1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የስለላ መረቡ 

ሐሙስ፣ ኅዳር 28 2010

የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዋሚዎቹ ላይ በዘመናዩ ቴክኖሎጂ ሰፊ የኮምፒውተር ጠለፋና የስለላ ዘመቻ አካሄደ። ይህንን ዛሬ ያጋለጠው የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂውመን ራይትስ ዎች ነው።

https://p.dw.com/p/2osuU
Symbolbild  Cyberattacke Virus Wurm Virusattacke
ምስል picture alliance/dpa/O. Berg

ያልተቋረጠው የኮምፒውተር ስለላ

ሂውመን ራይትስ ዎች አንድ የምርምር ማዕከል ያወጣውን ጥናት ጠቅሶ እንደዘገበዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የስለላ ዘመቻዉን የከፈተዉ  ዉጪም አገር ዉስጥም በሚኖሩ ተቃዋሚዎቹ እና የመብት አቀንቃኞች ላይ ነዉ። የቡድኖችን እና የግለሰቦችን መረጃ መጥለፍ የሚያስችለውን ቴክኖሎጂው የሚሸጡ ኩባንያዎች ሶፍትዌሩን በሚሸጡበት ተግባር ላይ ኃላፊነት የታከለበት አሰራር እንዲከተሉ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ጠይቋል።
በካናዳ የቶሮንቶ ከተማ የሚገኘው ሲቲዘን ላብ የተባለው ምርምር ማዕከል ባልደረቦች ዛሬ ይፋ ባደረጉት ጥናት ውጤት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የስለላ ዘመቻውን እንዳዳጠናከረ አሳይቷል።    በኢየሩሳሌም የሚገኙት የሂውመን ራይትስ ዎች ባልደረባ ኦማር ሸኪር የሲቲዘን ላብ ጥናት ጠቅሰው እንዳስረዱ፣ ይኸው የኢትዮጵያ መንግሥት  ርምጃ በተለይ የተጠናከረው  ከጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓም ገደማ  ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ዙርያ የታየውን  ተቃውሞ ተከትሎ ነው።
« የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ በሚገኙ ተቺዎቹ  አንፃር ግዙፍ የኮምፒውተር ጠለፋ እና የስለላ ጥቃት አካሂዷል። የመንግሥቱ የሳይበር ጥቃት ዒላማ ከሆኑት መካከል ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች ይገኙባቸዋል። »
ሂውመን ራይትስ ዎች  በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በዘመናዩ ቴክኖሎጂ ግዙፍ የኮምፒውተር ጠለፋ እና ስለላ ተግባር ያካሂዳል በሚል ተመሳሳይ ወቀሳ ሲያቀርብ የመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም፣ ያሁኑን ከቀድሞዎቹ የተለየ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል አንዱ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከአንድ ዓመት ገደማ ወዲህ በላይ በተቃዋሚዎቹ ላይ ስለላውን ማጠናከር ያስቻለውን መሳሪያ ያቀረበውን ኩባንያ ለይቶ ማወቅ መቻሉ እንደሆነ ሻኪር ገልጸዋል። ሂውመን ራይትስ ዎች ቴክኖሎጂውን ለመብት ረጋጮች ሸጧል በሚል አሁን በተለይ ወቀሳውን የሰነዘረበት የእስራኤል ኩባንያ ሳይበርቢት የተባለው ነው።

Oromo Proteste in Äthiopien
ምስል Oromia Media Network
Menschenrechte Logo human rights watch

« የኢትዮጵያን መንግሥት የሚያካሂደውን ስለላ በቀጥታ ከአንድ የታወቀ ኩባንያ ጋር ማገናኘት ችለናል። በኛ አስተሳሰብ ይኸው ኩባንያ የስለላውን ጥቃት ማስቆም ነበረበት፣ የእስራኤል ባለስልጣናትም የተባለውን ቴክኖሎጂ ሽያጭ መቆጣጠር  ነበረባቸው፣ ይህ ቁጥጥር ባለመደረጉ የስለላ ጥቃቶቹ ከሀገር ውጭም ሳይቀር  ቀጥለዋል። »
በመሆኑም፣ ይላሉ ኦማር ሻኪርየመብት ተሟጋቹ ድርጅት ዛሬ ባወጣው ዘገባው ይህንኑ ዘመናይ ቴክኖሎጂ  የሚሸጡ ኩባንያዎች ሶፍትዌሩ ማን እጅ ነው የሚገባው በሚለው ጥያቄ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።
« የኢትዮጵያ መንግሥት በመብት ተሟጋቾች  ላይ የዚህ ዓይነቱን ዘዴ በመጠቀም መብታቸውን የመጣስ የዳበረ ልምድ እንዳለው ይታወቃል። እና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር ኩባንያዎች ይህንኑ ቴክኖሎጂ  የመብት ጥሰት በመፈጸማቸው ለሚታወቁ ወገኖች  መሸጥ  የለባቸውም። » 

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ