1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢህአዴግ ድርጅቶች ጉዞ ወዴት?

ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2011

የኢሕአዴግ መሥራችና እስካለፈው ዓመት ድረስ የግንባሩ ዋና ፓርቲ ይባል የነበረው የህወሀት ማ/ኮሚቴ ባለፈው ሳምንቱ ስብሰባ ማጠቃለያ ያወጣው መግለጫ ከኢህአዴግ አመራር በኩል የተሰሙ ሃሳቦችን የሚጻረሩ ነጥቦችን የያዘ ነው። ከነዚህም አንዱ ዶክተር ዐብይ አህመድ የኢህአዴግ አባላት እና አጋር ድርጅቶች ተዋህደው አንድ ፓርቲ ይሆናሉ ማለታቸውን ነው።

https://p.dw.com/p/3Gnxm
EPRDF Logo

የኢህአዴግ ድርጅቶች ጉዞ በፖለቲካ ተንታኝ እይታ

ምክር ቤቱ በድርጅቱ ስራ አፈጻጸም እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እና ግምገማ እንደሚያካሂድ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። በመካከላቸው መከፋፈል እና ልዩነት እንዳለ የሚነገረው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የወደፊቱ ጉዞ እንዴት ይቀጥላል የሚለው ማጠያየቁ አልቀረም። ከምክር ቤቱ ስብሰባ ሊጠበቅ የሚችለውም እንዲሁ ያነጋግራል። 
ኢትዮጵያ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች በሚባልበት በዚህ ወቅት ላይ የሚካሄደው የሐገሪቱ ገዥ የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ትኩረት መሳቡ አልቀረም። በዝግ የሚካሄደው ስብሰባ የሚነጋገረው በጥቅሉ በስራ አፈጻጸም እና በወቅታዊ ጉዳዮች መሆኑ ከመገለጹ ውጭ እስከ ዛሬ ከቀትር በኋላ ድረስ ዝርዝሩ አልተነገረም።ይሁን እና የኢሕአዴግ መሥራችና እስካለፈው ዓመት ድረስ የግንባሩ ዋና ፓርቲ ይባል የነበረው የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ ያወጣው መግለጫ ከኢህአዴግ አመራር በኩል የተሰሙ ሃሳቦችን የሚጻረሩ ነጥቦችን የያዘ ነው። የመግለጫው ይዘት የምክር ቤቱ መነጋገሪያ ሊሆን እንደሚችል መገመትም አያዳግትም። የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚሁ መግለጫው እንደማይቀበላቸው ከገለጻቸው ጉዳዮች አንዱ ከዚህ ቀደም የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር ዐብይ አህመድ የኢህአዴግ አባላት እና አጋር ድርጅቶች ተዋህደው አንድ ፓርቲ ይሆናሉ ማለታቸውን ነው። ህወሀት የድርጅቶቹ መዋሀድ አሁን ባለው ሁኔታ ሊታሰብ የሚችል አይደለም ብሏል። ዶቼቬለ DW በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኮንን በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ድርጅቱ ለዚህ የሰጠውን ምክንያት በቅጡ ማጤን እንደሚገባ ተናግረዋል። በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት  ይቀርብበት በነበረው ወቀሳ ምክንያት መዋሀዱ ለድርጅቱ  ቀላል ሊሆን አይችልምም ብለዋል።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Office Of The Prime Minister

«ህወሀት በመግለጫው ላይ እኛ አሁን እየተግባባን አይደለም።እና ወደ ውህደት ከመሄዳችን በፊት በመካከላችን ያለው መጠራጠር ልዩነት ይፈታ ነው።እየተጠራጠርን ርስበ ርስ ባልሆነ ነገር እየተፈላለግን ወደ ውህደት ልንሄድ አንችልም ነው።ይሄ ደግሞ ተገቢ ይመስለናል ለኔ ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ልዩነት በግልጽ የሚታይ ነው። ላለፈው አንድ ዓመት የሄድንበትን ርቀት ህወሀትን በሀገሪቱ ለታዩ ነገሮች በሙሉ ጥፋተና አድርገን የሳልንበት ማለት ነው ።ስለዚህ ይህንን ተቀብሎ ህወሀት እኔ ነኝ ጥፋተኛው ብሎ ወደ ውህደት በቀላሉ ይገባል አይሆንም።ባለፈው አንድ ዓመት ሀገሪቷ አስቸጋሪ የሆነ ቀውስ ውስጥ ገብታለች ብለን እንመን እያለ ነው እኮ ህወሀት። ያንን ደግሞ የኦዴፓ ሰዎች በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀበሉ አይመስለኝም። አዴፓም በተመሳሳይ መልኩ የቱ ጋ እንደምትቆም አይታወቅም።»
በአንድ ዓመቱ የለውጥ ጉዞ ውስጥ አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከርበርስ ግንኙነት አንስቶ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይዘው መቀጠል እንዳልቻሉም በግልጽ እየታየ መሆኑንም ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኮንን ያስረዳሉ።
«ለአንድ ዓመት የተደረገው ጉዞ ህወሀትን አስከፍቶ መቀሌ አስገብቶታል።ህወሀት ያደርግ የነበረው ባለፉት አንድ ዓመታት ከኢህአዴግ እንደወጣ ድርጅት ወይም ደግሞ ከኢህአዴግ እንደተለየ ድርጅት ነው። ከዛ በተጨማሪ በኦዴፓ እና አዴፓ መካከል የዛሬ ዓመት የነበረው አይነት መንፈስ የለም በአሁኑ ሰዓት መጠራጠሮች አሉ ።ልዩነቶች አሉ።የአስተሳሰብ ልዩነት አለ። ሌላኛው ደኢህዴን ነው።ደኢህዴን አስቸጋሪ ነገር ውስጥ ነው ያለው።ሌጅትሜሲውን አጥቷል ክልልሉ ውስጥ ።በአራቱም ድርጅቶች በተለይ በሦስቱ መካከል በአስተሳሰብ ከፍልስፍና አንጻር ከአይዲዮሎጂ አንጻር ችግሮቹን የሚመለከቱበት መነጽር ለችግሮቹ የሚሰጡት መፍትሄ በአጠቃላይ የወደቀ ግንኙነት ነው ያላቸው ሶስቱም መካከል።»
ህወሀት በመግለጫው የግንባሩን መስመር የሳተ አካሄድ እንዳለ እና ለዚህም ተጠያቂው አመራሩ መሆኑን አስታውቋል። ረዳት ፕሪፌሰር ዳንኤል በበኩላቸው ኢህአዴግ ከዚህ ቀደም ይከተለው የነበረውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ይተው አይተው በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም፤ስለዚሁ ጉዳይ  የግንባሩ አባል ድርጅቶች የሚሉትም የተለያየ ነው ይላሉ። 
«ወደ ትግራይ ስትሄጂ አሁን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው።ሌሎቹን ስትጠይቂያቸው ወደ ካፒታሊዝም እየሄድን ነው።ወደ ሊብራሊዝም እየተጠጋን ነው። ስለዚህ  ወጥቷል መውጣት ብቻ ሳይሆን ውጥንቅጡ ወጥቷል ነው።የትኛው ነው በትክክል አይዲዮሎጂያቸው የሚለው ነገር የፈለገው ሰው የፈለገውን ይናገራል። እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩት  ኢህአዲግ ውስጥ ክፍተቶች እንዳሉ ነው።አዎ ኢህአዴግ ከመስመሩ ወጥቷል። »
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ኢህአዴግ በዚህ ስብሰባ ልዩነቶቹን ካላስተካከለ መዘዙ ከባድ ነው የሚሆነው።በረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል አስተያየት በአሁኑ የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ትልቅ ሊባል የሚችል ለውጥ ላይመጣ ይችላል። ምናልባት ግን ከህወሀት ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ሊረግብ ይችል ይሆናል ብለዋል። 

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ