1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን ምርጫ ዉዝግብ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 16 2001

እንደጠቅላይ ሚንስትር የኻሜኒይን አክራሪ መርሕ ሲያፈፅሙ የነበሩት ሙሳቪ እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እሁለት የሚረግጠዉን የራፍሳንጃኒንን መርሕ መከተሉ አልከበዳቸዉም

https://p.dw.com/p/IWes
ምስል DW


የኢራን እስላማዊ አብዮት መርሕ አፍላቂ፣ የመርሁ አራማጅ-ገቢር አድራጊዎች መሪ የነበሩት የአያቶላሕ ሩሁላሕ ሙሳቪይ ኾሜኒይ የልጅ ልጅ ሰይድ ሁሴይን ኾሜኒይ «ኢራናዉያን አሁን ነፃነት ያስፈልጋቸዋል» ብለዉ ነበር አሉ-በ2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) አሉባዮቹ ካለበሉ የታላቁ መሪ ያብራክ ክፋይ ሌላም አክለዋል።የኮሜኒይዋ-ኢራን አይታ- የማታዉቀዉን አዲስ ሁነት ስታይ ሰንብታለች።አዲሱ ሁነት ለነሁሴይን ምኞት የስኬትም-የድቀትም ምልክት ከመሆን ግን በርግጥ አላለፈም።የአዲሱን ሁነት መሠረት-ምክንያት፤ የምልክቱን ተቃራኒነት ላፍታ እንቃኛለን።አብራችሁን ቆዩ።

ከትናንት በስቲያ ሳምንት ቅዳሜ-ጥቂት የቴሕራን ወጣቶች የጀመሩት የተቃዉሞ ሰልፍ ዕለት-በዕለት እየደመቀ-ሳምንቱ ዞሮ ሳይገጥም መቶ ሺዎችን-አሳተፈ።እንደ ጥንታዊ ሥልጣኔ እምብርትነቷ ፣እንደ አለም ሐያልነቷ፣ እንደ ፍልስፍና ሐይማኖት-ማዕከልነቷ፣ እንደ ሥልታዊ፣ ሐብታምነቷ በምታደርግ፤ በሚደረግባት የአለም ሒደት እንደሾረ፣ ትኩረቱ እንደታሰበ፣ አድናቆት ግራሞቱ እንደረበባት ዘመነ-ዘመናት አስቆጥራለች።


ርዕሠ-ከተማ ቴሕራን በሰላሳ አመት ታሪኳ አይታዉ በማታዉቀዉ ተቃዉሞ ሰልፈኛ ስትጥለቀለቅ ወትሮም ያልተለያት የአለም ትኩረት፣ አድናቆት ደመቀባት።የሰልፈኛዉ ብዛት-ድፍረት ፋርሳዊቷን ሐገር ለበጎ-ይሁን ለመጥፎ የአለም ማዕከል ያድርጋት እንጂ እስካለፈዉ አርብ የነበረዉ ተቃዉሞ፣ ጥያቄ፣ አቤቱታ ኢራን ለዘመናት እንደምትወቅበት ራሷን የመቀይር አለምን ፖለቲካዊ ሒደት የመበይን አለማ በርግጥ አልነበረዉም።ጥያቄቸዉ በምርጫዉ ተሸንፈዋል የተባሉት እጩ እንዲሾሙ ነዉ።ሚር ሆሴይን ሞሳቪ።

ተቃዉሚዎቹ ያወገዙት-የምርጫ ዉጤት አጭበርብረዋል ያሏቸዉን በፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲነጃድና ሹማምንቶቻቸዉን እንጂ-የእስላማዊቷ ሪፐብሊኳን የበላይ መሪዎችን አይደለም።
አቤቱታቸዉ አሕመዲነጃድ ከሥልጣን እንዲወገዱ፣እንጂ የእስላማዊቷ ሪፐብሊክ ሥርዓት እንዲለወጥ አይደለም።የተቃዋሚዎቹ ቁጥር እየበዛ፤ ጥያቄቸዉ እየጠነከረ ሲመጣ ሮብ ሕጋዊ ጉዳዮችን የመርመርና የመበየን ሥልጣን ያለዉ-«አቃቤ-ምክር ቤት» ከተሰጠዉ ድምፅ አስር በመቶ ያህሉን በድጋሚ ቆጥሮ-ቅዳሜ ብይን ሊሰጥ ቀጥሮ ነበር።

ተቃዋሚዎቹ አልተቀበሉትም።ቴሕራን ሐሙስንም በሰልፍ ግጭት አሳለፈች።አርብ። ተቃዉሞ ሠልፈኞች የታላቁን መሪ ታላቅ ብይን ለመስማት እረፍት አደረጉ።አቶላሕ አሊ ኻሜኒይ ብይን እንዲሰጡ ከመጠየቅ ባለፍ ለአመታት የታገሉ፣ የታሰሩ፣ የተገረፉ፣ የተጋዙለት ስምንት አመት እንደፕሬዝዳት ሃያ አመት እንደ ጠቅላይ መሪ የሚዘዉሩት ሥርዓት፤ ሥልጣናቸዉም እንደማይነካ እርግጠኛ ነበሩ።

ከሥርዓት፣ ሥልጣናቸዉ ተገዢዎች መካካል ብዙ የማይታመኑት የበጣም የታማኛቸዉ ሥልጣን በአደባይሰልፍ ለመቀማት ሲያሰሩ ገለልተኛ ሊሆኑ አይችሉም።

«የተመረጡት የእስላማዊዉ መንግሥት ፕሬዝዳት ያገኙት ድምፅ ሃያ-አራት ሚሊዮን ብቻ አይደለም።ይልቅዬ አርባ ሚሊዮን እንጂ።ሕዝቡ አምኗቸዋል።የሰዎች ድምፅን መዝረፍ ምግባራቸዉ እንዳልሆነ የሌሎቹ እጩዎች ደጋፊዎችም እርግጠኛ መሆን አለባቸዉ።የኢራን የሕግ ሥርዓት በሐገራችን ማጭበርበር እንዲፈፀም አይፈቅድም።11ሚሊዮን ያሕል ድምፅ ልዩነት ደግሞ ሊኖር አይችልም።»

ኻሜኒይ-ለፕሬዝዳት አሕመዲነጃድ ድጋፋቸዉን በግልፅ ሰጡ።አርብ። በዚሑ ንግግራቸዉ ተቃዋሚዎች የአደባባይ ሰልፋቸዉን ከቀጠሉ «ለሚፈሰዉ ደም» ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስጠንቀዉም ነበር።እስከ አርብ ለጠቅላይ መሪዉ አመራር ተገዢነታቸዉን ሲገልጡ የነበሩት የተቃዋሚዎቹ መሪ ሚር ሆሴይን ሞሳቪ ቅዳሜ «መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ ነኝ» አሉ።አረንጓዴ አርማቸዉን ያጠለቀ ደጋፊቸዉም አደባባይ ወጣ።የታላቁ መሪ ታላቅ ቃል በርግጥ ተደፈረ።

ሰልፈኛዉን የተቀበለዉ ግን-የፖሊስ ቆመጥ-ጥይት ነበር።አረንጓዴዉ አብዮት በትንሹ አስር ሕይወት ጠፋበት፥ከአራት መቶ ሐምሳ በላይ ሰዉ ታሰረበት።የታላቁ እስላማዊ አብዮት መስራች የአያቶላሕ ሩሑላሕ ኾሜኒይ መታሰቢያም በቦም ነጎደ።

የእስላማዊቷ ሪፐብሊክ መስራች የአቶላሕ ረሑላሕ ሙሳቪይ የልጅ ልጅ ሰይድ ሁሴይን ኾሜኒይ ከስድስት አመት በፊት አሉት የተባለዉን ብለዉት ከነበር፥-ነፃነት ይገባዋል ያሉት የኢራን ሕዝብ ነፃነቱን የሚያገኘዉ በአሜሪካዉያን ጣልቃገብነት ብቻ ቢሆን እንኳ ይሕን መቀበል ያለበት ይመስለኛል ነዉ ነበር አሉ የተባለዉ።በየሰበብ አስባቡ የሐያሉ አለም ትኩረት ያልተለያት ሐገር ዉዝግብ፥ግጭት አስተጋብኦት ገመገም ዞር የዋሽንግተን፥ ለንደን፥ በርሊን-ብራስልስ ርዕሥም ሆናለች።

«የኢራን አድሐሪያን ሐይላት ለዉጥ አራማጆቹን በቀላሉ ለመደፍለቅ የሚችልበት ቀላሉ መንገድ ለዉጥ አራማጆቹን የምታሳምፀዉ ዩ.ኤስ ነች ማለት ነዉ።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም በሳምንቱ ማብቂያ መንግሥታቸዉ ከሰላማዊ ሰልፈኛዉ ጎን እንደሚቆም በግልፅ አስታወቁ።

«ሰብአዊ መብትና የዜጎች መብት የሚነጣጠሉ አይደሉም።በዚሕም ምክንያት እኛ እንደ ጀርመን ለእምነትና ለአስተሳሰብ ነፃነታቸዉና ለመብታቸዉ ከቆሙ እና ሰላማዊ ሰልፍ ከሚያደርጉ ኢራናዉያንን ጎን እንደምንቆም እናሳዉቃለን።»

የሰልፈኛዉ ድፍረት፥ የጠቅላይ መሪዉ ማስጠንቀቂያ መጣስ፤ የአለም ትኩረት መሳቡም በኢራን የሰላሳ አመት ታሪክ ሆኖ የማያዉቅ አዲስ ለዉጥ ነዉ።ለዉጡ ግን ሁሴይ ኾሜኒይ አሉት የተባለዉን አይነት ነፃነት ማስገኘቱ ላሁኑ ከሩቅ ተስፋ በላይ ተጨባጭ መሰረት ምልክትም አለመኖሩ ነዉ ሐቁ።

ያሁኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኾሜኒይ የእስላማዊቱ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳት በነበሩበት ዘመን አሁን የጠቅላይ መሪዉን ቃል-ማስጠንቀቂያ የደፈረዉ ተቃዋሚ ሐይል መሪ ሚር ሆሴይን ሞሳቪ ድፍን ስምንት አመት አሊ ኻሜኒይን በታማኝነት ያገለገሉ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።

ኻሜኒይ ባለፈዉ አርብ ንግግራቸዉ ካሉት ሁሉ ሥላንድ ሹማቸዉ የጠቀሱት የአያቶላሁዎቹን የፖለቲካ ጥልፍልፍ ጠቋሚ ነበር።

«ራፍሳንጃኒን ሁሉም ያዉቀዋል።አብዮቱን ለራሳቸዉ የግል ጥቅም ማገበሻ አዉለዉታል ለመባሉ ምንም ማረጋገጪያ የለም።እኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከሳቸዉ ጋር የሐሳብ ልዩነት አለኝ።ይሕ ደግሞ እንግዳ አይደለም።ይሁንና ይሕን ልዩነት ሰዎች አጓጉል ሊተረጉሙት አይገባም።ከ2005 ምርጫ ጀምሮ ባሁኑ ፕሬዝዳትና በራፍሳንጃኒ መካካልም የአመለካከት ልዩነት አለ።ይሕ ያለ ነገር ነዉ።እነዚሕ ያመለካከት ልዩነቶች በተለያዩ መስኮች ይገለጣሉ።በዉጪ መርሕ፤ በማሕበራዊና በፍትሐዊ ጉዳዮች አፈፃፀም፥ እንዲሁም በባሕላዊ ጉዳዮችም ሊንፀባረቁ ይችላሉ።የአሕመዲነጃድ አስተሳሰብ እኔ ካለኝ ጋር ይቀራረባል።»

በ1989 ኻሜኒይ አያቶላሕ ሩሑላሕ ኾሚኒን ተክተዉ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን ሲረከቡ አቶላሕ ዓሊ ሐሺሚ ራፍሳንጃኒ ፕሬዝዳት ሆኑ።ሙሳቪ ደግሞ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር።ዓሊ አኽበር ሐሺሚ ራፍሳንጃኒ የሐይማኖትን ፍልስፍናን ከፖለተክኝነት ጋር አጣምረዉ ከያዙት ከብዙ ጓዶቻቸዉ ባንድ ነገር ይለያሉ።በሐብት።ቱጃርነታቸዉ ምክንያት ሆኖ-ከአክራሪዎቹ የላላ-ከለዘብተኞቹ የከረረ የፖለቲካ መርሕ አቀንቃኝ አድርጓቸዋል።

እንደጠቅላይ ሚንስትር የኻሜኒይን አክራሪ መርሕ ሲያፈፅሙ የነበሩት ሙሳቪ እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እሁለት የሚረግጠዉን የራፍሳንጃኒንን መርሕ መከተሉ አልከበዳቸዉም።ሙሳቪ ከሚንስትርነታቸዉ ጋር የሥነ-ሕንፃ (አርክቴክቸር) አዋቂነታቸዉ፥ ሰአይነታቸዉ ታክሎበት ያኔ የባሕል ሚንስትር ከነበሩት ከመሐመድ ኻታሚ ጋር ይወዳጃሉ።ወዳጅነቱ ወደ ፖለቲካ መርሕ ተጋሪነት አደገ።

ራፍሳንጃኒንን ለመተካት በ1997 በተደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሙሳቪ እንዲወዳደሩ ተከታዮቻቸዉ ጠይቀዋቸዉ ነበር።ይሁን ሥፍራዉን ለከኻታሚ ለቀቁ።በሁለት ሺሕ አምስት በተደረገዉ ፕሬዝዳታዊ ምርጫ ለመወዳደር ግን አመልክተዉ ነበር።የድሮ አለቃቸዉን ራፍሳንጃኒን ላለመፎካከር ሲሉ ተዉት።በምርጫዉ ራፍሳንጃኒ በማሕሙድ አሕመዲነጃድ ተሸነፉ።

ራፍሳንጃኒ እስከ ሁለት-ሺሕ አምስት ድረስ ምንም በማይታወቁት በቴሕራን ከንቲባ በአሕመዲነጃድ መሸነፋቸዉ ለእዉቁ፥ ለቱጃሩ፥ ለቀድሞዉ ፕሬዝዳት ከዉርደት የሚቆጠር አይነት ነበር።የአሕመዲነጃድ ድል የወግአጥባቂዎቹ አሸናፊነት ማረጋገጪያም ነበር።ዘንድሮ በተደረገዉ ምርጫ ለወጥ አራማጁ የቀድሞዉ ፕሬዝዳት መሐመድ ኻታሚ ለመወዳደር ባለፈዉ መጋቢት ተመዝግበዉ ነበር።

የጋራ ፍላጎት ያስተሳሰራቸዉ የራፍሳንጃኒ፥ ኻታሚ፥ ሙሳቪ የለዘብተኞች ጎራ አሕመዲነጃን ለመቋቋም ከኻታሚ ይልቅ ሙሳቪን ተገቢ ሰዉ ሥላደረጋቸዉ ኻታሚ ከእጩነት ወጡ።ሙሳቪ-ቀጠሉ። የሙሳቪን የምርጫ ዘመቻ አብዛኛ ወጪ የሸፈኑት ራፍሳጃኒ ናቸዉ።ዉጤቱ ቢያንስ እስካሁን ያዉ ዉዝግብ ግጭት መሆኑ ነዉ ቁጭቱ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ /ሂሩት መለሰ