የኢትዮጵያ መንግሥት ምጣኔ ሐብታዊ የቤት ሥራዎች

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:31 ደቂቃ
10.10.2018

የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ በዚህ አመት መጨረሻ ይሻሻላል ተብሎ ይጠበቃል

የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ማሻሻያ በአመቱ መጨረሻ ለተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል፤ አገሪቱ ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የጀመረችውን ሒደት እስከ 2012 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ አቅዳለች። እነዚህ ጨምሮ ፕሬዝዳንት ሙላቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በአመቱ ሊሰራ ያቀዳቸውን በርካታ ውጥኖች ይፋ አድርገዋል። ይሳኩ ይሆን?

የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ማሻሻያ በዚህ አመት መጨረሻ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጥቆማ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሰኞ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አመታዊ የሥራ ዘመን በጋራ ጉባኤ ሲጀመር እንዳሉት ለሁለት አስርት አመታት የንግድ ሕጉን ለማሻሻል ሲደረግ የነበረው ጥረት በ2011 ዓ.ም. መጠናቀቂያ መቋጫ ሊያገኝ ይችላል። 
አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ በንጉሳዊው ሥርዓተ-መንግሥት የተተገበረ ቢሆንም በየጊዜው አነስተኛ ለውጦች እንደተደረጉበት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት መጠን፣ አሰራር፣ ተሳታፊዎች እና የንግድ ሥርዓቱ የሚሰራበት መንገድ በመቀየሩ ምክንያት የንግድ ሕጉን ማሻሻል ተገቢ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ያምናሉ። 
ፕሬዝዳንት ሙላቱ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እና የአመቱን አበይት የትኩረት አቅጣጫዎች አንስተዋል። ፕሬዝዳንቱ አበይት ባሏቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ሲያተኩሩ ንግግራቸው ሁለት መንገዶችን የተከተለ ሆኖ ታይቷል። የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት በተመለከተ ባነሷቸው ሐሳቦች ባለፉት አመታት አገሪቱ የደረሰችበትን ዕድገት፣ ምጣኔ ሐብቷ የገጠሙትን ፈተናዎች እና በአመቱ መንግሥት የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች ጠቃቅሰዋል። 
እንደ ፕሬዝዳንት ሙላቱ አባባል የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ዕድገት እያሽቆለቆለ ይገኛል። ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ፣ ሥር የሰደዱ ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ባለወረቶችን ተስፋ ማስቆረጡን ገልጸው የማገገሚያ ፖሊሲ እንደሚያሻው አስረድተዋል። ከብድር አስተዳደር እስከ ቁጠባ መንግሥት የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ሊወስዳቸው ያቀዳቸውን ዕርምጃዎች እንዲህ ጠቁመዋል። 
በአመቱ የኢትዮጵያን የገንዘብ፣ የካፒታል እና የኢንሹራንስ ገበያ የማጣጣም እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ጠቅለል ባለ ንግግራቸው ጠቁመዋል። የአገሪቱን የወጪ ንግድ ችግሮች መቅረፍ ፣  ለድንበር አካባቢ ንግድ ህጋዊ ማዕቀፍ ማበጀት እና ከቀጠናው እና በመላው አፍሪካ ያለውን የንግድ ትሥሥር ማጎልበት መንግሥት አበይት ካላቸው የቤት ሥራዎች መካከል እንደሚገኙበት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛ ለመስጠት መወሰኗ ለአገሪቱ ንግድ እና ቱሪዝም የጎላ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንቱ ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል ለረዥም አመታት የተጓተተው የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ይገኝበታል። ፕሬዝዳንቱ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ባይገቡም በሁለተኛው የዕድገት እና የትራንፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ማብቂያ ሒደቱን ለማጠናቀቅ መታቀዱን ጠቁመዋል። 
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ድርድር ከጀመረች አስራ አምስት አመታት ተቆጥረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩ ከሶስት አመታት በፊት ይጠናቀቃል የሚል እቅድ ነበረው። ድርድሩ ግን ላለፉት ስድስት አመታት ከነበረበት ፈቅ ለማለቱ የታየ ምልክት የለም። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ውስብስቡን የአባልነት ሒደት እና ውስብስቡን ድርድር በተባለው ጊዜ የማጠናቀቁ ጉዳይ ፈታኝ መሆኑ አይቀርም። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያም እስካሁን የአባልነት ጥያቄው ያለፈበትን ሒደት ተመልክቶ ፕሬዝዳንቱ ባሉት ጊዜ ይጠናቀቃል ብሎ መገመት እንደሚከብድ ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በብቸኝነት ተቆጣጥሯቸው የነበሩ የስራ ዘርፎች ለግል ባለ ሐብቶች ለመክፈት ፈቃደኝነት አሳይቷል። በኢሕአዴግ ውሳኔ መሠረት ኢትዮ-ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተብለው ከሚጠሩ ተቋማት ድርሻዎች መካከል የተወሰነውን ለግሉ ዘርፍ ለመሸጥ ኢትዮጵያ ዝግጅት ላይ ትገኛለች። ውሳኔው ከምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እና ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ቢገጥመውም የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለሚደረገው ጥረት ግን አዎንታዊ እርምጃ ይመስላል። አቶ ጌታቸው እንደሚሉት ግን ይኸ ብቻውን በቂ አይደለም። 
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው "መሬትን በባለቤትነት በካፒታል ድርሻ በመያዝ በተመረጡ ከተሞች ትላልቅ የጋራ ልማት ኢንቨስትመንቶች እንዲካሄዱ" እንደሚደረግ ተናግረዋል።  "የመንግስት ገቢና ወጪ አስተዳደር ህግን መሰረት አደርጎ በቁጠባና በውጤታማነት እንዲፈፀም፣ የታክስ ገቢ አስባሰብ ስርዓትን የሚያጠናከር፣ የታክስ ብክነትን በበቂ ሁኔታ የመከላከል እና ውዝፍ የታክስ ገቢን የሚቀንሱ ስራዎች ትኩረት እንደሚደረግባቸውም ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል። 
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

ተከታተሉን