1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን ኑኬልር -ዛቻ ፉከራዉ

ሰኞ፣ መጋቢት 3 2004

ወታደራዊ ጠበብት እንደሚሉት እስራኤል በቅርብ አመታት ከዩናይትድ ስቴትስ ያስገባቻቸዉ አንድ መቶ ሃያ-አምስት F-15i F-16 ዘመናይ ጄቶች-ለረጅም ርቀት በረራ ነዳጅ የሚቋጥሩበት ጋን ተገጥሞላቸዋል።ኢራን ላይ የሚዘረግፉት ግዙፍ-ቦምብም ታጭቋል።

https://p.dw.com/p/14Jcx
Mahmoud Ahmadinejad_s official website shows Iranian President Mahmoud Ahmadinejad (2-L) visiting visiting Tehran's nuclear reactor, Iran. Others are not identified. Iranian President Mahmoud Ahmadinejad on 15 February inaugurated three new nuclear projects, in a ceremony that was broadcast live on state television network IRIB. 'This is another huge step in Iran's nuclear technology and this path should be decisively continued, and all the shouting, threats and intimidations by the West should be ignored,' Ahmadinejad said at the ceremony. At the Iranian Atomic Organization in Tehran, Ahmadinejad witnessed the insertion of the country's first domestically made nuclear fuel rods into a medical reactor. EPA/PRESIDENTIAL OFFICIAL WEBSITE / HANDOUT HANDOUT EDITORIAL USE ONLY/NO SALES +++(c) dpa - Bildfunk+++
የኢራን የኑኬልር መርሐ-ግብርምስል picture-alliance/dpa

የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ጠንካራ መሪ ጆሴፍ ስታሊን ከጠበኛ ሐገራት የአንዱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሰላም ጉባኤ ካልተጠራ «ሞቼ እገኛለሁ» ብጤ ሙግት ከገጠመ፣ የሐገሩ መከላከያ ሚንስትር የዉጊያ ዝግጅቱን አጠናቋል ማለት ነዉ»።አይነት ብሒል ነበራቸዉ።የእስራኤል፣ መሪ፥ ሚንስትሮች፥ ተቃዋሚዎቻቸዉም ኢራንን ለመደብደብ ዛቱ እንጂ በርግጥ እንደራደር አላሉም። አሜሪካኖች ከአዉሮጶች ጋር ሆነዉ ከኢራን ጋር ከመደራደራቸዉ እኩል፣ የእስራኤሎችን ዛቻ፣ ፉከራ ያጋግማሉ።ኢራኖች ድርድርን በአፀፋ ዛቻ፣ እያጣፉ እንደገና ድርድር አሉ።ከእንግዲሕስ? ዲፕሎማሲ ወይስ ጦርነት።ላፍታ አብረን እንጠይቅ።



«በአሁኑ ደረጃ ይሕ (ዉዝግቡ) በዲፕሎማሲ ይፈታል ብዬ አምናለሁ።ይሕ የእኔ አምነት ብቻ አይደለም።የከፍተኛ የሥልላ ባለሥልጣኖቻችንም አመለካከት ነዉ።የእስራኤል ከፍተኛ የሥለላ ባለሥልጣናትም አመለካከት ነዉ።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ።ከኦባማ በፊት ግን መከላከያ ሚንስትራቸዉ ሌላ ብለዉ ነበር።
            
«ዩናይትድ ስቴትስ (ኢራን በመደብደቧ ሰበብ) ልትጠቃ ትችላለኝ።(በድብደባዉ ብንሳተፍም-ባንሳተፍም) ወደዱም ጠሉ እኛ መወገዛችን አይቀርም።»መከላከያ ሚንስትር ሊዮን ፓኔት።ባለፈዉ ወር።
                

«አብዮት» ብሎ ቃል ቴሕራን ሲገባ ምናልባት በማርክስ ኤንግልስ በኩል ሌኒን ያዉቁት እንደሁ እንጂ ሞስኮዎች ኋላ የተጠቀሙበትን፣ ገሚስ ዓለምን ያጥለቀለቀዉን ርዕዮተ-ዓለማዊ ፍቺ አልነበረዉም።የእስከዚያ ዘመኑ አብዛኛ ዓለም የሕዝብን የአዲስ ለወጥ አመፅን፣ የካፒታሊስቱን ሥልተ-ምርት አዲስነትን፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ለመግለጥ ይገለገልበት የነበረዉን ቃል ኢራኖች በ1906 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ያደረጉትን የፖለቲካ ሥርዓት ለዉጥ ገለጡበት።    

የጥንታዊቷ ሥልጡን፣ ታሪካዊት ሐገር ፖለቲከኞች «የፋርስ ሕገ-መንግሥታዊ አብዮት» ባሉት ሕዝባዊ አመፅ ፍፁም ፈላጭ ቆራጭ የነበረዉን ዙፋናዊ ሥርዓት ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ዘዉድ ቀይረዉ ምክር ቤታዊ ሥርዓትን አሰፈኑ።ዛሬ አብዛኛዉ ዓለም በጣሙን ፖለቲከኛዉ ካንጀቱም ሆነ ካንገቱ፥ እያደረገዉም ሆነ እየደፈለቀዉ ጠዋት-ማታ የሚምል የሚገዘትለትን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ኢራን ያወቀችዉም ያኔ ነዉ።

ግን አልቀጠለም።ኢራን ከስጋጃ ቅመማ ቅመም ሸቃጭነት ወደ ነዳጅ ዘይት ቱጃርነት፣ ከጥንታዊ ታሪክ ቅርስ ማከማቻነት ወደ ኮሚንስት፥ ካፒታሊስቱ ዓለም መራኮቻ ስልታዊ ሐገርነት፥ ወደ አረብ፥ እስራኤሎች መዳረሻ ወሳኝ የባሕር በርነት በተቀየረችበት በ1951 በተደረገዉ ምርጫ መሐመድ ሞሳድግሕ የተባሉ ፖለቲከኛ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ያዙ።ይሕ ለዋሽግተን-ለንደን ካፒታሊስቶች መርዶ ብጤ ነበር።

የለንደንና የዋሽግተን ገዢዎች ያዘመቷቸዉ ሰላዮች ለሁለት አመት ያሕል ባደራጁ፣ በመሩና ባቀነባበሩት መፈንቅለ መንግሥት በሕዝብ የተመረጡትን ጠቅላይ ሚንስትር አስወግዱ።የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስራች፣ የዲሞክራሲ ተቆርቋሪ፣ አራማጆቹ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን ጅምር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ጨፍልቀዉ ታማኛቸዉን እና የእስከዚያ ዘመኑን ሕገ መንግሥታዊ ንጉስ መሐመድ ሬዛ ሻሕ ፓሕሌቭን በፍፁም ፈላጭቆራጭ ገዢነት አነገሱ።ነሐሴ 1953።   


አሜሪካኖችን ከእንግሊዞች ጋር ያነገሷቸዉን ታዛዢያቸዉን ሥልጣን አጠናክረዉ ሥልታዊቷን ሐገርና ከነ-ነዳጅ ሐብቷ ለመቆጣጠር ቀድሞዉ ከወሰዷቸዉ እርምጃዎች ለሻሁ የኑክሌር ተቋም መመስረት አንዱ ነበር።በ1950 አጋማሽ የተጀመረዉ  የኑክሌር መርሐ-ግብር የኢራን ፖለቲካዊ ሥርዓት በሌላ አብዮት እስከተለወጠበት እስከ 1979 በአሜሪካኖች የሚሰራ በአሜሪካኖች የሚመራ ሥለነበር ለሰላማዊ አገልግሎት የሚዉልነቱን የጠረጠረ፣ የጠየቀም አልነበረም።ከነበረዉ የሰማዉ የለም።

የንጉስ ፓሕሌቭን ጨቋኝ ሥርዓት ያስወገዱት እስላማዊ አብዮተኞች ከጥቂት አመታት ፋታ በሕዋላ አሜሪካኖች የጀመሩትን የኑክሌር መርሐ-ግብር በሩሲያዎች ድጋፍ መቀጠላቸዉ ሲጋለጥ ግን የድፍን ዓለም ሠላም ሥጋት ሆነ።የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ከተጋለጠበት ጊዜ ጀምሮ የዋሽንግተን ለንደን፣ ብራስልስ መሪዎች ኢራንን ያለወገዙ፣ ያላስጠነቀቁ፣ ደግሞ በተቃራኒዉ ለድርድር ያልጋበዙበት ጊዜ የለም።ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ በቀደም ደገሙት።
            

«የኔ መርሕ ባለበት መያዝ አይደለም።መርሔ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራቸዉ ማገድ ነዉ። ምክንያቱም የኑክሌር መሳሪያ ካመረቱ በአካባቢዉ የጦር መሳሪያ እሽቅድምድም ይጭራል።የጦር መሳሪያ ያለማምረት አላማችንን ያዉካሉ።አሸባሪዎች እጅ ሊገባም ይችላል።»  

የዋሽግተን ቴላቪቭ መሪዎች ለድብደባ ያልዛቱበት ጊዜም ትንሽ ነዉ።የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር ኤሁድ ባራክ በርግጥ ከሻዉል ሞፋዝ፣ ከአሚር ፔሬስ ወይም ከሌሎች ቀዳሚዎቻቸዉ የተለየ ዓላማ፣ ፍላጎት፥ ተልዕኮም አይኖራቸዉ ይሆናል።የዛቻ ፉከራቸዉ ጥንካሬ ግን የጦር ዕቅድ፣ ዝግጅታቸዉን ያጠናቀቁ መከላከያ ሚንስትር አስመስሎ፥አስግቶም ነበር።
             
«በመላዉ ዓለም የሚገኙ ብዙ ባለሙያዎች፥ እዚሕ ያሉ ብቻ አይደሉም፥ እንደሚሉት እርምጃ ዓለመዉሰድ ዉጤቱ ኑክሌር የታጠቀች ኢራንን መፍጠር ነዉ።ኑክሌር እንዳትታጠቅ አሁን ከማገድ ይልቅ ኑክሌር የታጠቀችዉን ኢራን መቋቋም በጣም ዉስብስብ፥ በጣም አደገኛ እና ብዙ የደም ዋጋ ያስከፍላል።ሥለዚሕ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች እንደሚሉት «በኋላ ባይ፥ እጅግ የሚዘገይ» ሊሆን ይችላል።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ኢራንን በተመለተ «ሁሉም ነገር ጠረጳዛዬ ላይ» ነዉ የሚለዉን የፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽን ተወዳጅ ሐረግ-ይዉደዱ ይደጋግሙት እንጂ ጥቅል መርሕ እርምጃቸዉ ከቢል ክሊንተን ጠጠር ከቡሽ ለዘብ ያለነቱ ብዙ አላከራከረም።

ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን እስራኤልና ፍልስጤሞችን ለዘላቂዉ ለማስታረቅ በ1990ዎቹ አጋማሽ ያደረጉትን ጥረትን በነበረበት ካስቀሩት ዋና ዋና ምክንያቶች ለዘብተኛዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢን በድድሩ መሐል በአክራሪ አይሁድ ተገድለዉ ፥ በ1996ቱ ምርጫ አክራሪዉ ፖለቲከኛ ቢንያሚን ኔታንያሁ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን መያዛቸዉ፥ በጣሙን ግትር አቋማቸዉ አንዱ ነበር።

የክሊንተንን የፖለቲካ ፓርቲ የሚወክሉት፣ የክሊንተንን መርሕ ከክሊተን ጠንከር አድርገዉ የሚከተሉት ኦባማ ስልጣን በያዙ ማግስት ልዩ ትኩረት የሰጡት የእስራኤልና የፍልስጤም ድርድር  ቢያንስ እካሁን በነበረበት ነዉ የቀረዉ።

ኦባማ እስራኤልና ፍልስጤሞችን ለማስታረቅ እንደ ክሊንተን፣ ልዩ ትኩረት ሰጠተዉ በክሊንተን ባለቤት የበላይነት የነደፉት እቅድ፣ ካይሮ ድረስ ሔደዉ ለአረብ እስራኤሎች የሰጡት ተስፋ በዕቅድ ተስፋ ለመቅረቱ ትልቁ ምክንያት የኔታንያሁ ግትር አቋምነቱ ተንታኞችን አለነጋገረም።የአረብን የዘመነ-ዘመናት ሥርዓት የመነቃቀረዉ ሕዝባዊ አብዮት፥ ከስልሳ አመት በላይ ተስፋ እየተሰጠ የሚያደፈነዉን የፍልስጤሞችን ጥያቄ፥ በአዲስ መልክ ዳግም ማስነሳቱ አይቀርም።

ጥያቄዉን በቀጠሮ-እያሳደሩ ለማደፍን ከሚረዱት ዋና ዋና የአረብ መሪዎች ሙባረክ ዛሬ የሉም።እነ ንጉስ አብደላሕ የአማኑም ሆኑ የሪያዱ አንድም በየራሳቸዉ አለያም በየአካባቢያቸዉ ችግር ተወጥረዋል።የፍልስጤሞችን ጥያቄ ለማቆየት፥ የኦባማን ቃል-ተስፋ ባዶነት ለመደበቅ፥ ምናልባትም የኦባማ-ኔታንያሁን ልዩነት ለመሸፈን አብነቱ ከአስራ-ስምንት አመት በላይ የቆየዉን ዉዝግብ ዳግም መጫር ነዉ።ኢራን።
                
«ሆሎኮስትን የካደ፥ እስራኤልን ከካርታ ላይ ለማጥፋት የዛተና እስራኤልን ለማጥፋት የቆረጡ አሸባሪ ቡድናትን የሚረዳ ሥርዓት የኑክሌር ጦር መሳሪያ መታጠቁን ማንም እስራኤል መንግሥት አይታገሰዉም።ኑክሌር የታጠቀች ኢራን የእስራኤል የደሕንነት ጥቅምን ፍፁም ይቃረናል።የዚያኑ ያሕል የዩናይትድ ስቴትስን ብሔራዊ ጥቅምን ይቃረናል።»

ፕሬዳንት ኦባማ።ግን እኮ እስራኤል፥-
              
«ሁለት መቶ ሐምሳ የኑክሌር ቦምብ አላት።»

ይላል የሲ ኤን ኤንና የኒዊስዊኩ ጋዜጠኛ።የአሜሪካ-እስራኤል ፖለቲከኞች አይደሉም የአለም አዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፥የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥የአዉሮጳ ሕብረት፥የሌላዉም ሐገርና ተቋም ትልቅ ጉዳይ አይደለም።ምክንያቱ በግልፅ አልተነገረም።

ኢራንም ብትሆን የሚሰነዘርባት ዛቻ-ማስጠንቀቂያ እንጂ ጠላቶቿ ኑክሌር ሥለመታጠቃቸዉ ላሁኑ በግልፅ ያለችዉ የለም።በአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የኢራን አምባሳደር አሊ አስጋር ሶልታኒሕ በቀደም እንዳሉት ግን ኢራን ሲዛት፥ ሲፎከርባት የተባበሩት መንግሥታት ዝምታን መምረጡ አሳፋሪ፥ የራሱን ደንብም ተቃራኒ ነዉ።
              
«ሥለዚሕ፥-ይሕ በተደጋጋሚ የሚሰማዉን የጥቃት ዛቻ በተመለከተ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትም ሆነ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የገዢዎች ቦርድ አሳፋሪ ዝምታ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሕግንና በተለይ ደግሞ ዉሳኔ ቁጥር 433 የጣሰ በመሆኑ በጣም አሳሳቢ ነዉ።     

ብዙዎቹ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት አሁንም ዉዝግቡን በድርድር ማስወገድ ይቻላል የሚል እምነት አላቸዉ።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ በቀደም እንዳሉት ደግሞ እስራኤልም ሆነች ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን የኑክሌር ተቋማት ከመቱ መዘዙ በቀላሉ አይቆምም።
                  
ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማና ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ በቀድም ዋሽግተን ላይ ከተወያዩ በሕዋላ የሰጡት መግለጫ ባለፈዉ ወር ከሁለቱ ሐገራት መከላከያ ሚንስትሮች የተሰማዉ ማስጠንቀቂያ ያጫረዉን ሥጋት በመጠኑም ቢሆን ቀንሶታል።«ሰባትዮሽ» የሚባለዉን ድርድር ለመቀጠል በላጉዳዮች መስማታቸዉም ለጊዜዉም ቢሆን ጥሩ ተስፋ ነዉ።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢንያሚን ኔትንያሁ እንዳሉት ግን የእስራኤል ትግስት ከሳምንታት ወይም ከወራት አልፎ ዓመት የሚቆይ አይደለም።
      
ወታደራዊ ጠበብት እንደሚሉት እስራኤል በቅርብ አመታት ከዩናይትድ ስቴትስ ያስገባቻቸዉ አንድ መቶ ሃያ-አምስት F-15i F-16 i ዘመናይ ጄቶች-ለረጅም ርቀት በረራ ነዳጅ የሚቋጥሩበት ጋን ተገጥሞላቸዋል።ጄቶቹ ኢራን ላይ የሚዘረግፉት ግዙፍ-ቦምብም ታጭቋል።እስራኤል የምታመርታቸዉ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖችም ረጅም ርቀት፥ መጓዝ፥ ከፍተኛ ሚሳዬል መሽከም እንዲችሉ ተደርገዉ ተሻሽለዋል።

አዉሮፕላኖቹ ኢራን የሚደርሱበት አቅጣጫ ግን ፥በሳዑዲ አረቢያ፥ በኢራቅ-ሶሪያ፥ በሜድትራኒያን ባሕር በኩል፥ ወይስ በሰወስቱም አለየም።እስራኤል ከዚሕ ቀደም የኢራቅንና የሶሪያን ተጠርጣሪ የኑክሌር ተቋማት መትታለች።ሁለቱም ተቋማት አንዳድ ሥፍራ የነበሩ ነበሩ።የኢራን ግን የተበታተነ ነዉ።ወደ ሃያ አምስት።ዘመናዮቹ አዉሮፕላኖች ኢራን-ደርሰዉ የሚሰሩትን ሰርተዉ መመለስ-አለመመለሳቸዉም አጠያያቂ ነዉ።

ኔትንያሁ በቀደም-ዋሽግተን ላይ ያሉት ግን ሊዘነጋ አይገባም።«እኛ እናንተ ነን።እናንተ ደግሞ እኛ»

አንድም ሁለትሞቹ ሐገራት በኢራኑ ዘመቻም አንድም-ሁለትምነታቸዉን ካረጋገጡ ግን-አጠያያቂዎቹ ጉዳዮች ወጥ መልስ ያገኛሉ።የአፀፋ፦ መዘዙ ምንነትም-እንዲሁ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ
            














   
 


 


 

President Barack Obama, accompanied by Israeli Prime Minister Benjamin Netanyahu, delivers a statement outside the Oval Office of the White House in Washington, Wednesday, Sept. 1, 2010. (AP Photo/Pablo Martinez Monsivais)
«እኛ እናንተ ነን።እናንተ ደግሞ እኛ»ምስል AP
Iranian President Mahmoud Ahmedinejad flanked by a Turkish, left, and an Iran flag as he poses for cameras before a meetIing with Turkey's Prime Minister Recep Tayyip Erdogan in Istanbul, Turkey, Wednesday, Dec. 22, 2010.(AP Photo/Tolga Bozoglu, Pool)
ፕሬዝዳንት አሕመዲንጃድምስል AP