1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያውን የተባለ ሰባት አስክሬን ተገኘ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 5 2009

በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ከተማ አቅራቢያ የኢትዮጵያውን እንደሆነ የተጠረጠረ ሰባት አስክሬን ከወንዝ ተጥሎ ተገኝቷል፡፡ የሀገሬው ፖሊሶች በአስክሬኖቹ ላይ ምርመራ እያደረጉ ሲሆን በአቅራቢያው ባለ ጫካ 81 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መያዛቸው ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ አይቀርም የሚለውን ጥርጣሬ አጠናክሮታል፡፡

https://p.dw.com/p/2UH7q
Karte Tansania Nyarugusu Flüchtlingslager Englisch
ምስል DW

Suspected 7 Ethiopian bodies found in Tanzania - MP3-Stereo

አስክሬኖቹ የተገኙት ከዳሬ ሰላም በስተሰሜን በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባጋሞዮ አውራጃ ውስጥ ነው፡፡ ስድስቱ አስክሬኖች አውራጃውን አቋርጦ በሚያልፈው ሪቩ ወንዝ ላይ ተንሳፍፈው የተገኙት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኅዳር 28 ነበር፡፡ ከአንድ ቀን በኋላ ቀሪው አስከሬን እንደ ሌሎቹ ሁሉ በላስቲክ ተጠቅልሎ እና ድንጋይ ታስሮበት ተጥሎ ተገኝቷል፡፡

አስክሬኖቹ እንደተገኙ የታንዛንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሚዊጉሉ ንቼምባ በአንድ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው ሰጡት በተባለ አስተያየት ሟቾቹ ሕገወጥ ስደተኞች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ እና የኩሽ ዝርያ እንደሆኑ መለየቱን ተናግረዋል፡፡ ቀሪው አስክሬን በተገኘበት ዕለት የአካባቢው ፖሊስ በአቅራቢያው ባለ ጫካ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን መያዙ “ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ አይቀርም” የሚለውን ጥርጣሬ አጉልቶታል፡፡

አስክሬኖቹ የተገኙበት ክልል የፖሊስ ኃላፊ ቦናቫንቹር ሞሹንጊ 81 ኢትዮጵያውያን ከአቅራቢያው ጫካ መያዛቸውን ለዶይቸ ቨለ አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ሟቾቹ “ኢትዮጵያውያን ይሁኑ አይሆኑ አልታወቀም” ብለዋል፡፡

“ከኢትዮጵያ ናቸው ለማለት አንችልም፡፡ ከየት እንደመጡ እና ዘሯቸው ምን አንደሆነ ለማወቅ ምርምራ ገና እያካሄድን ነው፡፡ አስክሬኖቹ በመበስበሳቸው ማንነታቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ አሁንም የአስክሬን ምርመራ ውጤቱን እየጠበቅን ነው፡፡ አስክሬኖቹን ካገኘን በኋላ በመጥፎ ሁኔታ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አግኝተናል፡፡ አማርኛ እንጂ እንግሊዘኛ የማይናገሩ በመሆናቸው እነርሱን ለማነጋገር ችግር ገጥሞናል፡፡ ሆኖም ወደ ደቡብ አፍሪካ እየሄዱ እንደነበር ነግረውናል” ይላሉ የፖሊስ ኃላፊው፡፡

በህይወት የተገኙት ኢትዮጵያውያን ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 35 ባለው መካከል እንደሚሆን እና ሁሉም ወንዶች መሆናቸውን የፖሊስ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባጋሞዮ በሚገኝ የማቆያ እስር ቤት እንደሚገኙ፣ ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ገልጸዋል፡፡ በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተመልሰው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ነገር ግን በቋንቋ የመግባባት ችግር ስላጋጠማቸው አስተርጓሚ እያፈላለጉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የፖሊስ ኃላፊው “አስክሬኖቹ የኢትዮጵያውያን መሆናቸው አልተረጋገጠም” ይበሉ እንጂ ጉዳዩን “ዘ ሲትዝን” በተሰኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ለንባብ ያበቃው ጋዜጠኛ አቱማን ሙቱሊያ ግንየመሆን ዕድል እንዳላቸው ከእርሳቸው አፍ ሰምቼያለሁ ይላል፡፡

“የፖሊስ ኃላፊው ጋር ደውዬ [የሀገር ውስጥ ጉዳዮች] ሚኒስትሩ ስለተናገሩት በተለይ ስጠይቃቸው ከምንመለከታቸው ነገሮች አንዱ ነው ብለውኛል፡፡ ምክንያቱም አስክሬኖቹ በተገኙበት ወቅት የእዚያ ዘር ምልክቶች አግኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለን መደምደም ባንችልም ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል አለ ብለውኛል” ሲል ለዶይቸ ቨለ ተናግሯል፡፡

ጋዜጠኛው በርካታ አስክሬን በአንድ ቦታ ተጥሎ መገኘቱ ጉዳዩን አነጋጋሪ አንዳደረገው እና የሀገሪቱን ፖለቲከኞች ትኩረት እንደሳበ ይናገራል፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሲም ማጃሊዋ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ አዝዘዋል ሲል ጉዳዩ ያገኘውን ትኩረት ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ በታንዛንያ ኤምባሲ የሌላት ሲሆን በዚያ ያሉ ጉዳዮችን የሚከታተለው ተቀማጭነቱን ናይሮቢ ኬንያ ያደረገው ኤምባሲ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያኑን ሁኔታ አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረብንላቸው በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጉዳዩን ለማጣራት እየሞከሩ እንደሆነ ከመናገር ውጭ ተጨማሪ መረጃ ሳይሰጡን ቀርተዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሰ