1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ «የርስ በርስ መጠራጠር»

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13 2010

በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የተነሳው የ«እርስ በእርስ መጠራጠር» በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላይም ወደ ቃላት ጦርነት የተቀየረ ይመስላል። ቁሩቁሱ ባየለበት ባሁኑ ወቅት ኢሕአዴግ ስለ ዝግ ስብሰባው መግለጫ አስነብቧል።

https://p.dw.com/p/2pmv2
Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

በኢትዮጵያ ተቃውሞው መቀጠሉና «የሕዝባዊ ወገንተኝነት መሸርሸር» በኢሕአዴግ ውስጥ

ወትሮ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት በሚያንጸባርቁ ቡድኖች ዘንድ ነበር ይስተዋል የነበረው። አኹን ግን ቁርቁሱ በገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር አባል ድርጅቶች መካከል መስተጋባት ጀምሯል። የቁርቁሱ ነጸብራቅ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይም እየተስተዋለ ነው። በዚህ መሀል ኢሕአዴግ በዝግ ስብሰባው ደረስኩበት ያላቸውን ነጥቦች ረቡእ ምሽት አምስት ደቂቃ ግድም ርዝመት ባለው የቴሌቪዥን መግለጫ ዐሳውቋል። በአባላቱ ዘንድ «እርስ በእርስ መጠራጠር» መንገሡ ይፋ በተደረገበት መግለጫ ኢሕአዴግ ዝግ ስብሰባው «በድል እንደሚጠናቀቅ» አትቷል። 

በሀገሪቱ የተለያዩ ማእዘናት ውጥረት በነገሰበት በአኹኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚያካሂደው ዝግ ስብሰባ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል። በዝግ ስለሚደረገው ስብሰባ አንዳንድ የማኅበራዊ መገናኛ ንቁ ተሳታፊዎች አገኘን የሚሉትን መረጃ በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ። ከአንዱ ወገን የሚወጣው መረጃ በሌላኛው ወገን ሲደቆስና ሲተች ላስተዋለው በእርግጥም ኢሕአዴግ በዝግ ስብሰባው ቁርቁስ ውስጥ ነው ለሚባለው አስተያየት ማንጸባረቂያ የኾነ ይመስላል። 

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአንድ ሣምንት ያኽል በዝግ ሲያከናውን ስለቆየው ስብሰባ ረቡእ ምሽት ላይ ያወጣው መግለጫ፦ «ከታኅሣሥ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ግምገማ በማካሄድ ላይ» እንደሚገኝ በማተት ደረስኩበት ስላለው ድምዳሜ እንዲህ ይላል። «በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅታችን አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን በሚገባ ይገነዘባል። ሃገራችን በአሁኑ ሰዓት ለምትገኝበት አስጊ ሁኔታ ድክመቱ ያደረገው አስተዋፆ ከፍተኛ ነው» ብሏል። 

መግለጫው በድርጅቱ ውስጥ፦ «የርስ በርስ መጠራጠር፣ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦትና የሕዝባዊ ወገንተኝነት መሸርሸር» እንዳለ አትቷል። «በቅርብ ጊዜ በድል» ይጠናቀቃል ያለውን ዝግ ስብሰባ ለመላው የሀገሪቱ ነዋሪዎች እና «ለኢሕአዴግ አባላት በተከታታይ የሚገልፅ መሆኑን» በማተት ነው መግለጫው የተደመደመው።

መግለጫውን ተከትሎ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ድንቅነሽ አበበ በትዊተር ገጿ በአጭሩ ባሰፈረችው የእንግሊዝኛ ጽሑፏ፦ «ፍርክስክሱ ወጣ!» ብላለች። 

Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Reuters/Tiksa Negeri

ቃርባታ ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቀጣዩን መልእክት አስፍሯል። «እሺ፤ የኢህአዴግ እህት ተብዬዎች በሁሉም ነገሮች ተስማሙ ተባለ እንዴ? ማን ማንን እንደሰለቀጠው መቼ ነው ታዲያ ወጥተው የሚነግሩን? ጠቅላይ ሚንሥትሩስ ሀገሪቱን አኹንም እየመሩ ነው?» ብሏል።

ኢሕአዴግ (EPRDF official) በተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ላይ በኢትዮጵያ ስለተከሰተው ችግር  መንስዔ ከግንባሩ ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር የተደረገ ያለውን አጠር ያለ እና የተቆራረጠ የቪዲዮ ቃለ መጠይቅ አስፍሯል። «አሁን በሀገራችን እየታዩ ላሉ ችግሮች መንስዔያቸው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ መሆኑን አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያነሳሉ፡፡» የሚል ጽሑፍ ከቪዲዮ መልእክቱ ጋር ያያዘው የኢሕአዴግ የፌስቡክ ገጽ ቃለ መጠይቁን ያስከትላል። «ፌዴራላዊ ሥርአቱ በዚህ መንገድ የፈጠረው ምንም አይነት ችግር የለም።» ያሉት አቶ ሽፈራው፦«ሲኾን ሲኾን ችግር ነው የፈታው» ብለዋል እዛው የቪዲዮ ቃለ መጠይቅ ላይ። 

ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ጎዳና «ድርቅቅቅቅቅ ማለት ራስን ያስበላል!» ሲል አጠር ያለ መልእክቱን በፌስቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል። «ህወሃት/ኢህአዴግ፣ ከገባት…ተኝታም፣ ቆማም፣ ቆዝማም፣ ተሰብስባም፣ ተራምዳም…ቢሆን፤ አደገኛ ማጥ ውስጥ መግባቷን ማሰብና ማመን አለባት  አሁን!» ሲል በትምኅርተ አንክሮ ዐረፍተ ነገሩን የዘጋው ኤልያስ ያ ካልሆነ ምን ሊከሰት እንደሚችል እዛው ጽሑፉ ላይ ያብራራል። «እንደው…ለቸከ የሥልጣን፣ የጥቅም፣ የትምክህት፣ የማንአለብኝነት፣ የጉልበት ጥም…ሲሉ፤ ግግምምም ማለት፣ እያዩ መበላትን ያስከትላል! ከሌሎች አንባገነንና ጨቋኝ ችኮዎች ፍጻሜም ተማሩ። የፖለቲካ ስማርትነት ያሻል! አሊያ…እየሆነ ያለውን ማየት ነው!» ብሏል። ኤልያስ ጽሑፉንን የሚያጠቃልለው «…ልብ ያለው ልብ ይበል» ከሚል መልእክት ጋር ነው።

ኪዳነ ወልድ ደስታ፦«አመራሩ ሀገሪቱን መምራት ካልቻለ በየጊዜው ምክንያት ከመደርደር ህዝባዊ መንግስት እንዲቐቕም ከውስጥም ከውጭም ጥሪ በማድረግ ስልጣን ቢያስረክብ» የሚል አስተያየት የሰጠው በፌስቡክ ነው። 

አብዱረሒም በትዊተር ጽሑፉ፦ «ኢሕአዴግ ባወጣው መግለጫ ያደረኩት ተሃድሶ ጥልቀት ያልነበረው በመሆኑ ነው በሀገሪቱ ችግር የተከሰተው ብሏል። ተሃድሶ ሳይሆን ተገንድሶ ሚወድቀበት ቦታ አለመታወቁ ነው እኛን ያሳሰብን» በማለት የሣቅ ምልክት አኑሯል። ሃሊት መንገሻ በበኩሉ እዛው ትዊተር ላይ ቀጣዩን ጽፏል፦ «ኢህአዴግ አመነ! ቅቡልናዬ ተሸርሽሯል...ሃሃሃ "ታድሼ ወጣሁ መስመሬንም አስተካከልኩ" ከተባልን አመት ሞላን እንዴ?» አማኑኤል ተስፋዬ በእንግሊዝኛ ባቀረበው የትዊተር ጽሑፍ መግለጫው ላይ እንዲህ ሲል ተሳልቋል። «የመግለጫው ርእስ መኾን የሚገባው ‘በሺህ ቃላት አንዳችም የማይባለው እንዴት ነው‘» በማለት ይነበባል።

ኢሕአዴግ የሰጠውን መግለጫ በተመለከተ በዋትስአፕ ቊጥራችን የሚከተሉት አስተያየቶች ደርሰውናል። «መግለጫው ለእኔ እንደ መግለጫ ሳይሆን እንደ ማላገጫ ነው። ምክንየቱም የተለመደ ና ህዝብ ላይ"በተሀድሶ " ስም የሚቀልድ ነው።» ይላል የመጀመሪያው መልእክት።

Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Reuters/Tiksa Negeri

«የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አሁን አገሪቱ ዉስጥ «እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅታችን አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው» ናቸዉ። ምን ማለት እንደፈለገ ምኑ ታውቆ ምንዓልባት ይህን ሲል «እየወሰድነው ያለነው እርምጃ በቂ አይደለም ስለዚህም ነው ሁሉም የሚቃወመን» እያለ ሊሆን ይችላል የሚል መልእክትም ደርሶናል። 

«መግለጫው ትክክል እና ትክክል ነው። ነገር ግን ትክክልነቱ የምረጋጠው በቆራጥ አመራር ወደ ሥራ ወደ ለውጥ ከተገባ ነው። ኢሕአዴግ ዕሱን ወይም ድክመቱን መቀበል እና ይቅርታ መጠየቅ ላይ ችግር የለበትም። ነገር ግን ሆኖ መገኘት ችግር አለው። ከአሁን በኋላ ህዝብን በንግግር ብቻ ማሳመን ይከዳል። የተናገሩትን ወደ ተግባር መቀየር ነው። እሱ ነው ህዝብን የሚያሳምን። ባለስልጣን የተባለ በሙሉ በየቦታው ፎቅ ከሚሰራ በህዝብ ልብ ውስጥ ፎቅ ይስራ። ፎቁ ውስጥ መኖር የሚቻለው አገር ሰላም ሲኾን ነው። ሁላችንም ለሰላም እንትጋ እላለው፤ ቸር ዋሉ የነገ ሰው ይበለን» ይኼም በዋትስአፕ የደረሰን መልእክት ነው። 

«ከወሬ የዘለለ አይደለም የኢሕአዴግ ፕሮጋንዳ ያለፈ ለውጥ አያመጣም ዜጎቺ እያለቁ ነው ወሬው ሰልቺቶናል» ተጨማሪ የዋትስአፕ መልክት ነው። 

የኢሕአዴግ የረቡዕ ምሽት መግለጫ በርካቶችን የማነጋገሩን ያኽል ከመግለጫው ቀደም ብሎም በግንባሩ አባላት ደጋፊዎች ዘንድ የጀመረው የማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ንትርኩ ቀጥሏል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ ግድያዎች ተጠያቂነትን ከአንዱ ቡድን ወደ አንዱ የማሸሽ፤ በግጭቱ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖችን በተመለከተ ለአንደኛው ወገን ተቆርቋሪ መስሎ ሌላኛውን ችላ ማለት፤ ሌላኛው ቡድን አንደኛው ላይ መዛት እና ማስፈራራት ጎልቶ ተንጸባርቋል። ዱላ ቀረሽ ንትርኩ እና የቃላት ጦርነቱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች አኹንም እንደቀጠለ ነው። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ደጋፊዎች መካከል የሚንጸባረቀውን ዱላ ቀረሽ እንካ ሰላንቲያ ወደ ሬዲዮ ማምጣቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝንም ቃል በቃል ቃላቱን ከማምጣት ተቆጥበናል።

ሌላው በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የመነጋገሪያ ርእስ የኾነው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋለው ተቃውሞ በተለይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርት የማቋረጣቸው ነገር ነው። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት መጀመሩ ቢገለጥም በተለይ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ተቋርጦ ውጥረቱ ማየሉ ተዘግቧል። ተቃውሞው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አልፎ ወደ ኹለተኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሁሉ መዛመቱን የሚያሳዩ ፎቶግራፍ እና ቪዲዮዎች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ታይቷል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ የማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የተስተጓጎሉ ቢኾንም በተለያዩ ዙራዙር መንገዶች የሚወጡ ፎቶግራፎች የተማሪዎችን ተቃውሞ ያሳያሉ። ተማሪዎች አደባባይ ወጥተው ከወገባቸው በላይ ራቁት በመሆን፣ አለያም ጥቁር ልብስ ለብሶ መሬት ላይ በጋራ በመንበርከክ እና በተለያየ መንገድ ተቃውሞዋቸውን ሲገልጡ የሚታይባቸው ፎቶግራፎችም በዚሁ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተሰራጭተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ