1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ወታደሮች ከኤልቡር መውጣት

ረቡዕ፣ መጋቢት 27 2009

የኢትዮጵያ ወታደሮች ኤልቡር የተባለችውን የሶማሊያ ከተማ ከሦስት ቀናት በፊት ለቀው እንደወጡ ከተማይቱ የሶማሊያን መንግሥት በሚወጋው በአሸብብ ቁጥጥር ስር መውደቋ ተዘግቧል ። ወታደሮቹ ከተማይቱን ለምን ለቀው እንደወጡ ግልጽ አይደለም። የዶቼቬለ የመቅዲሾ ዘጋቢ ወታደሮቹ ከከተማይቱ ይውጡ እንጂ ከተማይቱ በምትገኝበት ግዛት ውስጥ ነው ያሉት ይላል ።

https://p.dw.com/p/2ajZK
Somalia al-Shabaab Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Sheikh Nor

Withdrawal of Ethiopian forces from Elbour - MP3-Stereo

ባለፈው ሰኞ በሶማሊያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን እንደተያዘች የተነገረው ኤልቡር ፣ጋልጋዱድ በተባለው የሶማሊያ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ከተማ ናት ። ቀድሞ የንግድ ማዕከል የነበረችው ማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ የምትገኘው ይህች ከተማ ከሦስት ዓመት በፊት የአሸባብ ጠንካር ይዞታ ነበረች ።  የዛሬ ሦስት ዓመት አሸባብ ፣ በአፍሪቃ ኅብረት ሥር በዘመተው የኢትዮጵያ ኃይል ከተማይቱን ለቆ ከወጣ ወዲህ አልተመለሰም ነበር ።ሆኖም ከሦስት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች ኤልቡርን ለቀው ከወጡ በኋላ  ባለፈው ሰኞ አሸባብ ወደ ከተማይቱ ተመልሶ የኤልቡርን ፖሊስ ጣቢያ እና የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች መቆጣጠሩ ተዘግቧል ።የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተማይቱን ለቀው እንደሚወጡም ሆነ የወጡበት ምክንያት እንዳልተነገራቸው አንድ የሶማሌ ባለሥልጣን ተናግረዋል ። የዶቼቬለ የመቅዲሾ ወኪል ሞሐመድ ኦማር ሁሴን የኢትዮጵያ ኃይሎች ከተማይቱን ለቀው ቢወጡም ከተማይቱ በምትገኝበት ግዛት ውስጥ ነው ያሉት ይላል ።

«የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ የአፍሪቃ ኅብረት ጦር ስር ነው የዘመቱት ስለዚህ በግዛቲቱ ውስጥ ወደ ማንኛውም ስፍራ ሊዘዋወሩ ይችላሉ ። ከተማዋ የምትገኝበትን ግዛት ሙሉ በሙሉ ለቀው አልወጡም ። በዚያው ግዛት በሌላ ቦታ ነው ያሉት ። እነርሱ ከተማዋን ለቀው እንደወጡ አሸባብ አልቡርን ተቆጣጠረ »

የሶማሊያው ባለሥልጣን እንደተናገሩት አሸባብ ከተማይቱን የያዘው ያለአንዳች ውጊያ ሰኞ ማለዳ ነው ። የአሸባብ ኃይሎች የአየር መቃወሚያ በተተከለባቸው ከ6 በላይ በሚሆኑ መኪናዎች ወደ ከተማይቱ መግባታቸውን እና ስልታዊ ቦታዎችን መያዛቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል ። የኢትዮጵያ ኃይሎች ጥለዋት የወጡት ኤልቡር ማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ ቁልፍ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ይገኝባት የነበረች ከተማ ናት። ከኢትዮጵያ ጦር ጋር የተወሰነ ቁጥር የነበራቸው የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ወታደሮችም  አብረው መውጣታቸው ተነግሯል ። አሸባብ ኤልቡርን መልሶ በመያዝ የሚቆጣጠራቸውን ከተሞች ቁጥር ቢያንስ በአንድ አሳድጓል ። ይህ የቡድኑ ጥንካሪ መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ ይሆን ? የዶቼቬለ ዘጋቢ መሐመድ ኦማር ሁሴን እንደሚለው ቡድኑ እየተጠናከረ ቢሆንም ችግሮች አሉበት ።

«አዎ አሸባብ እየተጠናከረ ነው ። በሶማሊያ አንዳንድ ከተሞችን ፣አካባቢዎችን ተቆጣጥሯል።ይሁን እና ጥንካሬው እንደ ቀድሞ አይደለም ። ቁጥራቸው ሲታይ ደህና ነው ። ሆኖም አሁን ወታደራዊ አቅርቦቶች የጦር መሳሪያዎች በቀላሉ አያገኙም ። አሁን ወደቦች በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው። በፊት ግን  በኪስማዩ እና በሌሎችም የባህር በሮች ያስገቡ ነበር ። አህን ግን አቅርቦት የላቸውም ።»

ሆኖም ይህ ቡድኑ በሶማሊያ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶችን ከመፈፀም አላገደውም ። ዛሬ መሀል መቅዲሾ ለተጣለው እና ሰባት ሰዎች ለተገደሉበት በመኪና የተቀመጠ ቦምብ ፍንዳታ እስከ ዛሬ ረፋድ ድረስ ሃላፊነቱን የወሰደ ባይኖርም በጥቃቱ አሸባብ ተጠርጥሯል ።ኢትዮጵያ በሶማሊያ የአፍሪቃ ህብረት ጦር ስር ካዘመተቻቸው ወታደሮች በተጨማሪ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር ባላት ውል መሠረት ሶማሊያ የሚገኙ ወታደሮች አሏት ።በአፍሪቃ ኅብረት ስር የዘመቱት የኢትዮጵያ ወታደሮች ቤይ ባኩል እና ጌዶ ከተባሉት የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ግዛቶች በተጨማሪ አንዳንድ ከተሞችን እየያዙ ለቀው በሚወጡባቸው በሂራን እና በጋልጋዱድ ግዛቶችም አሉ ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ