1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ መባረር እንደቀጠለ ነዉ

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2009

ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ባለፈው አንድ ዓመት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የገቡ ከ89 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረጉን የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት አስታወቀ፡፡ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳስታወቀው  ከጥቅምት ወር 2008 እስከ መስከረም ወር 2009 ድረስ ብቻ ወደ ኢትዮጵያ ከተጠረዙት 89 ሺህ ዜጎች ተባረዋል።

https://p.dw.com/p/2ZZAC
Äthiopien Ato Feysel Aliy
ምስል DW/Korri Saudi Arabia Riad

Ber. Riyad (Massendeportation von Äthiopien aus Saudi-Arabien hält an ) - MP3-Stereo

ከሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ እና የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል የደረሰውን መረጃ ዋቢ አድርጎ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳስታወቀው  ከጥቅምት ወር 2008 እስከ መስከረም ወር 2009 ድረስ ብቻ ወደ ኢትዮጵያ ከተጠረዙት 89 ሺህ ዜጎች ሌላ 2897 ( ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ዘጠና ሰባት) ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ ዓረቢያ በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፈው በመገኘታቸው እስር ቤት ገብተዋል፡፡

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵ ኤምባሲ በበኩሉ ወደ ሀገር እንዲመለሱ ከተደረጉትም ሆነ በወንጀል ተግባር ተሳትፈዋል ከተባሉት አብዛኞቹ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና ደላሎች ተታለው ከሀገራቸው የተሰደዱ ዜጎች መሆናቸውን ገልጾል ፡፡ የኢምባሲው የዳያስፖራ እና የቆንስላ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈይሰል አልይ ለዶቸ ቬሌ እንደገለጹት በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና በደላሎቻቸው ላይ ቁርጠኛ ርምጃ ካልተወሰደ ችግሩ በቀላሉ የሚቀረፍ አይሆንም፡፡

በማስተማር ፣ በማሳወቅ ፣ በማስፈራራትም ሆነ ግብረ ኃይል በማቋቋም ሊቀረፍ ያልቻለው የኢትዮጵያዊያን ሕገወጥ የሳዑዲ አረቢያ ጉዞ ዛሬም አልተገታም፡፡ ለደላላም ሆነ ለመንገድ መሪ ብዙ ሺህ ብር ከፍሎ ባህር አቋርጦ በሀሩር እና በበረሀ ጉዞ ቁም ስቅል አይቶ የሞተው ቀርቶ የተረፉት በከፍተኛ ወታደራዊ ዘብ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈውን የሳዑዲን ድንበር አልፎ ለመግባት ጥቂቶች ይችሉ ይሆናል፡፡ አብዛኞቹ ግን በሳዑዲ የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ይወድቃሉ፡፡ ከእነዚህ ብዙሀን ከፊሎቹ  በሕገወጥ አዘዋዋሪዎቻቸው የተሰጧቸው እቃዎች ወይንም ሸክሞች አደንዛዥ እጽ ሆነው ይገኙ እና አንድም በድንበር መጣስ ሁለትም በአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪነት ክስ ተመስርቶባቸው በሳዑዲ እስር ቤቶች ያሉ ኢትዮጵያዊያን በርካታ ናቸው፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዳያስፖራ እና የቆንስላ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈይሰል አልይ እንደሚሉት በሳዑዲ ዓረቢያ በየእስር ቤቱ ያለው የኢትዮጵያዊያን ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡

በረሀ ከቀሩትም ሆነ እስር ቤት ከታጎሩት ሌላ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት እንዳስታወቀው ከጥቅምት ወር ሁለት ሺህ ስምንት ጀምሮ እስከ መስከረም ሁለት ሺህ ዘጠኝ ድረስ ብቻ 89 ሺህ 8 መቶ  ማለትም በየቀኑ በአማካይ 246 ኢትዮጵያዊንን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ይህም ከሳዑዲ ዓረቢያ ሕገ ወጥ ተብለው  ከተባረሩ የሌሎች ሀገር ዜጎች ኢትዮጵያዊያን ቀዳሚውን ስፍራ ያሲዛቸዋል ፡፡ ከዚህም በላይ የየሀገሮችንም የወንጀል ሪፖርት ለኤምባሲው የተላከው ደብዳቤ ያመለክታል ከጥቅምት 2008 እስከ መስከረም 2009 ድረስ 2 ሺህ 8 መቶ 97 ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በሳዑዲ ወህኒ ቤት ገብተዋል፡፡

Äthiopische Flüchtlinge in Saudi
ምስል Nebiyu Sirak

የኢትዮጵያ ኤምባሲ  የዳስፖራ እና የቆንስላ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈይሰል አልይ እንደሚሉት ቁጥሩ ከእውነታው የራቀ አይደለም ፡፡ ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ብቻ ከሳዑዲ አረቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት ወደ ሀገር ለሚጠረዙ ዜጎች የይለፍ ሰነድ ያዘጋጃል በየ ሳምንቱ ከ2 ሺህ 5 መቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከሪያድ ኤምባሲ ብቻ ጊዚያዊ የይለፍ ሰነድ ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ጂዳ የሚገኘው የቆንስላ ጽህፈት ቤትም የሪያዱን ያህል ጊዚያዊ ሰነድ እንደሚያዘጋጅ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አቶ ፈይሰል አልይ እንደሚሉት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በሕገ ወጥ መንገድ ለመግባት የሚያስቡ ዜጎች ደግመው ደጋግመው ሊያስቡ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረግን ስደት በተመለከተ ይህ ነው የሚባል በበጎ የተለወጠ ነገር የለም ፡፡ መንግስት የየክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች በአባልነት የሚሳተፉበት የጸረ ሰዎች ዝውውር ብሄራዊ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን ቢገልጽም መሬት ላይ ወርዶ የሰራው ይህ ነው የሚባል ተግባር እንደማይታይ አስተያየታቸውን የሚሰጡ አንዳንድ የሪያድ ነዋሪዎች ያብራራሉ፡፡

በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ስብሰባ ላይ ስደተኝነትን በተመለከተ የተደረገ ጥናትን ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው በኢትዮጵያ መጣ የሚባለው የኢኮኖሚ እድገት ለወጣቱ የስራ እድል የሚፈጥር አለመሆኑ ወጣቶችም አስፈላጊውን ክህሎት እና ስልጠና እንዲያገኙ ያለመደረጉን ለፍልሰቱ መጨመር በምክንያትነት አስቀምጧል፡፡

ስለሺ ሽብሩ

አዜብ ታደሰ