1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርና የአይሁድ አዲስ ዓመት

ሐሙስ፣ መስከረም 6 2008

ኢትዮጵያውያን ቤተ- እስራኤሎች በአይሁድ አቆጣጠር መሠረት እሑድ መስከረም 2 ቀን 2008 ዓ.ም ማታ አዲሱን የአይሁድ 5776 ዓመት ጀምረዋል፡፡ «ሮሽ ሃሻናህ» በአማርኛ «ርዕስ ዓመት » ኢትዮጵያውያን ቤተ- እስራኤላዉያንን ጨምሮ አይሁዳዉያን አዲስ ዓመታቸዉን ከመስከረም 2 እስከ መስከረም 4 ቀን ማታ ድረስ አክብረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/1GYDp
Äthiopien Jüdische Gemeinde Addis Abeba "Kechene"
ምስል Teferawork Esubalew

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርና የአይሁድ አዲስ ዓመት


በአዲስ አበባ ከተማ ቀጨኔ አካባቢ በሚኘው ቤተ ሰላም ሲናጉግ «ምኩራብ» የቤተ-እስራኤል ማኅበረሰብ በተገኘበት በሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከብሯል፡፡ በእለቱ ዝግጅታችን ስለአከባበር ሥነ-ስርዓቱ እንዲሁም ስለ አይሁዳዉያን የዘመን አቆጣጠርና ከኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ወይም ባሕረ ሃሳብ ጋር ስላለዉ ተዛማጅነት የሚነግሩንን ባለሞያዎች ይዘናል።
አዲሱን 2008 ዓ.ም ከተቀበልን ዛሬ ስድስት ቀናት ተቆጠሩ፡፡ የዘመን መለወጫ በባህላዊውና ዓለማዊው ትውፊት «እንቁጣጣሽ»፣ በኢትዮጵያ ቤተ- ክርስቲያን ትውፊት «ቅዱስ ዮሐንስ» እየተባለም ይጠራል፡፡ የተሰናበትነዉ 2007 ዓ,ም በየአራት ዓመቱ እንደሚሆነዉ ጳጉሜ 6 ቀናትን ነበር የያዘችዉ፡፡ «የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከተለያዩ የዘመን አቆጣጠሮች ጋር ይዛመዳል፤ ከአይሁድ የዘመን አቆጣጠር ወይም ደግሞ «ሃሳበ አይሁድ» ጋር ይገናኛል ያሉን፤ የዘመን አቆጣጠር መምህርና ጋዜጠኛ አቶ ሄኖክ ያሬድ ፈንታ
« የኢትዮጵያ ካሌንደር ወይም የኢትዮጵያ ባህረ ሃሳብ ስንል፤ ልዩ ልዩ አቆጣጠሮችን የያዘ ነዉ። ኢትዮጵያ ስንል አይሁዱንም፤ ሙስሊሙንም ክርስትያኑንም ሌላዉንም ሁሉ ያጠቃለለ ነዉ። በዚህ ዉስጥ ባህረ ሃሳብ ብለን ስንመለከተዉ፤ አንዱ መገለጫዉ የአይሁዱ ባህረ ሃሳብ ማለትም ካሌንደር ነዉ። ይህ ሃሳበ አይሁድ የምንለዉ የዘመን አቆጣጠር መሰረት የሚያደርገዉ በፀሃይና በጨረቃ አቆጣጠር ነዉ። አይሁዶች በተለይ ወራቸዉን በጨረቃ ዓመታቸዉን በፀሃይ ይቆጥራሉ። እናም በጨረቃ አቆጣጠር መስከረም 29 ቀን አዲስ ዓመታቸዉን ያከብራሉ። ይህ ማለት፤ በፀሃይ መስከረም ሁለት ፤ በጨረቃዉ መስከረም 29 አዲስ ዓመታቸዉ ነዉ። በአይሁድ አቆጣጠርም ኢሉል 29 ነዉ። እናም ከ ማታ 12 ሰዓት በኋላ መስከረም ሁለት ቀን ወይም በአይሁድ አቆጣጠር ቲሽሪ 1 አዲስ ዓመታቸዉ ይገባል። ይህ ታድያ «ሮሽ ሃሻናህ» ይባላልl የይብራይስጡ ቃል ነዉ። በግዕዙ ርዕሰ አዉድ ዓመት ማለት ነዉ። የዓመት መጀመርያ የዓመት መነሻ።»
በኢትዮጵያ የክርስትና የእስልምናና የአይሁድ እምነቶች የዘመን አቆጣጠሮች ከጨረቃ አቆጣጠር ጋር ይገናኛሉ ያሉት የዘመን አቆጣጠር የሥነ ፈለክ ምሥጢር መምህር አቶ ሄኖክ ያሬድ ፈንታ በመቀጠል
«ባህረ ሃሳብ ስንል ካሌንደር ማለታችን ነዉ። ቁጥር ያለዉ ዘመን። የክርስትና የእስልምና እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች ዘመንን ሲቆጥሩ በጨረቃ ይገናኛሉ። መሠረት አለዉ ይያያዛል። እና የኢትዮጵያ አቆጣጠር ስንል የሶስቱንም የአቆጣጠር ስልት ይይጣል። »
በአዲስ አበባ ከተማ ቀጨኔ አካባቢ በሚኘው ቤተ ሰላም ሲናጉግ «ምኩራብ» የቤተ-እስራኤል ማኅበረሰብ በተገኘበት በሃይማኖታዊ ሥርዓት በዓሉ ተከብሯል፡፡ በአዲስ አበባ በሚገኘዉ ቤተ ሰላም ሲናጉግ የቦርድ አባሉ አቶ ተፈራ ወርቅ እሱባለው ፤ እንደተናገሩት የአይሁድ 7ኛ ወር የሆነው ቲሺሪ ወር አዳም የተፈጠረበት ወር ነው፡፡ አዳም ከተፈጠረ 5776ኛ ዓመት በሌላ አነጋገርም የዓለም የልደት ቀንም ነው ። የአዲስ ዓመት አከባበር ደግሞ ይላሉ አቶ ተፈራ ወርቅ በመቀጠል፤
« የአይሁዳዉያን አዲስ ዓመት አከባበር ከኢትዮጵያ እንቁጣጣሽ አከባበር ጋር ፈፅሞ የሚገናኝ አይደለም። አይሁዳዉያን አዲስ ዓመትን የምናከብረዉ በመጸሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ መሰረት ነዉ። በአከባበሩ የመግብያ ፀሎቶች ይካሄዳሉ፤መጭዉ ዘመን የተባረከና ጣፋጭ እንዲሆን ጣፋጭ የሆኑ ነገሮችን በመብላት አዲስ ዓመትን እናከብራለን። አዲስ ዓመትን «ሾፋር» በመንፋት ማለት ቀንደ መለከት በመንፋት እናከብራለን።»
በአይሁዳዉያን አዲስ ዓመት እርድ የለም? አቶ ተፈራ ወርቅ እሱባለው « እርድ እንዳለ፤ መስዋዕት እናደርጋለን። የእስራኤል ህዝብ የበላይ እንጂ የበታች አታድርገን፤ «ራስ እንጂ ጅራት አታድርገን» በሚለዉ ስርዓቱ ከእርድ በኋላ የበጉን ጭንቅላት በመያዝ ፀሎት ይደረጋል። አምላክ በመችዉ ዘመን ራስ እንጂ ጅራት እንዳያደርገን፤ ከሁሉ በላይ እንጂ በታች እንዳያደርገን በሚል ስርዓት እርድ እናከናዉናለን እንፀልያለን።»
አዲስ አበባ ቀጬኔ አካባቢ ነዉ የምንገኘዉ ፤ አዲስ ዓመት ክብረ በዓአላችንን አብረን ተሰባስበን ነዉ ያከበር ነዉ ነዉ ያሉኝ እና፤ እንደሚታወቀዉ አብዛኞች ቤተ- እስራኤላዉያን ጎንደር አካባቢ እንደነበሩ ነዉ የሚታወቀዉ፤
« አዎ የኢትዮጵያ ቤተ-እስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ገብቶአል ተብሎ የሚታሰበዉ ከንጉሥ ሰለሞን ሞት በኋላ እስራኤል በገጠሟት ችግሮች ነዉ ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ ተሰድዋል ተብሎ የሚታሰበዉ። ከዝያ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ዉስጥ የኖረ የአይሁድ ማኅበረሰብ ነዉ። በጎንደር ይኖር የነበረዉ ይህ ማኅበረሰብ በወቅቱ በነበረዉ የተለያየ ችግር በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተበታትኖአል። አዲስ አበባ ቀጨኔ የምንገኘዉ አይሁዳዉያን ደግሞ ከተለያዩ የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ተሰባስበን ያለን ነን። ከመረሃ-ቤቴ፤ ከመንዝ ከጅሩ ፤ ከደራ፤ የመጡ በፊት ንጉሱ ይኖሩ የነበሩት እንጦጦ አካባቢ ነበር የመንግሥትን ከለላ ለማግኘት ከእንጦጦ ዝቅ ብሎ ቀጨኔ ላይ የተሰባሰቡ ማኅበረሰቦች ናቸዉ፤ እኛ ከነዚህ ማኅበረሰቦች የወጣን በመቶዎች የምንቆጠር ወጣቶች ነን።»
ሰኔ ግም ብሎ የሐሃምሌን ጨለማ ጥሎ ሄዶ የነሐሴን ጎርፍ ሙላት አልፎ መስከረም መሰስ ብሎ ሲጠባ አደይ አበባ በየቦታዉ የሚታይበት፤ አዲስ ዓመት አዲስ ዘመን አንድ ብሎ የሚጀምርበት ብቻ ሳይሆን ከባዱ ዝናብ ጋብ የሚልበት ጥቢ የሚጀምርበትም ወር ነዉ። አቶ ሄኖክ ያሬድ ፈንታ
«ኢትዮጵያን ልዩ ከሚያደርጓት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ የዘመን አቆጣጠር ስልቷ ነው። ሌሎች አቆጣጠሮች በተለይ መደበኛ ሆኖ በዓለም ዙርያ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ጎርጎርዮሳዊው ቀመር «በዘልማድ የአውሮጳውያን አቆጣጠር»ዓመቱን በ12 ወሮች ሲመድብ የኢትዮጵያ ግን 13ኛ ወር አለበት፡፡ ባለ 13 የፀሐይ ወራት አገርም ተብላ ትታወቃለች፡፡ ዘመን እንዴት ይለካል? ባሕረ ሐሳብ ቁጥር ያለው ዘመን ነው ብለናል፡፡ ዘመኑ የሚለካበት ደግሞ መሬት ከፀሐይና ከጨረቃ ዑደት ጋር ካላት ግንኙነት የሚነሣ ሆኖ፣ ዘመኑ የሚለካበትም በዕለት፣ በወርና በዓመት ነው፡፡ የዘመን መለኪያዎቹ ዐውዶች ተብለው ይጠራሉ፡፡ የእነዚህ ዐውዶች ልኬት፣ ተመላላሽ ክሥተቶች በሚመጡበት ጊዜ ወይም ዘመን ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የመጀመርያው ዐውድ «ዞሮ የሚገጥም» ዐውደ ዕለት ሲሆን፣የሰባት ቀኖች መመላለስን ያሳያል፡፡ ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት ሰባት ቀኖችን ይዟል፡፡ በዕለት የሚቆጥሩ ሌሎቹ ዐውዶች የሚመላለስባቸው ዐውደ ወርኅ በጨረቃ 29/30 ቀን፣ በፀሐይ ዘወትር 30 ቀን፣ ዐውደ ዓመት በጨረቃ 354 ቀን፣ በፀሐይ 365 ቀን ናቸው፡፡ የዓመታት መመላለስን የሚያሳዩ ሌሎች ዐውዶችም በሐሳበ ዘመን ውስጥ አሉ፡፡ እነዚህም ዐውደ ወንጌላውያን 4 ዓመት «የዓመቱ ወንጌላዊ የሚታወቅበት»፣ የፀሐይና የጨረቃ ጥምር አቆጣጠር የሚያሳየው ዐውደ አበቅቴ በ19 ዓመት የሚመላለስ፣ ዐውደ ፀሐይ 28 ዓመት «በየዓመቱ መስከረም 1 ቀን የሚውልበት ዕለት መቼ እንደሚሆን የሚወቅበት ዐውድ» እና በሌሎችም ዘመኑ ይለካል፡፡ የዓመት አቆጣጠር መነሻ መደበኛው የኢትዮጵያ ካሌንደር በፀሐይ ቀመር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መሬት በፀሐይ ዙርያ በምታደርገው የ365 ከሩብ ቀናት ጉዞ አንድ ዓመት ይገኝበታል፡፡ መነሻውን ርእሰ ዐውደ ዓመት መስከረም 1 ቀን በማድረግ ዓመቱን እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ባላቸው 12 ወሮችና ተጨማሪ 5 ቀናት፣ በየአራት ዓመቱ ግን 6 የምትሆን አንድ ትንሽ ወር የሚይዝ ነው፡፡»
በተለምዶ የእንግሊዘኛዉን ቃል ወስደን ካሌንደር የምንለዉ በአማርኛችን ባህረ -ሃሳብ እንደሚባል አቶ ኄኖክ ያሬድ ፈንታ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን በተለይ ቅዱስ ዮሐንስ በምትለው የዘመን መለወጫ ዕለት በተለያዩ የዓመት መነሻዎች በፀሐይ፣ በጨረቃ እና በፀሐይና ጨረቃ ጥምረት በማስላት፣ የዘመኑን የትንሣኤ በዓልና ከርሱ ጋር የተያያዙትን ተዘዋዋሪ አጽዋማትና በዓላትን አግኝታ ታውጅበታለች፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመደበኛው የዓመተ ምሕረት አቆጣጠሯ በተጨማሪ በተለያዩ ታሪካዊ መነሻዎችም ዘመኑን ታሰላለች፡፡ አንደኛው ዓመተ ዓለም ነው፡፡ ዓለም ከተፈጠረበት ከክርስቶስ ልደት 5500 ዓመት በፊት አንሥቶ ይቆጥራል፡፡በዚህም መሠረት በ2008 ዓ.ም ዘመኑ 7508 ዓ.ዓ. ይሆናል፡፡ ይህም ዘመኑ ስምንተኛው ሺሕ ውስጥ እንዳለን ያሳየናል፡፡ ሌላኛው የፀሐይና የጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ነው፡፡ ይህ የፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ከዐውደ አበቅቴ የ19 ዓመት መመላለስ የሚገኝ ነው፡፡ እርሱም በፀሐይ ዓመት 365 ቀንና በጨረቃ 354 ቀን ልዩነት ይገኛል፡፡ ይህ ጥምር አቆጣጠር ትንሣኤን ይዘው በሚንቀሳቀሱና ልደትን ይዘው በማይንቀሳቀሱ በዓላትና አጽዋማት መካከል ያለውን ልዩነት ይረዳል፡፡ በዚህ መሠረት መስከረም 1 ቀን የሚገባው 2008 ዓ.ም የፀሐይ አቆጣጠር ሲሆን፣ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ደግሞ 2016 ዓ.ም ይሆናል፡፡ በምንቀበለው 2008 ዓ.ም ፋሲካ ሚያዝያ 23 ቀን እንደሚውል ያወቅነው፣ በ2016 አስልተን እንጂ በ2008 አይደለም፡፡ እንዲሁም በፀሐይ መስከረም 1 ቀን በጨረቃ መስከረም 28 ቀን መሆኑን፣ በሒጅራ ዙህልቃድ 28 ቀን 1436፣ በአይሁድ ኢሉል 28 ቀን 5775 መሆኑን ዕለታቱ በሦስቱም ሃይማኖቶች በጨረቃ አቆጣጠር የመስከረም መባቻ 28 መሆኑን ያረጋገጥነው በ2016 ነው፡፡ ስለዚህ መስከረም አንድ ቀን የእንቁጣጣሽ ዕለት በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2008ንም 2016ንም የምንቀበል መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ሁለት ዓይነት የዕለት«24 ሰዓት» መነሻም አለ፡፡ አንደኛው ከሥርዓተ አምልኮ ጋር የሚያያዘው ማታ 12 ሰዓት የሚጀመረው «ዕለተ ሊጡርጊያ» «ሊተርጂካል ዴይ» ሲሆን፣ ሌላው መደበኛው ፀሓያዊ ዕለት «ሲቪል ዴይ» የሚባለውና ጧት 12 ሰዓት የሚጀመረው ነው፡፡
አንዳንዶች የኢትዮጵያን ባህረ ሃሳብ ማለት ካሌንደር የጁልያን ሲሉ መጥራታቸዉ ፍፁም ስህተት ነዉ፤ ሌላዉ ኢትዮጵያዉያን አዲስ ዓመትን የሚቀበሉት ከለሊቱ ስድስት ማለት እኩለ ለሊት ሳይሆን ማለዳ 12 ሰዓት ላይ ነዉ ያሉት የዘመን አቆጣጠር የሥነ ፈለክ ምሥጢር መምህርና ጋዜጠኛ አቶ ሄኖክ ያሬድ ፈንታ በዝርዝር አስረድተዋል።

እኛ የመስከረም 1 ቀን 2008 ዓመተ ምሕረት መስከረም መባቻ፣ ዕለተ ዮሐንስ ቅዳሜ እንደሚውል ያወቅነው፣ መሬት ፀሐይን ዞራ ባስገኘችው ስሌት መሠረት ነው፡፡ በዚሁ ዓመት ዐቢይ ጾም «ሁዳዴ» የካቲት 28 ቀን 2008 ተይዞ ትንሣኤ «ፋሲካ» ሚያዝያ 23 ቀን ይከበራል ብለን በመስከረም መባቻ ያወጅነው አዋጅ ያገኘነው፣ በፀሐይ 2008 ሳይሆን በርሱ ላይ 8 ደምረንበት በ2016 አስልተን ነው፡፡ ስለዚህ በፀሐይ፣ በኢትዮጵያ 2008 ዓመተ ምሕረት፣ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቈጣጠር፣አሁንም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2016 ዓመተ ምሕረት፣ መስከረም 1 ቅዳሜ መሆኑን ታውቋል እንላለን፡፡ የስምንት ዓመቱ ልዩነት በሁለቱ የብርሃን መንገዶች መካከል የሚታይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፀሐይ 2008 በሁለቱ ዐበይት ብርሃናት ጥምር አቈጣጠር 2016 የተባለው ስለዚህ ነው፡፡
በእብራ ይስጥ በዘመን መለወጫ « ሮሽ ሃሻናህ » ሲባል መልካም ምኞት ይገለፃል። «ሻና ቶቫህ ዑመቱካህ» የተስማማ ጣፋጭ አዲስ ዓመት ሲባል ደግሞ መልካም ምኞት ይነገራል። ቃለ ምልልስ የሰጡንን በዶቼ ቬለ በማመስገን መልካም አዲስ ዓመት የዜና የፍቅር ዓመት ያድርግልን በማለት ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

Jüdisches Neujahrsfest
ምስል Marco Longari/AFP/Getty Images
Jüdisches Neujahrsfest
ምስል picture-alliance/dpa
Äthiopien Jüdische Gemeinde Addis Abeba "Kechene"
ምስል Teferawork Esubalew
Äthiopien Jüdische Gemeinde Addis Abeba "Kechene"
ምስል Teferawork Esubalew
Äthiopien Jüdische Gemeinde Addis Abeba "Kechene"
በአይሁዳዉያን አዲስ ዓመት ጣፋጭ ይበላል። መጭዉ ዘመን ጣፋጭ ይሆናል ተብሎም ይታመናል።ምስል Rafael Ben-Ari/Fotolia
Äthiopien Jüdische Gemeinde Addis Abeba "Kechene"
በአይሁዳዉያን አዲስ ዓመት ቀንዲል ይነፋልምስል Teferawork Esubalew
Jüdisches Neujahrsfest
ምስል picture-alliance/dpa/A. Sultan