1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግስት ፀረ-ሙስና እርምጃ፤ ሹም ሽር እና ምክንያቱ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሐምሌ 24 2009

ገዢዉን ፓርቲ መቶ በመቶ በሆነ ድምፅ መረጠ የተባለዉ ሕዝብ በተለይም የኦሮሚያ፤ የአማራ እና የደቡብ መስተዳድር ሕዝብ መንግስትን በመቃወም የጀመረዉ ዓመፅ ሲግም እንደ ምርጫዉ ዉጤት ሁሉ ካቢኔዉም፤አዲስ አወቃቀሩም የተባለላቸዉ እንዳልሆኑ በገሐድ ፈጋ።

https://p.dw.com/p/2hSfo
Äthiopien Addis Abeba Vereidigung Kabinett
ምስል Imago/Xinhua

መስከረም 2008 አዲስ የተዋቀረዉ የኢትዮጵያ ካቢኔ ሁለተኛዉን የዕድገት እና የለዉጥ ዕቅድን ገቢር የሚያደርግ፤ በዕዉቀት እና ልምድ በበሰሉ ሚኒስትሮች የተሞላ ተብሎ ነበረ።ተባለ።ባመቱ ፈረሰ።ጥቅምት 22 አዲስ ካቢኔ ተዋቀረ።በርካታ ምሁራንን ያካተተ፤ በገዢዉ ፓርቲ ጥልቅ ተሐድሶ፤ በአዋቂዎች ጥናት የነጠረ፤የሕዝብን ጥያቄ ለመለስ የቆረጠ እየተባለ ተወደሰ።ዉዳሴዉ ሳይሰክን በቀድም ቢያንስ ሁለቱ ከካቢኔ ሚንስትርነት ወደ አምባሳደርነት ተሾሙ።ወይም ተሻሩ።የፀረ ሙስና ኮሚሽነር በአምባሳደርነት መሾማቸዉ ከመታወጁ ከዕለታት በፊት በሙስና የተጠረጠሩ ከ30 በላይ ባለሥልጣናት ታሰሩ።እስራት ሹመት ወይ ሽረቱን የሰማነዉ የተጣለባቸዉን ግብር «የግብር ይዉጣ» ባዮች ተቃዉሞ ብልጭ-ድርግም በሚልበት ወቅት ነዉ።ለምን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

                                 

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመጀመሪያ ካቢያኔያቸዉን ያዋቀሩት ኢትዮጵያን እንደ አክሱም ሐዉልት፤ እንደ ሶፉዑመር ዋሻ ወይም እንደ አድዋ ድል ከዓለም ልዩ የሆነችበት የገዢዉ ፓርቲ የመቶ በመቶ ዉጤት ድል አነጋግሮ ሳያበቃ ነበር።መስከረም 2008።ጠቅላይ ሚንስትሩ በዉርስ የያዙትን ሥልጣን በምክር ቤት ድምፅ ባፀደቁ ማግሥት የመሠረቱት ካቢኔ እንደ ምርጫዉ ዉጤት ሁሉ ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ክላስተር የሚባሉ ሰወስት ክፍሎችን ያቀፈ ነበር።

ለሰወስቱ አዳዲስ ክፍሎች የሰወስቱ ተፎካካሪ ብሔረሰቦች የአማራ፤የኦሮሞና የትግሬ ተወላጆች በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የተደረደሩበት የያኔዉ አዲስ ካቢኔ የአምስት ዓመት ግቡ ያኔ አዲስ የሚጀመረዉን ሁለተኛዉን የዕድገትና የለዉጥ ዕቅድ «GTP»ን ገቢር ማድረግ ነዉ ተብሎ ነበር።

 ገዢዉን ፓርቲ መቶ በመቶ በሆነ ድምፅ መረጠ የተባለዉ ሕዝብ በተለይም የኦሮሚያ፤ የአማራ እና የደቡብ መስተዳድር ሕዝብ መንግስትን በመቃወም የጀመረዉ ዓመፅ ሲግም እንደ ምርጫዉ ዉጤት ሁሉ ካቢኔዉም፤አዲስ አወቃቀሩም የተባለላቸዉ እንዳልሆኑ በገሐድ ፈጋ።የአምስት ዓመት ዕቅድ ገቢር ያደርጋል የተባለዉ ካቢኔ በዓመቱ ተበተነ።ክላስተር የተባሉት ክፍሎች ፈረሱ።የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የለዉጥ ዕቅድም ባይፈርስ ደበዘዘ።አዲስ ዓመት።ጥቅምት 22 2009።አዲስ ካቢኔ።ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አዲስ ያዋቀሩትን ካቢኔ ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ የካቢኔ አባላቱ የተመረጡት ከረጅም ጊዜ ጥናት እና ከገዢዉ ፓርቲ የተሐድሶ ለዉጥ እንቅስቃሴ በኋላ ነዉ።

Hailemariam Desalegn Äthiopien
ምስል picture alliance/AP Photo/K.Fukuhara

                                    

የሚንስትሮቹን ሹመት ያፀደቀዉ ምክር ቤት አንዲት አባልም ካቢኔዉ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት በሚችሉ የዳበረ ዕዉቀትና ልምድ ባላቸዉ ሚኒስትሮች የተሞላ መሆኑን መስክረዉ ነበር።

                                 

ካቢኔዉ የተመሠረተዉ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሳዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞና አመፅ ለማስተንፈስ በተለይ በኦሮሚያ መስተዳድር ሹም ሽር ከተደረገ በኋላ ነበር።ተቃዉሞዉን ለመገደብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በደነገገ ማግሥት ነበር።አዲሱ ካቢኔ ተቃዋሚዎች ላነሱት ጥያቄ መልስ የሚሰጥ፤ መንግስት የመልካም አስተዳደር ጉድለት ያለዉን ችግር ለማረም የሚጥር የሚችልም ነዉ ተብሎም ነበር።

በአስረኛ ወሩ በቀደም ከ31ዱ የካቢኔ አባላት አቶ ካሳ ተክለ ብርሐንና ዶክተር ሽፈራዉ ተክለ ማርያም  ካዲሱ ካቢኔ፤ በቀድሞዉ ካቢኔ የምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ ከነበራቸዉ አንዷ ወይዘሮ አስቴር ማሞ  አምባሳደርነት ተሾሙ።አዲሱ ሹመት፤ የፖለቲካ ተንታኝ ፍቅረማርያም መኮንን እንደሚሉት ጥቅምት ላይ የተባለዉ ሁሉ ፉርሽ መሆኑን ጠቋሚ ነዉ።

                                 

ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ የአምባሳደርነት ሹመት የሰጡት ባጠቃላይ ለ12 ፖለቲከኞች  ወይም ዲፕሎማቶች ነዉ።ጥቅምት ላይ የተመሠረተዉ ካቢኔ የሠራና-ያልሰራዉ በቅጡ ሳይለይ፤ ሐገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየተገዛች፤ ነጋዴዎች ለተቃዉሞ በሚያንገራግሩበት በዚሕ ወቅት፤ ነባር ፖለቲከኞችን ከነባር ዲፕሎማቶች የቀይጠዉን ሹመት ብዙዎች በሰወስት ተርጉመታል።«የትኩረት አቅጣጫን ለማሳት። ሁለት በኢሐዴግ ባለSEልጣናት መካከል ያለን ሽኩቻን ለማስተንፈስ። ለተሾሚዎች መጦሪያና መታከሚያ ሰጥቶ ከአዲስ አበባ ገለል ማድረግ።» እያሉ።ሆርን አፌርስ የተባለዉ ድረገፅ ባለቤት ዳንኤል ብርሐኔ አንዱ ነዉ።

Äthiopien Neubildung Kabinett
ምስል DW/Y. Gebergziabeher

                       

አንጋፋዉ ተቃዋሚ  ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ደግሞ «ዉለታ» ይሉታል።ወይም «ጡረታ»አቶ ፍቅረ ማርያም  እንደሚሉት ደግሞ ሹመቱ ሁለት ነገሮችን ጠቋሚ ነዉ።በእድሜ ለገፉት ልክ ፕሮፌሰር በየነ እንዳሉት ጡረታና ዉለታ፤ በእድሜ ላልገፉት ወይም ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ላይ ላሉት ደግሞ ዳንኤል እንዳለዉ የዉሳጣዊ ፖለቲካዊ ሽኩቻን ማስተንፈሺያ።

                                 

በዩናይትድ ስቴትስ እና አዉሮጳ ሕብረት ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ብርሐነ ግብረ ክርስቶስ በቅርብ አመታት ዉስጥ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ደ ኤታ በጣም በቅርቡ ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ የዲፕሎማሲ ጉዳይ አማካሪ ሆነዉ ነበር።አሁን እንደገና ተመለስዉ ከዓመታት በፊት ወደተዉት አምባሳደርነት ተሾመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ፕሬፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ትልቁን የአካዳሚ ተቋም ከመምራት ኮክቴል ወደሚዘወተርበት ሙያ ተቀይጠዋል።የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናም እንዲሁ።  የኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ለረጅም ጊዜ የመሩት አቶ ዓሊ ሱሌይማን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መሆናቸዉን የሰማነዉ በሙስና የሚጠረጠሩ ከ30 በላይ ባለሥልጣናት መታሰራቸዉ በተነገረ ማግሥት ነዉ።ኮሚሽነር ዓሊ ለተተኪያቸዉ ያስረከቡት ዶሴ መከፈቱ ይሆን?

አቶ ፍቅረ ማርያም ግን ሰዎችን በሙስና የሚጠረጠሩ እያሉ ማሰር ለኢሐዴግ መራሹ መንግሥት አዲስ አይደለም።እርምጃዉ ግን ብዙ ጊዜ ሙስናን መዋጋት ሳይሆን ትኩረትን ማስቀየር ነዉ።

በሙስና ተጠረጠሩ ተብለዉ የታሰሩት ሰዎች  ጥፋተኛ-መሆን አለመሆናቸዉን የሚበይነዉ በርግጥ ፍርድ ቤት።ጉዳዩን የሚከታተሉ ሰዎች  ግን አሁንም ሆነ ከዚሕ ቀደም የታሰሩና የተከሰሱት ባለሥልጣናት በሙስና ከተዘፈቁ ከአሳሪዎቻቸዉ የበለጠ ሙሰኛ መሆናቸዉን ይጠራጠራሉ።አቶ ፍቅረማርያምም «ትላልቆቹ ሙሰኞች መቼ ተያዙና» ባይ ናቸዉ።

Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

                         

የመንግሥትን ሥራና አሰራር በመቃወም እስካለፈዉ መስከረም ድረስ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ጥያቄ እስካሁን በቅጡ አልተመለሰም።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም አልተነሳም።ፕሮፌሰር በየነ እንደሚሉት መንግሥት አንድ ጊዜ የካቢኔ ሹም ሽር፤ ሌላ ጊዜ የአምባሳደሮች ሹመት፤ ሌላ ጊዜ ሙሰኞችን ማሰር እያለ የሚወስደዉ እርምጃ ሐገሪቱን ለገጠማት ችግር መፍትሔ አይሆንም።የፖሊሲ ለዉጥ እንጂ።

                                        

አቶ ፍቅረማርያም በበኩላቸዉ መንግስት መዋቅራዊ ቀዉስ ዉስጥ ገብቷል ባይ ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

አርያም ተክሌ