1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጅ ቅድሚያ ሰጥተዋል

ሐሙስ፣ ሐምሌ 27 2009

የኢህአዴግ እና የ17 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች ባለፈዉ ማክሰኞ የጀመሩትን አዲስ ዙር ድርድር ዛሬም ቀጥለው ውለዋል፡፡ ተደራዳሪዎቹ በሶስት ከከፈሉት የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጅ፤ የመጀመሪያውን ክፍል ዛሬ አጠናቅቀዋል፡፡ በቀጣዩ ክፍል ላይ ለመወያየት ደግሞ ለፊታችን ማክሰኞ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2hepQ
Äthiopien Verhandlungsrunde zwischen Regierung und Opposition
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

ለፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጅ ቅድሚያ ሰጥተዋል

የገዢው ፓርቲ የኢህአዴግ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች ይደራደራሉ ከተባለ መንፈቅ አለፈ፡፡ በእርግጥ ወደ መደራደሪያው ጠረጴዛ መጥተው አንድ ሁለት እያሉ ጉዳዮችን መንቀስ የጀመሩት ግን ገና በዚህ ሳምንት ነው፡፡ ማክሰኞ፡፡ ሐምሌ 25፡፡ ለድርድራቸው ቅድሚያ የሰጡት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጅን ነው፡፡ 

የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጅ የወጣው ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ በሁለተኛው ዓመቱ በ1985 ዓ.ም ነበር፡፡ አዋጁ ከአንድ ዓመት በኋላ እንዲሻሻል ተደርጎ ለ14 ዓመታት አገልግሏል፡፡ በድጋሚ በ2000 ዓ.ም የተሻሻለው ይህ አዋጅ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ቅሬታ ሲያንሳ ቆይቷል፡፡ ለድርድር የተቀመጡት ኢህአዴግ እና 17 ተቃዋሚ ፓርቲዎች 63 አንቀጾች የያዘውን ይኸን አዋጅ ሶስት ቦታ በመክፈል እየተወያዩበት ይገኛሉ፡፡ 

ከተደራዳሪዎቹ አንዱ የሆኑት የመኢአድ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ፓርቲያቸው በአዋጁ ላይ እንዲሻሻሉ የፈለጋቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ማቅረቡን ይናገራሉ፡፡ 

“አንደኛ በዚህ የፓርቲ ምዝገባ አዋጅ ላይ የመመስረቻ ቁጥር ስንት ይሁን? የሚል አቅርበናል፡፡ ከዚህ በፊት የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ መነሻ ቁጥር 1500 ነበር እና እኛ ማሻሻያ አድርገን ያቀረብነው 2500 ነበር፡፡ የክልል ፓርቲዎችም እንደዚሁ 750 ነበር፡፡ እኛ 1500 አድርገን ነው ያቀረብነው፡፡ በምዝገባ አዋጁ አንቀጽ 8 ደግሞ ስለምዝገባ የሚቀርብ ማመልከቻ የሚል አለ፡፡ እርሱም እንዲስተካከል አቅርበናል፡፡ አዋጁ ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ኦዲተርን መሾም የሚል አለው፡፡ ይሄን መሾም የሚለውን አወዳድሮ መቅጠር በሚል ማሻሻያ ነበር ያቀረብነው” ይላሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ፡፡

እንደ አቶ ሙሉጌታ ፓርቲያቸው ካቀረባቸው ማሻሻያዎች ከአንዱ በስተቀር ሌሎች ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ሌላኛው ተደራዳሪ የአንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትዕግስቱ አወሉ አዋጁን አስመልክቶ በእርሳቸው ፓርቲ በኩል የቀረቡትን ነጥቦች እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ 

Äthiopien Verhandlungsrunde zwischen Regierung und Opposition
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

“በእኛ በኩል እንዲሻሻል ያቀረብነው የክልል ፓርቲ አደረጃጀት ብሎ አንቀጽ 6 ላይ አስቀምጦታል፡፡ አሁን ከተግባር ያየነው በብሔር ብቻ የመደራጀት ጉዳይ ነው ያለው፡፡ እዚያ ላይ ብሔር ብሎ ባይጠቅስም ግን ተግባሩ የሚያሳየን ያ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ጥሩም መጥፎም ነገር እንዳስከተለ ተገንዝበን፣ ገምግመን ፓርቲዎች መደራጀት ያለባቸው በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እና በፖለቲካ ፍልስፍና መሆን አለበት የሚል አቋም ነው ይዘን የገባነው፡፡”

“ሌላው ተጨማሪ የመስራቾችን መስፈርት በተመለከተ ነው፡፡ ለምሳሌ በእኛ በኩል መስራች ስብሰባ ላይ 10 በመቶ ዲፕሎማ እና ከዚያ በላይ መስራቾች ቢመዘገቡ፣ የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ 10 በመቶ ቢመዘገቡ፣ በአመራር ውስጥ ደግሞ 30 በመቶ የዲግሪ እና ከዚያ በላይ አባል ያለው ተመዘግቦ ቢቀርብ፣ በአመራሩ ላይ እንደመስፈርት ቢሆን [ብለናል]፡፡ ምክንያቱም ትግሉ የሀሳብ ትግል ነው፡፡ የሃሳብ ትግል ደግሞ ዕውቀትን ያላማከለ ሊሆን አይችልም በሚል ሰፊ ጊዜ ወስደን ነው የተከራከርነው” ይላሉ ሊቀመንበሩ፡፡  

እንደ አቶ ትግስቱ አባባል በከትላንት በስቲያ እና በዛሬው ውይይት የተደረሱባቸው ስምምነቶች በአደራዳሪዎች በኩል ተዘጋጅተው የፊታችን ማክሰኞ በሚደረገው ውይይት  ይቀርባሉ፡፡ ሁለቱም ተደራዳሪዎች እስካሁን የተመለከቱት የድርድር መንፈስ “ጥሩ” እንደሆነ እና ከገዢው ፓርቲ ጋርም መግባባት ላይ እንደደረሱ ያስረዳሉ፡፡ በድርድሮቹ ላይ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች እንደተገኙም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲዎቹ  በምርጫ ህግ እና በፓርቲዎች ስነ ምግባር ደንብ ላይ በቀጣይነት ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተደራዳሪዎቹ ፓርቲዎች አጠቃላይ ድርድራቸውን በሶስት ወር ለማጠናቀቅ ተሰማምተዋል፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ