1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ የወደብ ሽርክና

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 24 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት በጅቡቲ ወደቦች ልማት በሽርክና ሊሳተፍ ዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል። ጅቡቲ በምላሹ በኢትዮጵያ በመንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች እና የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ባለድርሻ ትሆናለች። ተንታኞች ሥምምነቱ ፍሬ ከያዘ ለሁለቱም የሚበጅ ነው ባይ ናቸው። 

https://p.dw.com/p/2x3l2
Dschibuti Hafen
ምስል DW/J. Jeffrey

ጅቡቲ ቴሌኮምን በመሳሰሉ ተቋማት ሸሪክ ትሆናለች

ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደቦች ሽርክና ልትጀምር ዝግጅት ላይ ትገኛለች። የወጪ እና የገቢ ንግዷ በጅቡቲ ላይ ጥገኛ የሆነባት ኢትዮጵያ አማራጭ ማማተር ከያዘች ብትቆይም አሁን ግን ፍለጋዋ የጠነከረ ይመስላል። ከጥቂት ወራት በፊት የዱባዩ ዲፒ ወርልድ በሚያስተዳድረው የበርበራ ወደብ 19 ከመቶ ድርሻ ከእጇ ያስገባችው ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ጅቡቲ አዙራለች። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደቦች ልማት በምትሳተፍበት ሁኔታ ላይ ከሥምምነት ደርሰዋል። አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ምኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ ወደ ፊት በሚፈፀም ሥምምነት መሠረት ጅቡቲ በኢትዮጵያ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ባለድርሻ እንድትሆን እድል እንደሚሰጣት ገልጸዋል። 

በጅቡቲ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ አዴቦ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ጉዳዩ «በይፋ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰፊው የተጠየቀ እና በሁለቱ መሪዎች ደረጃ ንግግር የተደረገበት» ነው። አምባሳደሩ እንደሚሉት የወደብ ሽርክና ጉዳይ «ቀደም ሲል አልታሰበም» ነበር። ኢትዮጵያ ባለ ድርሻ የምትሆንበት ወደብም ይሁም መጠን ለጊዜው በይፋ አለመታወቁንም አክለው ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ 95 ከመቶ ሸቀጦቿን ከምታጉዝበት የጅቡቲ ወደብ ጥገኝነቷ ለመላቀቅ አማራጭ ስትፈልግ ቆይታለች። የሱዳን፣ በሶማሌላንድ የበርበራ እና በኬንያ የሞምባሳ ወደቦች ፍላጎቷን ከዚህ ቀደም ፍላጎቷን ያሳየችባቸው ናቸው። በአወዛጋቢው የበርበራ ወደብ ኢትዮጵያ 19 ከመቶ ባለድርሻ ሆናለች።

በአፍሪቃ የጸጥታ ጥናት ተቋም በአማካሪነት የሚያገለግሉት ሲሞን አሊሰን "ኢትዮጵያ ኤኮኖሚዋ ባደገ ቁጥር ግብይቷን የምታቀላጥፍበት የንግድ መሥመር እጅግ ያስፈለጋት ይመስለኛል። አገሪቱ በተቻላት መጠን የተለያዩ አማራጮች እንዲኖሯት ለማረጋገጥ ጥረት ላይ ትገኛለች። ይኸን ለማድረግ ሁነኛው መንገድ በወደቦቹ ባለድርሻ መሆን ነው። ከዚህ ቀደም በሶማሌላንድ በሚገኘው የበርበራ ወደብ የኢትዮጵያ መንግሥት 19 በመቶ ባለድርሻ ሆኗል። መጠኑ ምን ያክል እንደሆነ ባይታወቅም በጅቡቲ የዱራሌሕ የኮንቴነር ወደብ ባለድርሻ ለመሆን እየሞከረች ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ የሚከወነው በጅቡቲ በኩል በመሆኑ ወደቡ ሥራውን በተገቢው መንገድ የመቀጠሉ ነገር ለአገሪቱ መፃኢ ጊዜ እጅጉን ጠቃሚ ጉዳይ ነው።" ሲሉ ይናገራሉ። 

23.02.2013 DW online Karte Djibouti eng

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሰ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ የደረሰው ወደብ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ሆኖበት ሳይሆን አይቀርም የሚል እምነት አላቸው። ተንታኙ እንደሚሉት መንግሥት በብቸኝነት ባለቤት በሆነባቸው የቴሌኮም እና የአየር መንገድ ኩባንያዎች ጭምር ለሽርክና መዘጋጀቱ የፖሊሲ ለውጥ ለመኖሩ የሚጠቁመው ነገር የለም። 

በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረገው ሽርክና ወይም የድርሻ ልውውጥ የኤኮኖሚ ትሥሥራቸውን ያጠናክራል ሲሉ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። የሥምምነቱ ተግባራዊነት ሁለቱ አገሮች ያቋቋሙት ኮሚቴ በሚያቀርበው ምክረ-ኃሳብ ላይ የሚወሰን ቢሆንም ከወዲሁ ፖለቲካዊ ይሁንታ ያገኘ ይመስላል።  አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ አዴቦ እንዳሉት ሐሳቡ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌሕ በሚመሩት የጅቡቲ መንግሥት በኩል አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌሕ ጉዳዩ «ሊፈለግ በሚችል ጊዜ ፈጥኖ እንዲፈጸም» አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በትክክል ድርድሩ ተጠናቆ ተግባራዊ የሚደረግበት ጊዜ ባይታወቅም። ኢትዮጵያ በጅቡቲ ላይ የመደራደር አቅሟን አሳድጋለች የሚሉት አቶ ቻላቸው ስምምነቱ ለሁለቱም አገሮች ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ግን እምነታቸው ነው። 

የጅቡቲ ኤኮኖሚ በአብዛኛው ከወደብ አገልግሎት በሚገኝ ገቢ ላይ ጥገኛ ነው። ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ባላቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሐብታቸው ጭምር አንዳቸው ለሌላቸው አስፈላጊ መሆናቸውን ሲሞን አሊሰን ይናገራሉ። የዱባዩ የወደብ አስተዳዳሪ ኩባንያ ዲፒ ወርልድ በሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ ሥራ ሲጀምር ከጅቡቲ መቃቃሩን ተንታኙ ያስታውሳሉ። በበርበራ ወደብ ኢትዮጵያ 19 ከመቶ ባለድርሻ መሆኗ ደግሞ የፕሬዝዳንት ጉሌሕን መንግሥት ያሳሰበ እርምጃ ነበር። የጉሌሕ መንግሥት በጅቡቲ የዱራሌሕ ዓለም አቀፍ የኮንቴነር ወደብን ለማስተዳደር ከዲፒ ወርልድ ጋር የገባውን ውል አፍርሶ ውዝግቡ ፍርድ ቤት ደርሷል። ተንታኙ የአሁኑ ሥምምነት ጅቡቲ የተጫናትን  ቅሬታ እና ሥጋት የሚቀርፍ እርምጃ አድርገው ይቆጥሩታል። 

"ለጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖር ጠንካራ የንግድ ግንንኙነት እጅጉን ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ። ጅቡቲ ከወደቦቿ በምታገኘው ገቢ ላይ ጥገኛ የሆነች አገር ነች። ይኸ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ እና በሚወጡ ሸቀጦች ላይ ማለት ነው። ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኑነት ትፈልጋለች። የጅቡቲ መንግሥት በበርበራ ወደብ ላይ ኢትዮጵያ  ስምምነት ስትፈርም ሥጋት ተጭኖት ነበር። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በርከት ያሉ ሸቀጦቿን ከጅቡቲ ይልቅ በሱማሌላንድ በኩል ታጓጉዛለች የሚል ጥርጣሬ ነበራቸው። ይኸ ደግሞ ጅቡቲ በምታገኘው ገቢ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ስለዚህ ይኸ ጅቡቲ ወደቦቿ ለጎረቤቷ ሸቀጦች ተመራጭ ማጓጓዣ ሆነው እንዲቀጥሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የጠበቀ እና የተሻለ ግንኙነት ለመመስረት የሚያደርገው ጥረት ምልክት ነው ብዬ አስባለሁ።" 

ጅቡቲ ልዕለ-ኃያላኑ የጦር ሰፈር ፍለጋ የሚተራመሱባት ከሆነች ሰነባብታለች። አቶ ቻላቸው ታደሰም ይሁኑ ሲሞን አሊሰን አገሮቹ ወደ ጅቡቲ ያቀኑበት ምክንያት ወታደራዊ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር እንደማይቃረን ይስማማሉ።

Dschibuti US-Militärstützpunkt "Camp Lemonnier"
ምስል Imago/StockTrek Images

ሲሞን አሊሰን"ብዙ ውድድር ይኖራል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም በጅቡቲ የሚገኙ ልዕለ-ኃያልን በዚያ የሚገኙት በተለየ ምክንያት ነው። በዚያ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቻይና ፤ ፈረንሳይ እና ጣሊያን የጦር ሰፈር  አላቸው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጅቡቲ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ሥልታዊ አቀማመጥ ነው። ጅቡቲ ለእነዚህ አገሮች ጠቃሚ የንግድ አጋር አይደለችም። የኢትዮጵያ ትኩረት በአንፃሩ ጅቡቲን እንደ ንግድ ማሸጋገሪያ የሸቀጥ ግብይቷን ለማስወጣት  በመጠቀም ነው። ስለዚህ በወታደራዊ ምክንያት በዚያ በሚገኙት ልዕለ-ኃያላን እና በኤኮኖሚያዊ ምክንያት ወደ ጅቡቲ ባማተረችው ኢትዮጵያ መካከል ምንም  ነገር የሚፈጠር አይመስለኝም" ሲሉ ያስረዳሉ። 

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ