1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የዕድገት ተምኔት ፣

ማክሰኞ፣ የካቲት 2 2002

ኢትዮጵያ ካለፈው ሐምሌ 2001 እስከ መጪው ሰኔ ወር ማለቂያ ኤኮኖሚዋ 10,1 ከመቶ ዕድገት ያሳያል ሲሉ በግብርና ሚንስቴር የልማት አቅድና ምርምር ክፍል ኀላፊ ፣ አቶ ጌታቸው አደም ጣሂር፣ በትንንቱ ዕለት ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/Lu3N
ምስል AP

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በዚህ አኅዝ አይስማማም። ነጻ የኤኮኖሚ ተንታኞችም የተጋነነ መሆኑን ነው የሚናገሩት። በለንደን ብሪታንያ ፣ የኤኮኖሚ ምርምር ተቋም ፣ ከሰሃራ በስተደቡብ የአፍሪቃ ክፍል ኀላፊ ፕራትሂባ Thaker ን በማነጋገር ተክሌ የኋላ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

ኢትዮጵያ፣ 80 ሚልዮን ህዝብ ያላት ፣ የህዝቧም ዓመታዊ የነፍስ-ወከፍ ገቢ፣ በኦለም ውስጥ እጅግ አነስተኛ የሆነ ፣ማለትም አማካዩ ዓመታዊ ገቢ 90 ዶላር ያህል ሲሆን ፣ 80 ከመቶ ገደማ የሚሆነው ህዝቧ ፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ምርት በሚገኝበት ጥንታዊ የአስተራረስ ዘዴ የተሠማራ መሆኑ ነው የሚነገረው ። ምንም እንኳ፣ አገሪቱ በተፈጥሮ ድሃ ባትሆንም ለፈጣን ዕድገት የሚያበቃትን ሥርዓት በመትከል ረገድ ገና እንዳልተሟላ፣ ዜጎቿ፣ የሚከራከሩበት ጉዳይ እንደሆነ ነው የሚገኘው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፣ የሆነው ሆኖ፣ ባለፉት 5 ዓመታት አገሪቱ ቀጣይነት ያለው ፣ ከሞላ ጎደል ከ 10 ከመቶ ያላነሰ ዕድገት ስታስመዘገብ ቆይታለች በማለት በየጊዜው ይገልጣል። ይህን አባባልም፣ ትናንት በግብርና ሚንስቴር የልማት አቅድ የምርምር ጉዳይ ኀላፊ አቶ ጌታቸው አደም ጣሂር ፣ ካለፈው ሐምሌ አንስቶ እስከመጪው ሰኔ 10,1 ከመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት ይገኛል ሲሉ ደግመውታል። ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ጠበብት ምን ይላሉ? በለንደን ፣ ብሪታንያ፣ የኤኮኖሞ ምርምር ተቋም ፣ ከሰሃራ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ኀላፊ ወ/ሮ ፕራቲብሃ ‘ታከር ---

«10 ከመቶ በጣም ተምኔታዊ ግብ ነው በተለይ ለይቼ እንዳስረዳሁት ኤኮኖሚው አሁንም ቢሆን በእጅጉ የግብርና ጥገኛ ነው ። ባለፈው ዓመት በግብርናው ዘርፍ የተከናወነውን መሠረት በማድረግ እኛ ማለትም የኤኮኖሚ ምርምር ተቋማችን ዕድገቱ እ.ጎ.አ በ2009 እንደነበረው በ2010 ም 7 ከመቶ ይሆናል ብሎ ነው የሚጠበቀው ። ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መድከምም በመጀመሪያ ያጋጠመ መሆኑ የታወቀ ነው ። በተጨማሪም የምርት ሽያጭ እንድሁም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች የሚልኩት ገንዘብ በመቀነሱ ባለወረቶች እንደሚፈለገው ግንዘባቸውን ሥራ ላይ በማዋላቸው አሁንም ቢሆን ዕድገቱ ከእክል ሳይላቀቅ ይቀጥላል ።»

ወ/ሮ ፕራቲብሃ ታከር በተለይ በዋናው ዓመታዊ የአዝመራ መሰብሰቢያ ወቅት፣ ምናልባት የታሰበውን ያህል ምርት የተገኘ አይመስልም፣ ያም ሆኖ ግብርናውን በማሻሻል፣ በአፈር ማዳበሪያ ትክክለኛ አጠቃቀም፣ በወንዝ ግድቦችና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማስፋፋትና የኅይል ምንጭን ችግር በማቃለል፣ ለኤኮኖሚው ማካካሻ የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል ይላሉ። ይሁንና ፣ ይህ 10 ከመቶ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችል አይደለም ፤ 10 % ዕድገት የሚኖራቸው፣ በነዳጅ ዘይት ሀብት የሚጠቀሙ እንዲሁም የማዕድን ሥራ ያስፋፉ አገሮች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ማላዊ ወይም ዛምቢያ ይህን ማከናወን እንደሚችሉ ይገመታል ነው ያሉት። ከኢትዮጵያ ግን ይህ የሚጠበቅ አይደለም፤ ከተሣካ፣ በመጪው ዓመት ወይም ዘንድሮ 8 ከመቶ ዕድገት ሊገኝ ይችላል ሲሉም፣ የለንደኑ የኤኮኖሚ ምርምር ተቋም ፣ ከሰሃታ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ተጠሪ አስረድተዋል። ስለመገናኛና የገንዘብ ተቋማት ተሃድሶም የተባለውን አስታከው እንዲህ ነበረ ያሉት--

«በመርኅ ደረጃ፣ አንዳንድ የተሃድሶ ለውጥ ለማስተዋወቅና ለባለወረቶች ክፍት እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና ገና ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው። አዎ ስለመገናኛና ስለገንዘብ የተቋማት ዘርፍም ተነግሯል። ግን ወደፊት የሚታይ ይሆናል። በአንድ መዓልትና ሌሊት የሚከናወን አይደለም ። ይህ እንዲሣካ፣ የፖለቲካ ጽኑ ፍላጎትንና አቋምን ይጠይቃል።»

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ