫይረስ መቆጣጠር ሳንችል ሌላ ቫይረስ? አሁንስ ህዝባችን ፈረደበት ወገን በስንቱ እንጨነቅ።»ሲሉ ጽፈዋል።
ረቡዕ ጥር 27 ቀን 2012 ዓ/ም ሌሊት ሰባት ሰዓት አካባቢ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሃያ ሁለት በሚባለው አካባቢ  ከአንድ «በህገ ወጥ መንገድ ተገነባ» ከተባለ ቤተክርስቲያን መፍረስ ጋር ተያይዞ በፀጥታ ሀይሎችን በምዕመናን መካከል በተፈጠረ ዉዝግብ የ2 ሰዎች መገደልና የበርካቶች ሌላዉ የዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ መነጋገሪያ ነበር።
ያቆብ ተስፋየ የተባሉ አስተያየት ሰጪ«በእኩለ-ለሊት ፖሊሶችን ወደ አካባቢው የላከውን አዛዥና ለ2 ሰዎች ሞትና ለ17 ሰዎች ጉዳት ተጠያቂ የሆኑትን ፖሊሶች መንግስት በአስቸኳይ ለህግ አቅርቦ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ አለበት።ሲሉ፤ አብርሀም ኢዮአስ «መንግስትና ፍርድቤት ባለበት ሀገር ህገ ወጥ ስራ ቢሆን  ህጋዊ ሂደቱን ተከትሎ የድርጊት ፈፃሚዎቹን  ተጠያቂ ማድረግ እየተቻለ ፤ ጨለማን ተገን በማድረግ ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ በታጠቀው አፈሙዝ ንፁሃንን ተኩሶ በመግደል ፈራጅ የሚሆንበት አካሄድ መቆም አለበት ።» በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል።
ከተማ ከተማ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ ደግሞ«ህግን በቀን ማስጠበቅ እያለ በሌሊት ሰው መግደል ሽፍትነት ነው።እንግዲህ መንግስት ወደ ሽፍትነት  ከተቀየረ ምን ማድረግ ይቻላል ? ብለዋል።
 ጆይ ዴልፕሮ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረዉ አስተያየት«መንግስት ህግን ለማስከበር ቀንና ለሊት መምረጥ የለበትም።ባይሆን የሰዉ ህይወት እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ነበረበት።» ይላል። ሙሴ ረጋሳ ደግሞ«አይደለም ሰባት ሰአት በየትኛዉም ጊዜ ህገ ወጥ ስራ ሲሰራ መንግስት ህግ የማስገበር ስራ ይሰራል።መስራትም አለበት።»በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።  
ቢቶደደድ ራስ በተባለ የፌስቡክ የሰፈረዉ አስተያየት ደግሞ«ሀይማኖትህ ተነካ፥ ተደፈርክ ፥እምነትህን ሊያጠፉብህ ነዉ ተነስ በማለት ህዝብን በማስቆጣት በማነሳሳት ለአመፅ ፥ ለብጥብጥና ደም ለማፍሰስ ከተለያዩ ሀይሎች ከፍተኛ ሴራ ሌት ተቀን እየተሰራ ነዉ ፤ወገን የሚፈጠሩ ክስተቶችን ለምን?እንዴት ?በምን ምክንያት እያልን ሰፋ አርገን ብንመለከት የተሻለ ነዉ።መስጊድም ቤተከርስቲያንም እምነትም ሳይስተጓጎል ሊቀጥል የሚችለዉ ሀገርና ህግ ሲኖር ነዉ።እባካችሁ ከዚህ ጀርባ አገር የሚያፈርስ ትልቅ ደባ ያለ ይመስላል  እንጠንቀቅ።» 
ሰብለ ዮሀንስ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ «ህግና ፍትህ ካለ ገዳዮቹ ለፍርድ ይቅረቡ።ወይ ፖሊስ እንደሌባ በሌሊት መምጣት።»ሲሉ አግራሞታቸዉን  ፅፈዋል። 
ዳዊት ማሞ  ደግሞ «ህጋዊነቱን ሳይጨርሱ ምዕመኑን ወደ ግንባታና አምልኮ ሲመሩ የነበሩትም በአኔ አስተያየት ጥፋተኞች ናቸዉ።ለእኔ ግን ህግ የጣሱ ምዕመናንም ነበሰ ገዳዮቹም እንደየጥፋታቸዉ ልክ በህግ ሊጠየቁ ይገባል።» ሲሉ፤ዳንያ ዳባ ደግሞ «አሁንም በዚህ  መልክ ለግጭት ክፍት የሆኑ የአምልኮ ቦታዎቸ ካሉ ጥንቃቄ ያሻቸዋል። በመንግስት በኩል ዘላቂ መፍትሄ ቢሰጥ። »ብለዋል።
«ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ ባገኜዉ ክፍት ቦታ ቤተ- እምነት መገንባት የለበትም ።ሀይማኖትን መዉደድ በዚህ አይገለጥም።የሚሻለዉ ህጋዊ መንገድ መከተል ነዉ።ለሞቱት ወጣቶች ነብስ ይማር »ያሉት ደግሞ በዚሁ ፌስቡክ አመለወርቅ ሰናይ ናቸዉ።

Äthiopien PK Abune Mathias
ምስል DW/T. H. Haile-Giorgis
China Wuhan Labor testet auf Coronavirus
ምስል AFP
Logos TOLF  EPRDF

 

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ