1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ነባር ነገዶችና፤ «ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል»

ዓርብ፣ መስከረም 26 2004

ኢትዮጵያ ነባር ነገዶች ተወላጆች የሆኑ 100 ያህል ሰዎች «ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል» የተሰኘው ድርጅት እንደገለጸው ፣ የግቤውን ወንዝ 3ኛ ግድብ ሥራ በመቃወማቸው፣ በቅርቡ ተይዘው ታሥረዋል።

https://p.dw.com/p/Rpr7
ምስል DW

ይኸው ድርጅት ፤ አንድ የኢትዮጵያ ፖሊስ፤ ለነባሩ ህዝብ ማኅበረሰብ ሰጠ የተባለውን ማስጠንቀቂያ ፤ ቃል ጠቅሶ እንዳለው፤ «መንግሥት መንግሎ እንደሚያስወግድ ተሽከርካሪ(ቡልዶዘር)በመሆኑ ፤ በመቃወም ከፊቱ የሚቆሙትን ይደፈጠጣል »።

ተክሌ የኋላ፣ የ «ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል»ን የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ የሆኑትን አሊስ ባየርን አነጋግሮ ፤የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

በደቡብ ኦሞ ወንዝ ተፋሰስ አውራጃ የሚኖረው ህዝብ ከፊል አርብቶ አደር ሲሆን፤ መሬቱ ፤ SI እንደዘገበው፤ ለውጭ ኩባንያዎችና ለመንግሥት ኩባንያዎች ሸንኮራ አገዳ፤ እህልና ለነዳጅ የሚወል ተክል እንዲያለሙበት የሚሰጥ በመሆኑ ተወላጆቹን ባዶ እጅ የሚያስቀር ነው። ተያዙ ስለተባሉት 100 ያህል ሰዎች ፣ ስለነባር ህዝቦች መብት የሚሟገተው ዓለም አቀፍ ድርጅት SI የሚያውቀው ጉዳይ አለ? ከድርጅቱ ተወክሎ ያያቸው ሰው አለወይ? አሊስ ባየር---

«ቢሆን መልካም ነበር። ግን፤ የሚቻል አይደለም። ባካባቢው የፍርሃት መንፈስ ነው እንዳረፈ ነው፤ ያገኘነው መረጃ ፣ የሰማነው ቢኖር፤ 100 ገደማ የሚሆኑ የሙርሲና ቦዲ ብሔረሰቦች አባላት የጊቤ 3 ግድብ እንዳይሠራ በመቃወማቸው ፣ ተይዘው መታሠራቸውን ነው። ይህንም የተቃወሙት በመሬታቸውና በኑሮአቸው ላይ የሚያስከትለውን በማገናዘብ ነው።»

የታችኛው የኦሞ ወንዝ ሸለቆ፤ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት፣ የዓለም ቅርስ ተብሎ መመዝገቡ ታውቋል። ግቤ 3 የሚሰኘው ግድብ ተግባራዊ ቢሆን፣ ይደርሳል የሚባለው የጥፋት መጠን እስከምን ድረስ የሚያሳስብ ነው ይባላል?

«በኦሞ ወንዝ ታችኛው ሸለቆ ለሚኖሩት፤ ብርቱ ጥፋት ነው የሚደርሰው። 100 ሺ ያህል ሰዎች ናቸው በዚያ የሚኖሩት። የ።ግቤ ግድብ ሥራ ቢቀጥል ጉዳት ይደርስባቸዋል። የኑሮ ዘዴአቸው ይናጋል፤ በዓመታዊው የውሃ ሙላት የሚመኩ ሲሆን፤ ግቤ 3 ግድብ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ግን የውሃ ሙላቱ ይቋረጣል። በተጨማሪ የሰማነው፤ መንግሥት ለሸንኮራ ፤ እንዲሁም ለነዳጅ የሚውል ተክል ለማልማት ፤ ለውጭ ኩባንያዎችና ለመንግሥት ኩባንያዎች፣ በማከራየት ላይ መሆኑን ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው፤ እስካሁን ራሳቸውን ችለው በሚኖሩ ነገዶች መሬት ላይ ነው። ግን ፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች፤ ተግባራዊ የሚሆኑ ከሆነ፤ ራስ መቻላቸው ይቅርና የመንግሥት ተመጽዋቾች ይሆናሉ።»

«ሰርቫይባል ኢንተርናሽናል»፤ የኦሞ ወንዝ ሸለቆን አካባቢ ይዞታ በተመለከተ ፣ በተደጋጋሚ አሳሳቢ ነው በማለት መግለጫዎች ሲያወጣ መቆየቱ የሚታበል አይደለም። ዋና ፍላጎቱም ሆነ ጥያቄው ምንድን ነው? የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ተጠሪ ፣ አሊስ ባየር ፤ እንዲህ ይላሉ።

«የእኛ ጥያቄ የአነዚህ ሰዎች መብት እንዲከበር ማንኛውም በመሬታቸው ላይ የሚፈጸም ጉዳይ፤ እነርሱን ሳያማክሩና ሳያስፈቅዱ እንዳይከናወን ነው። ይህ አቋም መከበር ይኖርበታል፤ የሚያሳዝነው፤ የአካባቢውን ሰዎች ያማከረ አለመኖሩ ነው። እነርሱም ለማንም ፈቃድ አልሰጡም። ብዙዎቹ እንዲያውም፤ ርስት-ጉልታቸውን እንዲለቁ ተገደው ወደሌላ ቦታ መሄድ እንዳለባቸው አያውቁም። »

ዋና ጽ/ቤቱ በለንደን ብሪታንያ የሚገኘው፣ SI ዋና ሥራ አስኪያጅ Stephen Corry «የኢትዮጵያ መንግሥትና ደጋፊዎቹ፣ የእነዚህን ነገዶች መሬት በመዝረፍ ፣ ኑሮአቸዋን ሊያናጉባቸው ቆርጠው ተነስተዋል። ራሳቸውን ችለው የሚኖሩትን ነገዶች የመንግሥት ተመጽዋቾች ለማድረግ፤ የማይስማሙትንም እሥር ቤት መወርወር ነው የሚፈልጉት።

ይህ ከዕድገትና ልማት ጋር የተያያዘ ነው የሚል አስመሳይ ምክንያትም ይሰጣሉ። አሳፋሪ ተግባር፣ ወንጀልም ነው, እናም ማንም መሠረታዊ ሰብአዊ መብትን የሚንከባከብ ሁሉ በጽናት ሊቃወመው ይገባል» ሲሉ ጠንከር ያለ የተቃውሞ መልእክት ማስተላለፋቸው ተጠቅሷል፤ አሊስ ባየር በዚህ ረገድ የለጋሽ መንግሥታት ድርሻ ምን ሊሆን እንደሚገባና ድርጅታቸው ከአነርሱ ምን እንደሚጠብቅ ሲያወሱ እንዲህ ነበር ያሉት።

«ለጋሽ መንግሥታት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ለሰብአዊ መብት መጣስ ኀላፊ መሆኑን፣ በማንኛውም በሚቻልለው ሁሉ እንዲያስገነዝቡና እንዲያስቆሙ ጥሪ እናቀርባለን። ይህን በተመለከተ፣ ለጀርመን መንግሥት ድብዳቡ ጽፈናል። እኛ የምንለው፤ ሰፊ የልማት እርዳታ፤ ለፕሮጀክቶች እየተባለ ወደ ኢትዮጵያ መላኩ ተቀባይነት የሌለው ነው። እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች፤ አጥፊና የሰብአዊ መብትን በመጣስ የሚከናወኑ ናቸው። ይህ ተቀባይነት የለውም። SI ን የመሳሰሉ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ በኦሞ ሸለቆ የሚኖሩ ነገዶችን መብት እስኪያከብር ድረስ ፤ ስለሰብአዊ መብት መጣስ ማጋለጣቸውን ይቀጥላሉ።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ