1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ ስብሰባና ውጥረት በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2010

በይፋ ባይነገርም በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል ድርጅቶች መካከል መቃቃር መፈጠሩ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ይሰማል። የኢሕአዴግ መደበኛ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በዝግ እንደቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/2pf3v
Karte Äthiopien englisch

ውጥረት ከነገሰበት የኢሕአዴግ ስብሰባ ምን ይጠበቃል?

ኢሕአዴግ ታኅሣሥ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. የጀመረው ስብሰባ በዝግ እንደቀጠለ ነው። ዝርዝር ጉዳዩ በይፋ ባይገለጥም በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች በኢሕአዴግ መካከል ውጥረት መንገሱ ይሰማል።  የሕግ ባለሞያ እና ጦማሪ ዳንኤል ብርሐኔ ከልዩነት ያለፈ ነገር አይታያቸውም። «አንዳንድ ነጥቦች ላይ የሚታይ ልዩነት ወይንም መስማማት ሊኖር ይችላል» ያሉት ጦማሪው «እንደ አጠቃላይ ግን ይኼ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች እና በተለያዩ ቦታዎች የምናየው ምኞት ነው።» ብለዋል። «ይጣላሉ፣ ይለያያሉ የሚለው እነዚህ ሦስት ድርጅቶች ወይንም አራት ድርጅቶች በአጠቃላይ እንደ ኢሕአዴግ ካላቸው የጋራ ኅልውና ውጪ አራቱ ተለያይተው የተለየ የፖለቲካ ዕድል፤ እጣ ፈንታ ይኖራቸዋል ብዬ እኔ ብዙም ዐይታየኝም።» ሲሉ አክለዋል። 

ጦማሪና የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ሥዩም ተሾመ ከኢሕአዴግ ስብሰባ ቀደም ብሎ ሕወሓት የደረሰበት ውሳኔ ስር ነቀል ለውጥ አልባ መኾኑ በድርጅቱ ውስጥ ውጥረቱን አባብሷል ይላሉ። የሀገሪቱ የደኅንነት ሹማምንት በሕወሓት ሥራ አስፈጻሚነት መመረጣቸውም በኢሕአዴግ አባላት ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል። «በእርግጥ አኹን በይፋ እንደሚታየው ኦሕዴድ እና ብአዴን በአንድ ወገን እንዲሁም ሕወሓት እና ደሕዴን በሌላ ወገን ኾነው ልዩነት ተፈጥሯል። ልዩነት ሲፈጠር ምንድን ነው የሚደረገው? ይኼ ግለሰብ ሥራው ምንድን ነው? የፓርቲ አባል ኾኖ እዛ ጋር የተቀመጠው ከብአዴን እና ከኦህዴድ አመራሮች የተለየ ሐሳብ ተነስቶ የተለየ አቋም ሲያራምዱ ምናልባት እንደተባለው ስብሰባ ረግጠው ከወጡ ይኽ ግለሰብ ምን ሊሠራ ነው? የሀገሪቱን ደኅንነት እና የሕዝቡን ሠላም እንዲያስከብር የተሰጠውን የሥልጣን መዋቅሩን ተጠቅሞ እነዚህ የፖለቲካ አመራር ላይ ተጽዕኖ  ለማሳረፍ መንቀሳቀስ የሚጀምርበት ኹኔታ ነው ያለው።»

ጦማሪ ሥዩም አያይዘው ሲናገሩ የኦሕዴድ እና የብአዴን አባላት ላይ ማስፈራራት እና ጫና በመፍጠር የሕወሓት የበላይነትን ለማስጠበቅ እየተሠራ ነውም ብለዋል። የኢህአዴግ ድርጅቶችን አስተሳስሮ የቆየው የብሔር ፖለቲካም ቢሆን የተወሰኑ ወገኖችን የሚጠቅም በመኾኑ ልዩነቱ እየሰፋ መጥቷል ሲሉ አክለዋል። እንደ ጦማሪ ዳንኤል ግን በግንባሩ ውስጥ ተፈጠረ የተባለው ልዩነት በድርጅቶች መካከል ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ የተከሰተ ነው። 

Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

«እንደ ድርጅት ኦሕዴድ ወይንም ብአዴን ወይንም ሕወሓት  አለያም ደሕዴን አኩርፎ ወይንም ጥሎ  የሚወጣበት ወይንም እንደዚህ አይነት አጋጣሚ እኔ አልጠብቅም በበኩሌ» ያሉት ጦማሪ ዳንኤል ነገር ግን ይላሉ። «ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ በተለያየ ምክንያት  ምክንያቱም እንደየ ሰዉ አስያየት ነው፤ በተለያየ ምክንያት ጫፍ ላይ የሚወጣ ሰው ይኖራል።  አንዳንዴ ቅሬታ ያለህ ጉዳይ እና እዚህ የምትጨቃጨቅበት ጉዳይ አንድ ላይኾን ይችላል፤ግን የዚያው ነጸብራቅ ነው የሚኾነው። እና በአንድ ወይንም በሌላ መልኩ ችግሮቻችን እነዚህ ናቸው ብለው ሲስማሙ እነዚህ ችግሮቻችን አይደሉም ብለው ውድቅ ሲያደርጉ ይኼን አልስማማም ብሎ ጫፍ የሚወጣ ሰው ይኖራል፤ ወይ ሥራ የሚለቅ ይኖራል።»

ጦማሪ ዳንኤል አያይዘውም፦ «ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶቹ የተለያዩ ሐሳቦች በተለያዩ ሰዎች ቀርቦ በዚያ ላይ ክርክር ተደረገ እንጂ፤ አንዱ ቡድን ሌላውን ቡድን እያጠቃ ነው የሚል መረጃ የለኝም» ብለዋል። 
በሀገሪቱ ሰፍኖ የቆየው የብሔር የፖለቲካ «ተቃራኒ ለሚሉት ሌላ ወገን ጥላቻ የማሳየት፣ የማድላት እና የመግፋት ባሕሪ አለው» ያሉት ጦማሪ ሥዩም በሀገሪቱ ቅራኔ ለመስፋፋቱ ሰበቡ ያ ነው ባይ ናቸው። ካለፉት 20 እና 25 ዓመታት ወዲህ ግን በአማራ እና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል «በተለይ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች» መቀራረብ መታየቱ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥም ተንጸባርቋል ብለዋል። 

«በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ እንኳን ኹለቱ ፓርቲዎች በጋራ አንድ ላይ ትብብር ፈጥረው ፤ የሕወሓት የበላይነት ይብቃ ብለው ሕወሓት ጋራ የኃይል ሽኩቻ ውስጥ የገቡበት ኹኔታ ነው ያለው። እና የዚህ ኹሉ መሠረቱ አንደኛ ሕወሓት ኢሕአዴግ  የፖለቲካ አመለካከት ስር የተመሰረተ የብሔርተኝነት አመለካከት  አንድ፤ ኹለተኛ ደግሞ ይኼ የብሔርተኝነት አመለካከት  እንዲሁም አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱ  ሕወሓትን የበላይነት ለማስቀጠል ተብሎ በዚያ ላይ የተመሰረተ  እንደኾነና ያ ነነገር ይብቃ የፖለቲካ አመለካከቱ አክራሪ የፖለቲካ  አመለካከት ይዘው ብሔርተኝነት ይቀየር፤ የሕወሓት የበላይነት ይብቃ የሚለው ነገር ይበልጥ ተጠናክሮ የቀጠለበት ኹኔታ እናዳለ ነው የሚታየኝ።»

በዝግ ስበሰባ የተቀመጠው የኢሕአዴግ የፌስቡክ ገጽ ላይ፦ «እየታደስን እንሰራለን፤ እየሠራን እንታደሳለን!» የሚል መፈክሩ በጉልኅ ሠፍሯል። በእርግጥ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ምን እንደሚፈጠር መገመት አይቻልም፤ በመላ ሀገሪቱ የሚታዩ ውጥረቶች አቅጣጫም ዐይታወቅም። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ