1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዲግ መጻኢ የውሳኔ እቅድ፤ ከግንባር ወደ ውህድ

ዓርብ፣ መጋቢት 7 2010

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውሱን ለመፍታት እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት ውስጣዊ ችግሮቹን ፈትቶ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት የመድብለ ፓርቲን ሥርዓት ማጠናከር እንደሚገባ አንድ ምሁር አስገነዘቡ።

https://p.dw.com/p/2uSNi
Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ውሁድ ፓርቲ?

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውሱን ለመፍታት እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት ውስጣዊ ችግሮቹን ፈትቶ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት የመድብለ ፓርቲን ሥርዓት ማጠናከር እንደሚገባ አንድ ምሁር አስገነዘቡ :: ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ከብሄራዊ ድርጅቶች ግንባርነት ወደ ተዋሃደ አንድ ፓርቲ ለመሸጋገር የያዘው ዕቅድ ሊሳካም ላይሳካም ይችላል ሲሉ ለዶቼቨለ የገለጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር አስናቀ ከፍአለ ለውህደት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ግንባሩ እና አጋሮቹ መቶ በመቶ የተቆጣጠሩትን የፓርላማ ሥርዓትም ማሻሻል እንደሚገባም አመልክተዋል :: ዝርዝሩን እንዳልካቸው ፈቃደ አጠናቅሮታል ::

የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ በፖለቲካ ቀውስ እና አለመረጋጋት የሚናጠው ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ከአመታት በፊት ወጥኜው ነበር ባለው ወደ ተዋሃደ አንድ ፓርቲ የመሸጋገር ዕቅድ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለፊታችን ነሐሴ ወር ላይ ቀጠሮ ይዟል :: የግንባሩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እስካሁን አብረው ከሚሰሩት  አጋር ከሚሏቸው ፓርቲዎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነትም አስመልክቶ ኢህአዲግ በዚሁ በነሐሴው የድርጅቱ አጠቃላይ ጉባኤው ላይ ይወስናል ነው ያሉት :: አሁን በሀገሪቱ ከሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት  በገዢው ፓርቲ መካከል ተፈጥሮ ከቆየው መጠራጠር እና አለመተማመን እንዲሁም ዕለት ከዕለት ከሚለዋወጠው የሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አኳያ ለውህደት የሚደረገውን ጉዞ ይሳካል ወይም አይሳካም ብሎ ከወዲሁ መተንበይ እንደሚያስቸግር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት ፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር አስናቀ ከፍ አለ ያስረዳሉ ::

ከወራት ግምገማ እና ግለ ሂስ በኋላ ኢህአዲግ ችግሬን በጥልቀት ተገንዝቤያለሁ ኪራይ ሰብሳቢነት የአቅም ማነስ ችግር ሙሰኝነት እና ብልሹ አመራር በውስጤ ተንሰራፍቷል ብሎ ነበር:: የተፈጠረውን ቀውስም ለመፍታት የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋለሁ ባለ ማግሥት የዜጎችን መሰረታዊ የዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብቶች ጨርሶ የሚገድብ እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም እግር ከወርች የሚያስር ነው የተባለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል። ከዚህ በተያያዘም በመንግሥት ኃይሎች የሰዎች ግድያ እና እስር  እየተካሄደ መሆኑ እየተዘገበ ነው:: እንዲህ የፖለቲካ ውዝግቡ እና እሰጥ አገባው ባየለበት ሁኔታ የኢህአዲግ አባል ድርጅቶች እንፈጥራለን ያሉትን ውህደት የህዝባዊ ተቃውሞው መፍቻ ቁልፍ አድርገው የተነሱ ይመስላል የሚሉ ወገኖች አሉ :: የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የፖለቲካ ተንታኙ ዶክተር አስናቀም ውህደቱ መፍትሄ ያመጣል ? ለሚለው የብዙዎች ጥያቄ የበኩላቸውን አስተያየት ሰንዝረዋል::

Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson

ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔር አገር መሆኗን የሚጠቅሰው ኢህአዲግ በመተዳደሪያ ደንቡም ይሁን በሚመራባቸው አጠቃላይ የአደረጃጀት መርሆዎች የግንባሩን ዓላማ ለማሳካት ብሔረሰባዊ አደረጃጀቶች ብቻ አዋጭ መሆናቸውን ነው ደጋግሞ የሚገልጸው:: ግለሰቦችን በተናጥል የሚያሰባስብ ኅብረ ብሔር ድርጅት ግን ሕገ መንግሥታዊ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ብሔር ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን ለማታገል አቅም አይኖረውም የሚል ዕምነት አለው:: ዶክተር አስናቀ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም::

በአገሪቱ የሚታየው የፖለቲካ ትኩሳት እና ግለት ዕለት በዕለት የሚለዋወጥ ሆኗል:: የፊታችን ነሐሴ ወር የኢህአዲግ  ብሔራዊ ተጣማሪ ድርጅቶች  ውህደት ለመፍጠር የያዙት ዕቅድ ላይ የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ለ 27 ዓመታት በዘለቀው የግንባሩ አመራር መጻኢ ዕድልም ሆነ በአገሪቱ የወደፊት ጉዞ ላይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ መተንበይ እንዳማይቻል ብዙዎች ይስማማሉ :: እቅዱ ውሳኔ ቢሰጥበትም እንኳ እንደ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የኢህአዲግ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ ገለጻ ከሆነ ወዲያውኑ ኢህአዴግ  ውሁድ ፓርቲ ይሆናል ማለት ግን አይደለም ::

እንዳልካቸው ፍቃደ

ሸዋዬ ለገሰ