1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ስምምነት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7 2007

የዓለም ልዕለ ኃያላን አገራት ኢራን የኑክልየር ቦምብ እንዳታመርት ለማከላከል እና በዚሁ መርሐ-ግብርዋ ሰበብ በአገሪቱ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደረሱ። ስምምነቱን የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር «ታሪካዊ« ብለው ሲያሞካሹት የአውሮጳ ህብረቱ ተደራዳሪ ደግሞ «የተስፋ ምልክት» ብለውታል።

https://p.dw.com/p/1FyXv
Atomgespräche in Wien abgeschlossen
ምስል picture-alliance/dpa/H. Neubauer

[No title]

ከ18 ቀናት እልህ አስጨራሽ ድርድር በኋላ የዓለም ልዕለ ኃያላን አገራት ለ13 አመታት የዘለቀው የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር እሰጥ አገባ በቪየና መቋጫ ተበጅቶለታል። ስምምነቱ ከኢራንም ይሁን የልዕለ ኃያላኑ አገራት መሪዎች ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል።የአሜሪካኑ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የኢራን የመንግስት ቴሌቭዥን ጣቢያ በቀጥታ ባስተላለፈው ንግግራቸው የስምምነቱን አንኳር ስኬቶች ጠቃቅሰዋል።

«በዚህ ስምምነት ምክንያት ኢራን የኑክሌር ቦምብ ለመስራት የሚያገለግለውን ማዕድኑን ዩራኒየምና ፕሉቶኒየምን ማብላላት ታቆማለች። በዚህ ስምምነት ምክንያት ኢራን ቦምብ ለመስራት የሚያስፈልገውን ዩራኒየም ለማበልጸግ ያዘጋጀቻቸውን ግዙፍ መሳሪያዎች በማስወገድ ቋሚ ዓለም አቀፍ ክትትል በሚኖርበት ቦታ ታስቀምጣለች።»

Wien Atomgespräche mit dem Iran Zarif
ምስል picture-alliance/AP Photo/C. Barria

በምስራቃዊ ኢራን የናታንዝ ከተማ አገሪቱ የኑክሌር መርሐ-ግብር መጀመሯን የምዕራባውያን የስለላ ተቋማትና የኢራን ተቃዋሚዎች በጎርጎሮሳዊው 2002 ዓ.ም. ማጋለጣቸውን ተከትሎ የተጀመረው የሁለቱ ጎራ ፍጥጫ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ዘልቋል። ኢራን በናታንዝ ከተማ የአቶሚክ የጦር መሳሪያ ለመስራት የሚያስችል ዩራኒየም ማብላላት መጀመሯን ተከትሎ ድርድር የጀመሩት ጀርመን፤ ታላቋ ብሪታኒያና ፈረንሳይ ነበሩ። ኢራን በጎርጎሮሳዊው 2003 ዓ.ም. ዩራኒየም የማብላላቱን ሂደት ብታቋርጥም ከሶስት ዓመት በኋላ ወግ አጥባቂው ፕሬዝዳንት አህመዲን ነጃድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ እንደገና መጀመሯ ለምዕራባውያን የራስ ምታት ሆኖ ነበር።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ፤ሩሲያና ቻይናን ጨምሮ ኃያላኑ አገራት ከኢራን ጋር ያደረጓቸው ድርድሮች ስኬታማ አልነበሩም።

የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ፌዴሪካ ሞግሄሪኒ አሁን በስኬት የተቋጨው ድርድር ለአመታት የዘለቀውን አለመተማመን መፍትሄ ከመስጠት ያለፈ ትርጉም አለው ብለዋል።

«አሁን የምንወስደው ውሳኔ በኢራን የኑክሌር መርሓ-ግብር ላይ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ያለፈ ትርጉም አለው። በዓለም አቀፍ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና ዲፕሎማሲና መተባበር ለአመታት የዘለቀ ውጥረት ለመፍታት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው።»

159 ገፆች ያሉት ስምምነት ለተግባራዊነቱ አምስት የጊዜ ሰሌዳዎች ተይዘውለታል። በስምምነቱ መሰረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቆጣጣሪዎች የኢራንን የጦር ሰፈሮች የመፈተሽ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ኢራን ስምምነቱን ስትፈርም የተጣሉባት ማዕቀቦች የሚነሱ ቢሆንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጦር መሳሪያ ግዢና ሽያጭ ማዕቀብ ለአምስት አመታት፤ የሚሳኤል ማዕቀብ ደግሞ ለስምንት አመታት የሚቆዩ ይሆናል። ኢራን ሁለተኛው ማዕቀብ እንዲነሳ ጥያቄ አቅርባ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ መቅረቱን ሬውተርስ ዘግቧል። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሃመድ ዣቫድ ዛሪፍ ስምምነቱን «ታሪካዊ» ብለውታል።

Atomverhandlungen mit Iran in Wien
ምስል picture alliance / landov

« ይህ ታሪካዊ ወቅት ነው ብዬ አምናለሁ። ለሁላችንም ምሉዕ ያልሆነ ስምምነት ላይ እየደረስን ነው። ቢሆንም ልናሳካው የምንችለው እና ለሁላችንም ጠቃሚ ስኬት ነው።»

የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ወደ ኢራን ለመጓዝ አሳብ እንዳላቸው መናገራቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በሚቀጥሉት 60 ቀናት በስምምነቱ እጣ ፈንታ ላይ ይወስናል ተብሏል። ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ኢራን ስምምነቱን ከጣሰች ማዕቀብ የመጣል አማራጭ እንደሚኖር ተናግረዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን «ታሪካዊ ስህተት ተፈጸመ» ሲሉ የኃያላኑን ውሳኔ ወቅሰዋል።


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ