1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የሀዘን ሳምንት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 13 2007

ራሱን እስላማዊ መንግስት «አይ ሲስ» ብሎ በሚጠራው አክራሪ ቡድን ሊቢያ ላይ ከተገደሉት ኢትዮጵያውያን መካከል የእያሱ ይኩኖአምላክ እና ባልቻ በለጠ ቤተሰቦች አዲስ አበባ በተለምዶ ቂርቆስ በሚባለው ሰፈር ድንኳን ጥለው ሃዘን ላይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/1FBzZ
Trauer um IS-Opfer in Äthiopien
ምስል DW/E. Bekele

የተሻለ የስራ እድል ፍለጋ ከኢትዮጵያ በሱዳን አድርጎ ሊቢያ የገባው እያሱ የቤተሰብ ሃላፊነት የተጣለበት ወጣት ነበር። ከዚህ ቀደም ለተወሰነ ጊዜ ኳታር በስራ ቆይቷል። «እህታችን ከሞተች በኋላ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው እሱ ነው። አልጋ ላይ ደካማ እናት አሉት። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሪን የሚማር ወንድሙንም የሚያስተምረው እሱ ነው።» በማለት የእያሱ ታላቅ ወንድም አቶ ስዩም ይኩኖ አምላክ ተናግረዋል።

እያሱ ይኩኖአምላክ እና ባልቻ በለጠ እንደ ወንድማማች የሚቀራረቡ ጓደኛሞች ነበሩ። አዲስ አበባ ላይ በነ ባልቻ ግቢ በሰሯት አንድ ክፍል ቤት አብረው ይኖሩም ነበር። «መብራት ሃይል ነው የሚሰራው» ያሉት አቶ ስዩም ደስተኛ አለመሆኑ ከጓደኛው ከእያሱ ጋር በመሆን ወደ አውሮጳ ጉዞ እንዲጀምር ሳያደርገው እንዳልቀረ ይናገራሉ።

ራሱን ‘እስላማዊ መንግስት’ ወይም «አይ ሲስ» ብሎ በሚጠራው አክራሪ ቡድን በማህበራዊ ድረ-ገፆች በለቀቀው የጅምላ ጭፍጨፋ ቪዲዮ ላይ የታዩት እያሱ እና ባልቻ የተሻለ የስራ እድል ፍለጋ የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሃሳብ ነበራቸው። ሁለቱ ወጣቶች ከኢትዮጵያ ከወጡ ሁለት ወራት አልፏቸዋል።

አቶ ስዩም ይኩኖ አምላክ «አሁን ትኬት ሊቆርጡልኝ ነውና ብሩን ባንክ አስገባልኝ ብሎኝ 90 ሺ ብር አስገባሁለት። ከዛ ደረሰኝ ብሎ ከደወለልኝ በኋላ አግኝቼው አላውቅም።» በማለት ከታናሽ ወንድማቸው ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተነጋገሩት እሱ በሊቢያ ሳለ በስልክ መሆኑን ያስታውሳሉ።

Islamischer Staat Video Christen Libyen
ምስል picture-alliance/AP Photo

29 ደቂቃ የሚረዝመው የጅምላ ጭፍጨፋ ቪዲዮ በመገናኛ ብዙሃን ከተሰራጨ በኋላ ኢትዮጵያውያን ቁጣና ምሬታቸውን በማሰማት ላይ ናቸው። በርካቶች ጥቁር ሳምንት ሲሉ ሰይመውታል። በዶይቼ ቨሌ የፌስቡክ ገጽ ላይ አስተያየታቸውን ካሰፈሩ ሰዎች መካከል ናቡቴ ይመር «በመጀመሪያ ስሰማ ልቤ ደማ የምይዘውን የምጨብጠውን አጣሁ በሁዋላ ቀስ በቀስ ሳስብ መጽናናትን አገኝሁ።» ሲሉ ጽፈዋል። ገደፋዬ ጓዴ ደግሞ «እንደመንግስት በሀገር ውስጥ የስራ ዕድል መፍጠር፣አስተማማኝ የሆነ የፖለቲካ እርቅ ማድረግ ፣አስመራሪ የሆነውንና እና በዘመድ አዝማድ መጠቃቀሚያ ያልሆነ ግብር በፍታዊ መንገድ ማስከፈል።እንደ ወጣቱ ደግሞ ስራ ሳይመርጥ በሀገር ውስጥ ደጋግሞ ለመለወጥ መጣጣር።» ሲሉ አሳባቸውን አጋርተዋል። « በአገራችን ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ይኑር፤ በአገራችን በቂ የስራ እድል ይፈጠር፤ የተፈጠረውም የስራ እድል በዘር በብሄር እና በፖለቲካ አመለካከት እየተመረጠ አይሰጥ» የሚል አስተያየት ያሰፈሩት ደግሞ አብይ አይ የተባሉ የማፍበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚ ናቸው።

አዲስ አበባ ውስጥ በኢትዮጵያውያኑ ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ በመቃወም እና ፍትህ በመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉ ተሰምቷል። በኢትዮጵያውያኑ ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ የጅምላ ግድያ በጓደኛው በኩል የሰማው ወጣት ከሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች« ከለቅሶ ቤት ከድንኳኑ ተነስተን ውጭ ጉዳይ ሄድን። ከውጪ ጉዳይ ደግሞ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጸሎት አድርገን ከዛ አፍሪቃ ህብረት ለመሄድ ነበር ሃሳባችን።ፌዴራል ፖሊሶች አናስኬድም አሉን።ከዛ ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሰን መጥተን ጸሎት አድረገን አሁን ለቅሶ ቤት አካባቢ ነው ያለንው።» በማለት ሁኔታውን ለዶይቼ ቨሌ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም በውጭ አገራት የሚገኙ ስደተኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ መንግስታቸው ሃላፊነት እንዳለበት ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ተናግረዋል።

ዛሬ ጠዋት ወደ ሐዋሳ የተጓዘዉ የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ዮሐንስ ገብረ-እግዚ አብሔር እንደዘገበዉ ደግሞዉ በጉዘዉ መሐል ያየ፤ያጋጠመዉ መንገደኛ የሐዘንና የቁጭት ስሜት የሚፈራረቅበት ነበር።እዚያዉ ሐዋሳ ያነጋገራቸዉ የከተማይቱ ነዋሪዎችም በኢትዮጵያዉያኑ ላይ የተፈፀመዉን አሰቃቂ ግድያ አዉግዘዉ የኢትዮጵያን መንግሥት በአሸባሪዉ ቡድን ላይ «ተመጣጣኝ» ያሉትን እርምጃ ለመዉሰድ አላስታወቀም በማለት ቅሬታቸዉን ገልፀዋል። ሙሉ ዘገባዉን እነሆ።

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረ እግዚ አብሔር

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ