1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሐጅ ከ228 በላይ በረራዎች ማዘጋጀቱን አስታወቀ 

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2011

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለአመታዊው የሐጅ ጸሎት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለማጓጓዝ ከ228 በላይ በረራዎች ማዘጋጀቱን አስታወቀ። መንፈሳዊውን ጉዞ ለማሳለጥ ከ30 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ባለሙያዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይጓዛሉ። የእምነቱ ተከታዮች በጉዞ ወቅት የሚያዳምጡት ተክቢራ ተዘጋጅቷል። 

https://p.dw.com/p/3LoWI
Saudi-Arabien - Beginn des Hadsch
ምስል Reuters/Z. Bensemra

የዘንድሮው ሐጅ ነሐሴ ይደረጋል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለአመታዊው የሐጅ ጸሎት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለማጓጓዝ ከ228 በላይ በረራዎች ማዘጋጀቱን አስታወቀ። አየር መንገዱ እንዳለው በዚህ አመት ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ከ40 ሺሕ በላይ ምዕምናን ለሐጅ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያጓጉዛል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ከዚህ ቀደም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ባደረጓቸው ጉዞዎች እንግልት ይገጥማቸው እንደነበር ይናገራሉ። 

በመጪው ነሐሴ  ስለሚደረገው መንፈሳዊ ጉዞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት መንፈሳዊውን ጉዞ ለማሳለጥ ከ30 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ባለሙያዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይጓዛሉ። የእምነቱ ተከታዮች በጉዞ ወቅት የሚያዳምጡት ተክቢራ ተዘጋጅቷል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በሳዑዲ አረቢያ ያለው መሠረተ-ልማት በተጓዥ ምዕምናን ቁጥር መብዛት ምክንያት ቢጨናነቅም ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ ነን ብለዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሐጅ ሙፍቲ መሐመድ ኢድሪስ «የዘንድሮው ሐጅ የተቃና እና ሕዝቡን የሚያረካ» ይሆናል የሚል ተስፋቸውን አሰምተዋል። 

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ
ሸዋዬ ለገሠ