1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን ኑክሌር ድርድር

ሰኞ፣ ኅዳር 2 2006

ባለፈዉ ሐምሌ-ሐሰን ሩሐኒ ለፕሬዝዳትነት ሲመረጡ ፕሬዝዳንት ኦባማ ከአራት ዓመት በፊት ለዓለም ሠላም ከገቡት ብዙ ቃል-ኢምንቱን እንኳ ገቢር አላደረጉም።ከሰጡት አያሌ ተስፋ-አብዛኛዉ ከተስፋ አላለፈም።ያም ሆኖ ኦባማ ሲሆን እራሳቸዉን ካልሆነም ቢል ክሊንተንን እንጂ ጆርጆ ቡሽን እንዳልሆኑ አስመስክረዋል።

https://p.dw.com/p/1AFWW
U.S. Secretary of State John Kerry (2nd L), EU foreign policy chief Catherine Ashton (C), and Iranian Foreign Minister Mohammad Javad Zarif (2nd R) attend the third day of closed-door nuclear talks at the Intercontinental Hotel in Geneva November 9, 2013. France warned of serious stumbling blocks to a long-sought deal on Iran's nuclear programme as foreign ministers from Tehran and six world powers extended high-stakes negotiations into a third day on Saturday to end a decade-old standoff. REUTERS/Jean-Christophe Bott/Pool (SWITZERLAND - Tags: POLITICS ENERGY)
ድርድሩምስል Reuters/Jean-Christophe Bott

ሁለት ሺሕ ዘጠኝ።(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) አንደበተ-ርቱዑ፥ ክልሱ፥ ፖለቲከኛ የልዕለ-ሐያሊቱን ሐገር ሐያል ሥልጣን ሲይዙ የቀደሚያቸዉን መርሕ-ምግባር ተቃርነዉ ከዋሽግተን ያንቆረቆሩት የሠላም ተስፋ ለቴሕራን አያቶላሆች የተለመደ «የጠላት መሰሪ መልዕክት» ነበር።ነሐሴ ሁለት-ሺሕ አስራ-ሰወስት።እንደአያቶላሆቹ-ጥምጥማሙ፥ጢማሙ ፖለቲከኛ የኢራንን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን ሲያዙ ከቀዳሚያቸዉ ተቃርነዉ ለእርቀ-ሠላም-ቃል-ሲገቡ ለዋሽግተኖች «የአያቶላኸሆች ማታለያ»-ነበር ትርጉሙ።ሰሞኑን ከዋሽግተን-ቴሕራን፥ የሚሰማዉ፥ ዤኔቭ-ብራስልስ የሆነዉ ግን በነበር ከሚዘከረዉ ጥርጣሬ፥ ግምት፥ የሚቃረን እዉነት ነዉ-ተስፋ።

ንጉስ መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ ሻሕ ይመሩት የነበረዉ የኢራን ዘዉዳዊ አገዛዝ በ1960ዎቹ የኑክሌር መርሐ-ግብር ሲጀምር በዋሽግተኖች ይሁንታ፥ ድጋፍ ና ትብብር ሥለ-ነበር ለምዕራባዉያን ዓላማዉ ሠላማዊ፥ ጅምሩም ተገቢ ነበር።

ሻሁ የጀመሩትን መርሐ-ግብር ሻሁን ከሥልጣን ያስወገዱት እስላማዊ አብዮተኞች በሩሲያ ድጋፍና ትብብር መቀጠላቸዉ በሁለት ሺሕ ሁለት ሲታወቅ-በምዕራባዉያን ዘንድ ያደረዉ ጥርጣሬ ወትሮም ጠመንጃ ያመዘዘዉን ርዕዮተ-ዓለማዊ ጠብ፥ ዉዝግብ ለማጋጋም ጥሩ መደላድል ሆነ።እርግጥ ነዉ አያቶላሕ ሩሑላሕ ኾሜይኒይ የመሯቸዉ የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች የቴሕራንን ቤተ-መንግሥት ከተቆጣጠሩበት ከ1979 ጀምሮ ሥር የሠደደዉ የቴሕራን እና የዋሽግተኞች ጠብ፥ ጥላቻ የጅ አዙር ቁርቁስ-ዛሬም አልበረደም።

ከሁለት ሺሕ ሁለት ጀምሮ ርዕዮተ-ዓለማዊዉን ጥላቻ ጠብ፥ ቁርቁስ ለማጋጋም ዋና መሳሪያ የሆነዉ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ዉዝግብን ለማስወገድ የዋሽግተን-ብራስልስ፥ የቴሕራን-ሞስኮ ተወካዮች ባለፉት ጥቂት ወራት ባደረጉት ድርድርም ከሁነኛ ሥምምነት ላይ አልደረሱም።የበጎ ተስፋ ጭላንጭል መፈንጠቁን ግን ሁሉም አረጋግጠዋል።

«ወደ ዤኔቭ ሥንመጣ ከነበረዉ ይልቅ አሁን ከዤኔቭ ሥንሰናበት ይበልጥ መቀራረባችን ምንም አያጠያይቅም።ከጥሩ ሥራ እና እምነት ጋር በሚቀጥሉት ሳምንታት በርግጥ ግባችንን መምታት እንችላለን።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ትናንት።የኢራኑ አቻቸዉ መሐመድ ጀዋድ ሳሪፍም ተስፋዉን ይጋራሉ።

«ዝርዝር ጉዳዮችን ሥናነሳ የሐሳብ ልዩነት መታየቱ የማይቀር ነገር ነበር።ይሕ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር።(ስምምነት ባለመደረሱ) በጭራሽ አልተናደድኩም።ጥሩ ስብሰባ ነበር።እንደሚመስለኝ ሁላችንም በተመሳሳይ ርቀት ላይ ነን።ይሕ ጠቃሚ ነዉ።በሚቀጥለዉ ጊዜ ስንገናኝ ወደ ፊት እንድንራመድ ጥሩ ግብዓት ይሆነናል።»

በሁለት ሺሕ-ስምንት የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲካ አንፀባሪቂ ኮኮብ ሴናተር ባራክ ሁሴይን ኦባማ ዳግማዊ ለፕሬዝዳትነት ሲወዳደሩ የሐይለኛዉ ኢራን መጅሊስ (ምክር ቤት) አፈ-ጉባኤ ዓሊ ላርጃኒ ሮይተር ዜና አገልግሎት እንደጠቀሰዉ «ምንም እንኳን የዩናይትድ ስቴትስ መርሕ እንደማይቀየር ብናዉቅም ኦባማ ቢያሸንፉ ደስ ይለኛል።» ብለዉ ነበር።

የኢራን ፖለቲከኞች ርዕሠ-ርዑሳን አያቶላሕ ኻሜኔይ ግን « ለአሜሪካ የሚወስነዉ ማን እንደሁ አላዉቅም» አሉ እና «ፕሬዝዳንቱ ነዉ? ምክር ቤቱ ነዉ? ወይስ ከመጋረጃ ጀርባ ያሉት ሐይላት?» ጠየቁ።

ባለፈዉ ሐምሌ-ሐሰን ሩሐኒ ለፕሬዝዳትነት ሲመረጡ ፕሬዝዳንት ኦባማ ከአራት ዓመት በፊት ለዓለም ሠላም ከገቡት ብዙ ቃል-ኢምንቱን እንኳ ገቢር አላደረጉም።ከሰጡት አያሌ ተስፋ-አብዛኛዉ ከተስፋ አላለፈም።ያም ሆኖ ኦባማ ሲሆን እራሳቸዉን ካልሆነም ቢል ክሊንተንን እንጂ ጆርጆ ቡሽን እንዳልሆኑ አስመስክረዋል።

ኦባማ ሲመረጡ ዋሽግተን ላይ ነጥራ-ቴሕራን ያረፈችዉ ኳስ ግን ሐምሌ ላይ ከቴሕራ ተለግታ-ዋሽግተን አረፈች።ከአያቶላኾቹ አመራር ተለይተዉ የማያዉቁት-ግን ለዘብተኛዉ፥ እስልምናን ያጠኑት ግን ዘመናዊዉ ሕግን ስኮትላንድ የተማሩት በሳል ፖለቲከኛ የኢራንን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን ሲይዙ የገቡት ቃል፣ የሰጡት ተስፋ ለብዙዎቹ የዋሽግተን ፖለቲከኞች ከተለመደዉ የቴሕራን አያቶላሆች ፕሮፓንጋንዳ የተለየ አልነበረም።ሰዉዬዉ ግን ሲቀርብ እራሳቸዉን፥ ሲርቅ-መሐመድ ሐታሚን እንጂ ማሕሙድ አሕመዲኒጃዲን እንዳልሆኑ ለማሳየት ጊዜ አልፈጁም።

ርዕሠ-ርዑሳን ኻሜኔይም «በድርድሩ መለሳለስ አስፈላጊ ነዉ» ብለዉ ሩሐኒ የፈለጉትን ፈቀዱላቸዉ። በርሊን በሚገኘዉ የሳይንስ እና የፖለቲካ ጥናት ተቋም የኢራን ጉዳይ ባለሙያ ቫልተር ፖሽ እንደሚሉት የሩሐኒ የመጀመሪያ ርምጃ ባለሙያዎችን መሠብሰብ ነበር።

«ሩሐኒ በእዉቅ ባለሙያዎች የተሞላ ቡድን መሠረቱ።እና ኢራን ከልቧ እና ከምር መደራደር እንደምትፈልግ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ማሳየት ቻሉ።»

ሩሐኒ ሥልጣን የያዙት የቴሕራን መሪዎች በአሕመዲኒጃድ ዘመን ሐገራቸዉን ክፉኛ የጎዳዉ ተተከታታይ ማዕቀብ የሚወገድበትን ብልሐት በሚያሰላስሉበት ወቅት ነዉ።በርግጥ ዩናይትድ ስቴትስ ለሰወስት አስርታት ያፀናቸዉ ማዕቀብ መጀሪያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ ሐቻምና በአዉሮጳ ሕብረት ማዕቀብ ሲጠናከር በጋዝና በነዳጅ ዘይት ሐብት የተንበሻበሸችዉን ሐገር ምጣኔ ሐብት አሽመድምዶታል።ኢራን እስከ ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ድረስ በቀን 2.2 ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ ዘይት ለዉጪ ትሸጥ ነበር።አምና መስከርም ላይ ለዉጪ ገበያ መሸጥ የቻለችዉ በቀን ስምንት መቶ ሥልሳ ሺሕ በርሚል ብቻ ነበር።

ከአትላንቲክ ማዶ ደግሞ ወቅቱ ፕሬዝዳት ኦባማ ለፕሬዝዳትነት መወዳደር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ፕሬዝዳት ቡሽ ያወደሙ፥ ያመሰቃቀሉትን ምጣኔ ሐብት፥ ለማስተካከል፥ ከሁሉም በላይ ሰላም ባጣችዉ ዓለም ሠላም ለማስፈን በየደረሱበት የገቡት ቃል-ተስፋ ጨርሶ ባይሞት-የሚያጣጥርበት ጊዜ ነዉ።

የኦባማ መስተዳድር ከወደ ቴሕራን ሽዉ ያለዉን የድርድር ተስፋ-መጠቀም የመርሕ ጉዳይ ብቻ አይደለም።በሚያጣጥረዉ ቃል፥ ተስፋ ላይ ቢያንስ አንድ ሥፍራ-ላጭር ጊዜም ቢሆን ነብስ የመዝረት፥ በቃለ-አባይነት ከመወቀሰስ መዳኛ ምክትም ብጤም ጭምር ነዉ።

እና ትንኝም ለሆዷ፥ ዝሆንም ለሆዱ---ዉሐ እንጠጣ ብለዉ ወደ ወንዝ ወረዱ---» እንዲል ኢትዮጵያዊዉ ባለ ቅኔ «የዝሆኗ-ዋሽግተን» ትልቅ መሪ እና «የትንኟ ኢራን» አዲስ መሪ ከ1979ቱ እስላማዊ አብዮት ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥልክ ተነጋገሩ።ሁለቱም መሪዎች በኒክሌር መርሐ-ግብር ሰበብ የተጋጋመዉን ዉዝግብ በድርድር ለማስወገድ እንደሚሹ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሳይቀር በግልፅ አስታወቁ።መስከረም ነበር-ይሕ የሆነዉ።

በወር ዕድሜ ዋሽግተን የለንደን፥ የፓሪስ፥ እና የበርሊን ወዳጆችዋን አስከትላ-ኢራን አወዛጋቢ የኑክሌር መርሐ-ግብሯን እንድታቆም ለማግባባት፥ ቴሕራን ባንፃሩ የሞስኮና የቤጂንግ ትላልቆችን ተከትላ፥ የተጣለባት ማዕቀብ በከፊልም ቢሆን ለማስነሳት አልማ፥ ሁሉም «ሠላም» ብለዉ---ወይም በብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በዊሊያም ሔግ ቋንቋ ከዓለምን እጅ ያፈተለከዉን አጋጣሚ ለመጠቀም ወደ ዤኔቭ ወረዱ።ወይም ወጡ።


«በጣም እንገነዘበዋለን።እዚሕ ያለነዉ ሚንስትሮች በሙሉ በዚሕ ድርድር የሆነ ጥሩ ተጨባጭ ክስተት መፈጠሩን እናዉቃለን።በዚሕ ድርድር ብዙ ተጨባጭ እዉነታዎች ታይተዋል።ይሕን አጋጣሚ እና ሁኔታ በመጠቀም ከስምምነት ላይ ለመድረስ ሁላችንም የምንችለዉን ሁሉ ማድረግ አለብን። ከዓለም እጅ ለረጅም ጊዜ ሲያሟልጭ የነበረዉን፥ዓለም ለረጅም ጊዜ መድረስ ካቃተዉ ስምምነት ለመድረስ መጣር አለብን።»

ትናንት የተጠናቀቀዉ ሁለተኛዉ ዙር ድርድር ከስምምነት ላይ ይደርሳል የሚል ተስፋ-ተጥሎበት ነበር።ድርድሩም እንደ ከዚሕ ቀደሙ የአምባሳደሮች፥ ወይም የልዩ ተደራዳሪዎች ብቻ አልነበረም። የሚንስትሮች ጭምር እንጂ።የተፈለገዉ ስምምነት በርግጥ አልተደረገም።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ወይዘሮ ካትሪን አሽተን እንዳሉት ግን ያሁኑ ድርድር፥ ያገራቸዉ ልጅ ለረጅም ጊዜ ከዓለም እጅ የሚያፈተልክ እንዳሉት አይነት አይሆንም።ምክንያቱም በአሸተን አገላለፅ በርካታ ተጨባጭ እርምጃ ታይቷልና።

«በርካታ ተጨባጭ እርምጃዎች ተወስደዋል።ትንሽ ልዩነቶች ግን እንዳሉ ናቸዉ።እዚሕ መጥተዉ እኛን የተቀየጡትን ሚንስትሮች ማመስገን እንፈልጋለን።የሲዊስ እና የተመድ አስተናጋጆቻችንን ማመስገን እንፈልጋለን።ሚንስትር ዛሪፍ እና እኔ ከኢራን ተደራዳሪ ቡድን፥ እና ከE3+3 የፖለቲካ ሐላፊዎች ጋር ሕዳር ሃያ-እዚሕ ዳግም እንገናኛለን።»

የሞስኮ ቤጂንግ ፖለቲከኞች የእስካሁኑን ዉጤት አድንቀዋል። የተባበሩት መንግሥታት የአዉቶሚክ ተቆጣጠሪ ባለሥልጣን (IAEA) የበላይ ሐላፊ ዩኪያ አማኖ ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ቴክኒካዊ ያሉትን ለመፈራረም ቴሕራን ናቸዉ።ፓሪሶች ግን የዋሽግተን፥ ለንደን ወዳጆቻቸዉን ያክል እንኳ አልተደሰቱም።

ከጄኔቭ-ብራስልስ፥ ከዋሽግተን ቴሕራን የሚንቆረቆረዉ የሠላም ተስፋ፥ የስምምነት ቃል-ቀጠሮ ለእስራኤል መሪዎች የሚጥም አልሆነም።ምዕራባዉያን ሐገራት በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ የጣለችዉን ማዕቀብ እንዳታነሳ የእስራኤል ፖለቲከኞች ፖለቲካዊ ዘመቻ-ብጤ ጀምረዋል።በዚሕም ሠበብ አንዳድ ታዛቢዎች እንዳሉት የከንግዲሁ ልዩነት የኢራን-ምዕራቦች ወይም የምዕራብ-ምስራቆች ከመሆን ይልቅ የምዕራብ-ምዕራቦች ልዩነት ነዉ-የሚሆን።ሥለ ማሕደረ ዜና ዝግጅት አስተያየት፥ የሰጣችሁንን አመሰግናለሁ።ወደፊትም አስተያየታችሁን፥ ማሕደረ ዜና ቢቃኘዉ ጥሩ ነዉ ብላችሁ የምታስቡትን ርዕሠ፥ በደብዳቤ፥ በስልክ፥ በኢሜይል፥ እና በኤስ ኤም ኤስ ላኩሉን።

U.S. Secretary of State John Kerry steps aboard his aircraft in Geneva, November 10, 2013. REUTERS/Jason Reed (SWITZERLAND - Tags: POLITICS)
ኬሪምስል Reuters
(L-R) British Foreign Secretary William Hague, Iranian Foreign Minister Mohammad Javad Zarif, Germany's Foreign Minister Guido Westerwelle and EU foreign policy chief Catherine Ashton attend the third day of closed-door nuclear talks at the Intercontinental Hotel in Geneva November 9, 2013. France warned of serious stumbling blocks to a long-sought deal on Iran's nuclear programme as foreign ministers from Tehran and six world powers extended high-stakes negotiations into a third day on Saturday to end a decade-old standoff. REUTERS/Jean-Christophe Bott/Pool (SWITZERLAND - Tags: POLITICS ENERGY)
የኢራኑ ዉጉሚ ከምራባዉያን አቻቸዉ ጋርምስል Reuters/Jean-Christophe Bott
U.S. President Barack Obama delivers remarks on the end of the U.S. government shutdown in the State Dining Room of the White House in Washington, October 17, 2013. The U.S. Congress on Wednesday approved an 11th-hour deal to end a partial government shutdown and pull the world's biggest economy back from the brink of a historic debt default that could have threatened financial calamity. REUTERS/Jason Reed (UNITED STATES - Tags: POLITICS BUSINESS EMPLOYMENT)
ምስል Reuters
NEW YORK, NY - SEPTEMBER 24: Iranian President Hassan Rouhani addresses the U.N. General Assembly on September 24, 2013 in New York City. Over 120 prime ministers, presidents and monarchs are gathering this week for the annual meeting at the temporary General Assembly Hall at the U.N. headquarters while the General Assembly Building is closed for renovations. (Photo by Brendan McDermid-Pool/Getty Images)
ምስል Getty Images

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ