1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ተስፋ

ሰኞ፣ ኅዳር 8 2007

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታውን እጅግ የጠበበ ዕድል ይዞ ረቡዕ ያከናውናል። ቡድኑ በአዲስ የውጭ ሀገር አሠልጣኝ መመራት ከጀመረ ወዲህ ለማሸነፍ የቻለው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው። ምክንያቱ ምንድን ነው? ጂብራልታርን 4 ለ0 ያሸነፈው የጀርመን ቡድን አሠልጣኝ በውጤቱ አልተደሰቱም።

https://p.dw.com/p/1Dorq
Südafrika Äthiopien Fußball Africa Cup DW-Reporter Haimanot Turuneh in Johannesburg
ምስል DW/H. Turuneh
በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ ዩክሬናዊው ብላድሚር ክሊችኮ የቡልጋሪያው ኩብራት ፑሌቭን አብረክርኮታል። ፑሌቭ ከተዘረረበት ሲነሳ እንደ አሎሎ የተነረተ የዓይኑን ቆብ እና ዙሪያ ያለማቋረጥ በበረዶ አስደግፎ ለመያዝ ተገዶ ነበር። የአፍሪቃ ዋንጫን በማዘጋጀት ዙሪያ ሞሮኮ ከካፍ ጋር ተወዛግባለች።
ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ታሪክ አጀማመሯ ጠንካራ ነበር። ተደጋጋሚ ድልም አስመዝግባለች። ሆኖም ብሔራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት ወዲህ ዘላቂ የሚባል መሻሻል አላሰየም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውጭ እና የሀገር ውስጥ አሠልጣኞች የተለያየ የአሰለጣጠን እና የአሠላለፍ ስልት ሲመራ ቆይቶ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የውጭ ሀገር አሠልጣኝ በከፍተኛ ወጪ ተቀጥሮለት የሚሠለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ የወዳጅነትም ሆኑ የጥሎ ማለፍ የተለያዩ ግጥሚያዎችን አኪያሂዶ ያሸነፈው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው። ለምን? የሃትሪክ የስፖርት ጋዜጣ ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ ኢሳቅ በላይ።
Äthiopische Fußballfans Entschuldigung an CAF Afrika-Cup 2013 in Südafrika
ምስል Himanot Tiruneh
የኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና በ ኤፍ ኤም 101 የብስራት ስፖርት አዘጋጅ መንሱር አብዱልቀኒ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድክመት እና ጥንካሬን ሲተነትን ባለፈው የአፍሪቃ ዋንጫ ከተሳተፈው ቡድን ጋር በማነፃፀር ነው።
ኢሳቅ በበኩሉ የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች የግል ችሎታቸው የሚደነቅ ቢሆንም በቡድን ደረጃ ግን ብዙ ሊሰራበት ይገባል ብሏል። መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣትም ጊዜያዊ ውጤት ላይ ከማተኮር የቡድኑን ደካማ እና ጠንካራ ጎኖች በባለሙያ ማስተንተን እንደሚያሻ ጠቅሷል።
የኢትዮጵ ብሔራዊ ቡድን ከአልጄሪያ ጋር በነበረው ግጥሚያ በጉዞ ወቅት ከ10 ሠዓታት በላይ መጉላላቱ ተጠቅሷል። ቡድኑ እጅግ አሰልቺ ከሆነ ረዥም የዓየር በረራ በኋላም ትናንት ዘግይቶ አዲስ አበባ መግባቱ ተገልጿል። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ሆኖም ብሔራዊ ቡድኑ የቀድሞው አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስተያየት ለመስጠት ትንሽ ጊዜ ይቀራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ቀደም ሲል ከአልጀሪያ ጋር ባደረገው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 2 ለ1 እንዲሁም አልጄሪያ ሙስጣፋ ቻላር ስታዲየም ውስጥ 3 ለ1 ተሸንፏል። ካሙዙ ስታዲየም ውስጥ በማላዊ 3 ለ2 ተረትቷል። ከማሊ ጋር በደርሶ መልስ ጨዋታ አዲስ አበባ ውስጥ 2 ለ0 ሲረታ፤ በመልሱ ጨዋታ አሸንፏል። የኢትዮጵያ ቡድን እስካሁን ማሸነፍ የቻለው ባማኮ ከተማ ውስጥ የማሊ ቡድንን ሲሁን ውጤቱም 3 ለ2 ነበር። ቀድማ ማለፏን ያረጋገጠችው አልጀሪያ 6 ነጥብ ካላት ማሊ ጋር ከነጌ በስትያ ከተጫወተች ከሦስት ሠዓታት በኋላ 3 ነጥብ ያላት ኢትዮጵያ 6 ነጥብ ከሰበሰበችው ማላዊ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ በደጋፊዋ ፊት ትጋጠማለች።
ኢኳቶሪያል ጊኒ
ኢኳቶሪያል ጊኒምስል Alexander Joe/AFP/Getty Images
ከእዚሁ ከአፍሪቃ ዋንጫ ሳንወጣ፤ ቀጣዩን የአፍሪቃ ዋንጫ ሞሮኮ ኢቦላ ያሰጋኛል በሚል እንደማታሰናዳ ከገለፀች በኋላ ከአፍሪቃ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በምኅፃሩ ካፍ ጋር መወዛገቧ ይታወቃል። ካፍ ሞሮኮን ከውድድሩ በቀጥታ አሰናብቷታል። የካፍ ቃል አቀባይ ጁኒየር ቢንያም።
«የሞሮኮ ባለሥልጣናት የእራሳቸው መቃወሚያ አላቸው። መስከረም ወር ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ካፍ ባካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ሞሮኮ ለጊኒ አለኝታነቷን በማሳየቷ ምስጋና እና የእንኳን ደስ አለሽ ደብዳቤ ልኳል። ደግሞም ሞሮኮ በኢቦላ ወደተጠቁ ሃገራት የዓየር በረራ ከሚያኪያሂዱ ሃገራት መካከል አንዷ ናት። አሁን የኢቦላን ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ ጥሰት ለመፈፀም መከራከሪያ አድርገው መጠቀማቸውን ለመረዳት ይከብደናል። ሞሮኮ የፊፋ የቡድኖች የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ታዘጋጃለች። እና ያኔ ሪያል ማድሪድን ደግፈው ወደ ሞሮኮ የሚያቀኑ አፍሪቃውያንን እንዳይመጡ ልትከለክል ነው?»
ሞሮኮ ውድድሩን እንደማታዘጋጅ መግለጿን ተከትሎ ቃታር ውድድሩን በማዘጋጀት ለመተባበር ገልጣ ነበር። ሆኖም ኢኳቶሪያል ጊኒ ውድድሩን ለማዘጋጀት በመጠየቋ ያለምንም ማጣሪያ እንድታልፍ እና ከውድድሩ የተሰናበተችው ሞሮኮን እንድትተካ ተደርጓል። የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዲዲየር ድሮግባ ከመወዛገብ ይልቅ የኢቦላ ወረርሽኝን በመታገል ዙሪያ ብናተኮር ይሻላል ሲል አስተያየት ሰጥቷል።
«እዚህ የምገኘው ለአንድ ለተወሰነ ዓላማ ነው። በቅድሚያ ስፖርት እና ኢቦላ በአሁኑ ጊዜ እጅግ የተቆራኙ መሆናቸው እሙን ነው። ግን ደግሞ ባለስልጣናቱ አንዳች ውሳኔ አስተላልፈዋል። እናም እኛ በእዛ መገዛት አለብን። ዋናው ነገር የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች እዚህኛው ሀገር አለያም እዛኛው ሀገር ተኪያሄደ የሚለው አይደለም። ዋናው ነገር ይህች ሀገር ወደፊት ሌሎች ውድድሮችን ማስተናገድ ይፈቀድላት ዘንድ የኢቦላ ወረርሽኙን መዋጋቱ ነው። አንዲት ሀገርን የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎችን እናዳታስተናግድ ከማገድ ይልቅ በሽታውን በመዋጋቱ ዙሪያ ብናተኩር ይሻለናል።»
ሞሮኮን ተክታ የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎችን የምታሰናዳው ኢኳቶሪያል ጊኒ የኢቦላ ወረርሺኝ ከተቀሰቀሰባቸው የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት 2500 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ትገኛለች። ኢቦላ በላይቤሪያ፣ በሴራሊዮን እና ጊኒ ከ5000 በላይ ሰዎችን መቅጠፉ ተዘግቧል። የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች በኢኳቶሪያል ጊኒ የማላቦ፣ ባታ፣ ሞንጎሞ እና ኤቤቢዪን ከተሞች እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል።
በዝረራ የተሸነፈው ቡልጋሪያዊው ኩብራት ፑሌቭን
በዝረራ የተሸነፈው ቡልጋሪያዊው ኩብራት ፑሌቭንምስል picture-alliance/dpa/D. Bockwoldt
የአውሮጳ እግር ኳስ የማጣሪያ ጨዋታዎች በመኪያሄድ ላይ ሲሆን፤ የጀርመን ቡድን ንዑሷ ጂብራልታርን ከሦስት ቀናት በፊት 4 ለ ዜሮ በማሸነፉ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዮኣሒም ሎቭ አለመደሰታቸውን ገለጡ።
«በጨዋታው ደስተኛ አይደለሁም፤ ምክንያቱም ዛሬ 4 ለ 0 ማሸነፋችን ለእኛ በጣም ዝቅተኛ ነው። በቂ ግቦች አልተቆጠሩም። ከቡድኑ ዛሬ ብዙ ጠብቄ ነበር፤ በተለይ በኹለተኛው አጋማሽ። በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰኑ የግብ ዕድሎችን ማምከኑ እና ግቦችን ማስቆጠሩ ተሳክቶልናል። በኹለተኛ አጋማሽ ግን ብዙም የግብ ዕድሎች አልነበሩም።»
የጀርመን ቡድን አሠልጣኝ እና ህዝብ የጂብራልታር ቡድን ልምድ የሌለው በመሆኑ የዓለም ዋንጫን የጨበጠው ቡድናቸው በርካታ ግቦችን ያስቆጥራል ብለው ጠብቀው ነበር። ጀርመን በነገው ዕለት ከስፔን ቡድን ጋር የሚጋጠም ሲሆን፤ ግብ ጠባቂው ማኑኤል ኖይማን በቀኝ ቁርጭምጭሚቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት እንደማይሰለፍ ተገልጧል።
የከባድ ሚዛን ቡጢ ባለድሉ ዩክሬናዊው ቭላድሚር ክሊችኮ ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ ከትናንት በስትያ የቡልጋሪያው ኩብራት ፑሌቭን በዝረራ አሸንፏል። የ38 ዓመቱ ዩክሬናዊ የ33 ዓመቱን ቡልጋሪያዊ በማሸነፉ ለ17ኛ ጊዜ ባለድል ለመሆን ችሏል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተክሌ የኋላ