1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 1 2004

ድንገተኛ ከባድ ትኩሳት፤ የሰዉነት ድካም፤ ራስ ምታት፤ ማስመለስ እና የኩላሊት ህመምን ያስከትላል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተ ወዲህ 36ዓመታት ቢቆጠሩም እስካሁን መድሃኒትም ሆነ ክትባት አልተገኘለትም። ኢቦላ ቫይረስ። ኢቦላ የያዛቸዉን አለመንካት ይመከራል።

https://p.dw.com/p/15lDR
ኢቦላ ቫይረስምስል picture-alliance/ dpa

የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ዑጋንዳ ዉስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየዉ ኢቦላ ቫይረስ በወቅቱ የ224 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ዘንድሮ ደግሞ ሰሞኑን በዚችዉ ሀገር ምዕራባዊ ግዛት ተቀስቅሶ 16 ሰዎችን ገድሏል። ስያሜዉን በሰሜን ዴሞክራቲክ ኮንጎ ከሚገኘዉ ኤቦላ ወንዝ የወሰደዉ ተላላፊ በሽታ ለመጀመሪያ ከታየበት ከዛሬ 36ዓመት አንስቶ በተደጋጋሚ የተከሰተዉ አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ። የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመዉ ኮት ዴቬዋር እና ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ አንዴ፤ ጋቦን ሁለቴ፤ ዑጋንዳን ጨምሮ ሱዳንና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ግን ከሁለቴ አልፎ እያሰለሰ፤ በተደጋጋሚ እየተቀሰቀሰ ለበርካቶች ህልፈተ ህይወት ምክንያት ሆኗል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢቦላ የተሰኘዉ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየዉ በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ1976ዓ,ም ነሐሴ ወር ማለቂያ ላይ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ከዚያም ሱዳን ላይ ነዉ።

Ebola Uganda 2007
ኢቦላ ዑጋንዳ ዉስጥምስል Getty Images

በወቅቱ ኮንጎ ዉስጥ 318 ሰዎች ላይ ተገኝቶ የ280ዎቹን ህይወት ሲቀጥፍ፤ ሱዳን ዉስጥ ደግሞ 284 ሰዎችን ይዞ 151ዱ አልተረፉም። በቫይረሶች አማካኝነት መድማትን ጨምሮ ከፍተኛ ህመም የሚያመጣዉ ይህ ከሰዉ ወደሰዉ የሚተላለፍ በሽታ ድንገተኛ ከባድ ትኩሳት፤ የሰዉነት ድካም፤ ራስ ምታት፤ ማስመለስ እና የኩላሊት ህመምን ያስከትላል። በዚህ በሽታ የተያዘ ሰዉ የመትረፍ እድሉ አነስተኛ እንደሆነ ነዉ የዓለም የጤና ድርጅት የሚገልፀዉ። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ታሪክ ያሳራቪች  ስለበሽታዉ ምንነት ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፤

«እንደተገለፀዉ ከሰዉ ወደሰዉ የሚተላለፍ የበሽታ ዓይነት ነዉ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከታወቀ ወዲህ በተለያዩ ምዝን የአየር ርጥበቱ ከፍተኛ በሆነባቸዉ የአፍሪቃ ሀገሮች ተከስቷል። በሽታዉ በቫይረሱ የተያዘን ሰዉ በመንካት ይተላለፋል። መንካት ሲባል አንዳንዴ የታማሚዉን አካል በመንካት ብቻ ሊሆንም ይችላል፤ ሆኖም ግን አብዛኛዉን ጊዜ ከታማሚዉ ግለሰብ በሚወጣዉ ፈሳሽ ይተላለፋል።»

የዓለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ እንደሚሉት ከሆነ ይህን ተላላፊ በሽታ ለመከላከል ብቸኛዉ መንገድ ከታመሙ ሰዎች ጋ የሚኖር መነካካትን በማስወገድ ነዉ። ይህንንም ሲያብራሩ፤

«ከታመሙ ሰዎች ጋ የሚኖር የአካል ንክኪን ማስወገድ ማለት ነዉ። በመሠረቱ ቫይረሱ የሚራባበትን የጊዜ መጠን መግለፅም ይኖርብናል፤ ይህም ከሁለት እስከ 21ቀናት ነዉ። ባለፈዉ ጊዜ ወረርሽኙ እንደየአካባቢዉ ባህርዩን ሲቀያይር ታይቷል። ምክንያቱም ሰዎች በፍጥነት እየታመሙ ለመጓጓዝ አልቻሉም ነበር።»

Ebola Virus
ኢቦላ ቫይረስምስል picture-alliance/Everett Collection

ሰሞኑን ኢቦላ ቫይረስ ዳግም የታየባት ሀገር ዑጋንዳ ናት። ላለፉት 12ዓመታት ይህችዉ ሀገር ሶስት ዋና ዋና የሚባሉ የኤቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ አጋጥሟታል። በተለይ በአዉሮጳዉያኑ 2000ዓ,ም 425 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸዉ ተረጋግጦ፤ የ224ቱን ህይወት አጥፍቷል። በድጋሚ በ2007ዓ,ም እንዲሁ 149 ሰዎች ላይ ተገኝቶ 37ቱን ገድሏል። ባለፉት ሳምታት ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ ዑጋንዳ ዉስጥ ኤቦላ ሲከሰት ለ16ሰዎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት ሆኗል። ወረርሽኙ ወደዋና መዲና ካምፓላ እስኪደርስ ሃኪሞች አፋጣኝ ምላሽ አልሰጡም በሚልም ተተችተዋል። ከሃኪሞቹ የተሰጠዉ ምላሽ ግን ቀደም ሲል የዓለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ የጠቆሙትን የቫይረሱን ባህሪ የመለዋወጥ አዝማሚያ ያጠናከረ ነዉ የሆነዉ።

እንዲያም ሆኖ ወረርሽኙ እንዳይዛመት በተደረገዉ ጥንቃቄ መስፋፋቱን ለመቆጣጠር ብሎም በህይወት ላይ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ የተደረገዉ ጥረት ዉጤት ማሳየቱን ነዉ የወጡ ዘገባዎች ያመለከቱት። ዮአኺም ሳዌካ በዑጋንዳ የዓለም የጤና ድርጅት ተጠሪ እንደሚሉት ከሆነም በሽታዉ ከያዛቸዉ ጋ የተነካኩ የተባሉ ወደ176ሰዎች ተለይተዉ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸዉ ነዉ። ለበሽታዉ የሚሆን ህክምና እስካሁን አለመገኘቱን በመጠቆምም ኢቦላ በአሁኑ ወቅት በተከሰተበት ምዕራብ ዑጋንዳ የሚገኙት የህክምና ባለሙያ ዴኒስ ሉዋማፋ ምላጎ ሃኪም ቤት በሽታዉ እንዳይስፋፋ የሚያደርገዉ ጥረት የኮሌራ ወረርሽኝ ሲከሰት ከሚያደርገዉ ጋ የተመሳሰለ መሆኑን ነዉ የገለፁት፤

 «ምላጎ ዉስጥ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነጥሎ የማቆያ ይዞታ የለንም፤ ያለን ሁኔታ ለኮሌራ ህክምና የምናደርገዉ ዓይነት ነዉ። ኮሌራ አልፎ አልፎ ስለሚከሰት ለዚህ የሚዉለዉ ስፍራ ስራ ላይ ካልዋለ አንዳንዴ የምጠቀምበት በመሆኑ፤ ቦታዉን ለለዚህ አገልግሎት ለማዋል ርምጃዎችን ወስደናል፤ በቋሚነት ሰዎች ተነጥለዉ የሚታከሙበትን ለማመቻቸት እቅድ ይዘናል፤ ከዓለም ዓቀፍ ተባባሪዎችም ድጋፍ እያገኘን ነዉ።»

የዑጋንዳ ዕለታዊ ጋዜጦች የኢቦላን ቫይረስ ለመከላከል ህዝቡ ሊያደርግ ስለሚገባዉ ጥንቃቄ፤ እነማን ለዚህ የተጋለጡ እንደሆኑ፤ ስለበሽታዉ ምልክቶችና ተያያዥ መረጃዎች ለህዝቡ በየቀኑ የማሳወቅ ተግባራቸዉን አጠናክረዉ ተያይዘዉታል። እንዲያም ሆኖ ህዝቡ በበሽታዉ የመያዝ ስጋቱ ከፍተኛ መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ። ሰዎች የሚያዉቋቸዉንም ሆነ የቤተሰቦቻቸዉን አባላት እጅ ለመጨበጥ አይደፍሩም። ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ራሳቸዉ ወደመድረክ ብቅ ብለዉ ለህዝቡ ያስተላለፉት ማስጠንቀቂያም ጠንከር ያለ ነዉ፤

Symbolbild Bioterrorismus
ምስል picture-alliance/dpa

«ኢቦላ መታከም የሚኖርበት መከላከያዉን ባደረጉ የህክምና ባለሙያዎች ብቻ ነዉ። ሁኔታዉን በዚህ መልኩ ከተከታተልን ብቻነዉ ኤቦላን ፈጥነን ልናጠፋዉ የምንችለዉ። የዛሬ ስድስት ወር ገጠር ዉስጥ የሆነዉም ይኸዉ ነዉ። አንዲት ታዳጊ ወጣት በኤቦላ ቫይረስ ተይዛ ቦምቦ ወታደራዊ ሃኪም ቤት ትሞታለች። ከመነሻዉ ሃኪሞቹ የበሽታዉን ምንነት በመጠርጠራቸዉ ያስታመሟት በጥንቃቄ በመሆኑ በሽታዉ ወደሌላ አልተዛመተም። በሽታዉን በወቅቱ የደረሱበትን የሩዌሮ ዶክተሮች እያመሰገንኩ፤ እናንተም ራሳችሁን እንድትጠብቁ እጅ መጨበጥንም እንድታስወግዱ አሳስባለሁ። በዚህ መሰል በሽታ የሞተ ሰዉን እንዳትቀብሩ፤ የህክምና ባለሙያዎች ይህን እንዲያከናዉኑት እንድታደርጉ፤  የወሲብ ተጓዳኞቻችሁንም እንዳትቀያይሩ፤ ምክንያቱም በወሲብም በሽታዉ ሊተላለፍ ይችላል።»

በቫይረሱ ከተያዙ መካከል ምን ያህሉ ሊሞቱ እና ምን ያህሉስ ሊተርፉ ይችላሉ ብሎ መገመት እንደሚቻል የዓለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ          

ታሪክ ያሳራቪች ሲያብራሩ፤

«በበሽታዉ ዓይነት ላይ የተመሠረተ ነዉ የሚሆነዉ፤ አምስት ዓይነት የኤቦላ ቫይረስ ይገኛል፤ በዚህም ከ20 እስከ 90 በመቶ ድረስ በሚገኝ ደረጃ ዉስጥ ነዉ ለሞት የሚያሰጋዉ ይዞታ። እስካሁን የተመዘገበዉ የሞት መጠን ወደአንድ ሺህ ስምንት መቶ ይደርሳል።»

የኢቦላ ቫይረስ ምንነት፤ የሚያደርሰዉ የጤና እክልም ሆነ የሰዉ ህይወትን መቅጠፉ ከታወቀ ከሶስት ዓስርት ዓመታት በላይ ቢሆንም እስካሁን ግን ሊያድን የሚችል መድሃኒትም ሆነ ለመከላከያ የሚሆን ክትባት አለመገኘቱን ነዉ ባለሙያዉ ያመለከቱት። ምክንያቱንም ይገልፃሉ፤

«እንዳለመታደል ሆኖ ለኢቦላ የሚያድን መድሃኒትም ሆነ ክትባት የለም። ችግሩን ለመቋቋም የምናደርገዉ ምንድነዉ፤ በከፍተኛ ሁኔታ በበሽታዉ የተጎዱ ህሙማንን እጃችን ላይ ባሉ መድሃኒቶች ማከም ነዉ። ማዳኛ መድሃኒት ግን የለም። መድሃኒትና ክትባትን ለማስገኘት የሚያስችሉ ምርምሮችም ያን ያህል እየወጡ አይደለም፤ ምክንያቱ ሊሆን የሚችለዉም፤ ከሌሎች የበሽታ ዓይነቶች መደራረቡ ነዉ፤ እንደወባ፤ እንደኤድስ እንዲሁም ሌሎች መድሃኒትም ሆነ ክትባት ያላገኘንላቸዉ በሽታዎች ማለት ነዉ፤ እነዚህ በሽታዎች ደግሞ በጤና ባለሙያዎች ዘንድ ቅድሚያ የሚሰጣቸዉ መሆኑና የገበያዉ አንቀሳቃሾችም ብዙ ህዝብ ለሚጎዱት የበሽታ ዓይነቶች ትኩረት መስጠታቸዉ ይሆናል።»

Ebola Patienten im Krankenhaus von Gulu Uganda
የኢቦላ በሽተኞች ጉሉ ዑጋንዳምስል AP

የኢቦላ ቫይረስ ምንነት ሲቃኝ፤ መረጃዎች እንደሚሉት ከሆነ በሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሚያጠቡ ሌሎች 30,000 እንስሳት እና የአዕዋፍ ዝርያዎች ላይም ከጎርጎሮሳዉያኑ 1976 እስከ 1998ዓ,ም ድረስ መገኘቱን ያመለክታሉ። በሽታዉ በአየር የሚዛመት ስላልሆነም ባለሙያዎች አበክረዉ የሚያሳስቡት ቀጥተኛ የሆነ የአካል ንክኪን በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ማስወገድን ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ከታማሚዎቹ አካል የሚወጣ ማንኛዉንም ፈሳሽ አለመንካት፤ በተጠቀሙባቸዉ የመመገቢ እቃዎችሞ ሆነ ሌሎች እቃዎችን አለመጠቀምን ይመክራሉ። በሽታዉ ያለባቸዉን የዱር እንስሳት መንካት በቫይረሱ ለመያዝ ምክንያት ነዉ። ህመምተኞቹ በቫይረሱ ካልተያዙ ሰዎች ተገልለዉ ለብቻ ተገቢዉን ጥንቃቄ በሚያደርጉ የህክምና ባለሙያዎች ሊረዱም ይገባል።  

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ