1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ "ልማታዊ መንግሥት" ከወዴት አለ?  

እሑድ፣ ሚያዝያ 27 2011

ኢሕአዴግ የሚከተለውን የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ያጠኑ ባለሙያዎች ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል መፍጠር ለሙስና እጅ መስጠቱን ይናገራሉ። ኢሕአዴግም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የተወሰነ ድርሻ በመሸጥ ባለፉት አመታት ከተከተለው ልማዊ መንግሥት ሞዴል ማፈንገጥ ለመጀመሩ ጥቆማ ሰጥቷል። ኢሕአዴግ ከእንግዲህ በልማታዊ መንግሥት መንገድ ይቀጥላል?

https://p.dw.com/p/3HuOu
Äthiopien Addis Abeba im Bau
ምስል DW/E. Bekele

የኢሕአዴግ መንገድ እና የልማታዊ መንግሥት እጣ-ፈንታ

የኢሕአዴግ ልሒቃን ለረዥም አመታት ኢትዮጵያን ከድሕነት ይታደጋል፤ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ ይቀላቅላታል ብለው የደሰኮሩለት ልማታዊ መንግሥት አሁን አሁን ድምፁ ጠፍቷል። መስማማት የተሳናቸው አራት ፓርቲዎችን ያቀፈው ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የተወሰ ድርሻ ለግል ባለወረቶች ሲሸጥ ወደ ነፃ ገበያ መርኅ እያጋደለ ለመምጣቱ ጥቆማ ተገኝቷል።

ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ ለማስገባት ኹነኛው መንገድ ከእስያ አገሮች የተቀዳው ልማታዊ መንግሥት አሰራር ነው ሲሉ ይሞግቱ የነበሩ የኢሕአዴግ ልሒቃንም ከአደባባይ ፖለቲካው ገሸሽ እያሉ ነው።

ግንባሩን የሚመሩት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድም ከአቶ መለስ ዜናዊ እና ኃይለማርያም ደሳለኝ በተቃራኒ በነጻ ገበያ መርኅ የሚያምኑ ካፒታሊስት መሆናቸውን በይፋ ተናግረዋል።

በገበያው መንግሥት የአንበሳ ድርሻ ሊኖረው ይገባል በሚል መርኅ የተጀመሩ ግዙፍ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች በታቀደላቸው ገንዘብ እና የጊዜ መርሐ-ግብር ሳይጠናቀቁ ቀርተው ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እና በብድር ጫና ቅርቃር ውስጥ ወድቃለች። ለመሆኑ ልማታዊው መንግሥት ከወዴት አለ? ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ