የኢትዮጵያ የባህል ቀን በለንደን ሙዚየም

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:40 ደቂቃ
07.10.2018

የኢትዮጵያ የባህል ቀን በቪክቶርያ እና አልበርት ሙዚየም

በለንደን የሚገኘው የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም ከ150 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ከተዘረፉ ቅርሶች መካከል የተወሰኑትን መርጦ ባለፈው ሚያዝያ ወር ለህዝብ ዕይታ ማብቃቱ ይታወሳል። ከመቅደላ በተዘረፉት ቅርሶች ውዝግብ ውስጥ የሰነበተው ሙዚየሙ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የኢትዮጵያ የባህል ቀንን አዘጋጅቶ ነበር።

በታላቋ ብሪታንያ መዲና ለንደን በሚገኛው በቪክቶርያ እና አልበርት ሙዚየም ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ. ም. ከቀትር ጀምሮ የኢትዮጵያ የባህል ቀን ሆኖ ነበር የዋለው። “ወደ ብርሀን የኢትዮጵያ ባህላዊ ቀን በሚል መጠሪያ” በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የቀረበው ዝግጅት ዓላማው መቅደላን ማስታወስ በሚል ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ከኢትዮጵያ ከተዘረፉ ታሪካዊ ቅርሶች የተወሰኑትን ለህዝብ ዕይታ በማቅረቡ ተጨማሪ ጎብኚዎችን ለማግኛት በማሰብ ነው።

ሙዚየሙ ቅርሶቹን ለአውደ ርዕይ ያበቃቸው የእንግሊዝ ጦር ድልን 150ኛ ዓመት በማስታወስ ነበር። ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ሃገሬ በጠላት እጅ ስትወድቅ ከምመለከት ብለዉ ራሳቸዉን በ1868 ዓ.ም ከሰዉ በኋላ ከመቅደላ አምባ ላይ የእንግሊዝ ጦር አበጋዞች በርካታ ብርቅ እና ድንቅ ቅርሶችን በ15 ዝሆኖች እና ከ200 በላይ በሚሆኑ በቅሎ በማስጫን ዘርፈው ወስደዋል። በሌተናንት ጄነራል ሰር ሮበርት ናፒየር የተመራው የእንግሊዝ ጦር በወቅቱ አቢሲንያ ትባል የነበረውን ኢትዮጵያን ሲዘርፍ የወሰዱት ውድ ቅርሶችን ብቻ አልነበረም። በሕጻንነታቸዉ ተማርከዉ ብሪታንያ ዉስጥ በ18 አመታቸው የሞቱት የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን ጭምር እንጂ።

ይህ ከሆነ ከ150 አመት በኋላ በተመሳሳይ ወር ቪክቶርያ እና አልበርት ሙዝየም ባለፈው ሚያዝያ ወር በወቅቱ ከተዘረፉት ቅርሶች መካከል የተወሰኑትን በመምረጥ ለዓመት ያህል ለህዝብ በነፃ እንዲጎበኙ አድርጎዋል። መዚየሙ ለዕይታ ካቀረባቸው ታሪካዊ የሀገራችን ቅርሶች መካከል ከፍተኛ ዋጋ ያለው ከ 18 ካራት ወርቅ የተሰራ ባለሶስት እርከን የወርቅ ዘውድ አንዱ እና ዋነኛው ነው።

የወርቅ ፅዋ፣ አፄ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ በብሪታንያ ወታደሮች የተቀበሩበት አቅራቢያ የሚገኛው የቅዱስ መድኃኒያለም ቤትክርስቲያን ፎቶ፣ የአፄ ቴዎድሮስ ባለቤት የእቴጌ ጥሩነሽ በጥልፍ የተዋበ ቀሚስ፣ ሁለት የተለያዩ የአንገት ጌጦች፣ የእጅ አምባሮች እና የእግር አልቦዎች፣ የልዑል አለማየሁ ፎቶ፣ የተለያየ ቅርፅና መጠን ያላቸው አምስት የብር እና የነሀስ ጥንታዊ የእጅ መስቀሎች፣ በእጅ የተጻፉ ሶስት መካከለኛ እና አንድ ትልቅ የብራና መፀሃፍት ይገኛበታል። ይህ ቁጥር በሌላኛው የሙዝየሙ ክፍል ለዕይታ ቀርበው ያሉትን መስቀሎች እና ታሪካዊ የብራና  መፀሀፍትን አይጨምርም።

ሙዝየሙ የጎብኚዋቹን ቁጥር ለመጨመር ያዘጋጀው የኢትዮጵያ የባህል ቀን ዘጠኝ ትዕይንቶች ቀርበውበታል። ድምፃዊት ሀይማኖት ተስፋ በተስረቅራቂ ድምፅዋ በክራር በመታጀብ ያማረ መዚቃዋን ለጎብኚዋች በማቅረብ ነበር ዝግጅቱ የተጀመረው። ታዳሚዎች መሬት ላይ ተቀመጠው በአማረ የመዚቃው ልስላሲ ተዝናንተው እና በጥሞና አዳምጠው  ሲጨርሱ የመረጡትን ያደርጉ ዘንድ የተለያዩ ዝግጅቶች ምርጫ ነበራቸው።  ስዕል መሳል፣ ቀለም መቀባት አና በአማርኛ ስማቸውን መፃፍ የፈለጉ ለእዚሁ ወደተዘጋጀው ክፍል ይገባሉ። በዚህ ክፍል በአብዛኛው የሚታዩ የነበሩት አዳጊ ልጆች ናቸው። አዳጊዎቹ የሚያውቁትን አማርኛ ለመናገር፣ ለመፃፍ እና ቀለም ለመቀባት በደስታ ሲቸኩሉ አይቻለሁ።

“ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ በአፍሪካ እንደምትገኝ እናውቃለን። እኛም ራሳችን አፍሪካዊ ነን” ሲሉ የነገሩኝ አንዲት እናት ናቸው። “ከምዕራብ አፍሪካ ነው መሰረታችን። ስለኢትዮጵያ በአፍሪካ የት ቦታ እንደምትገኝ ከማወቃችን በስተቀር በእውነት ብዙ የምናውቀው ነገር አልነበረም ።ያው ቅዳሜ እንደመሆኑ ልጆቻችንን ይዘን ሙዚየም ለማየት መጣን። እዚህ ስንደርስ የኢትዮጵያ ባህል ቀን መሆኑ ተነገረን። ወደውስጥ ስንገባ አንዲት ድምፅ መልካም ሴት በአማርኛ ስታዜም ሰማን። ወደውስጥ ስንገባ ደግሞ ልጆች የተለያዮ የኢትዮጵያ ስእሎችን ቀለም ቀቡ። የተለያዩ ዲዛይኖችን መስራት ቻሉ። ከዚህም በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በ አማረርኛ ፊደል ስማቸውን በመፃፍ ባጅ በመስራት ወደቤታቸው ለመውሰድ ችለዋል። በዚህም ደስተኞች ናቸው” ሲሉ ገልፀዋል።

የሚቀጥለው አውደ ትርዒት ደግሞ የእቴጊ ጥሩነሽን የመዋቢያ ጌጣጌጦችን መነሻ በማድረግ አስመስሎ መስራት ነበር። መልሰው ሊያገለግሉ በሚችል ቁስ መስቀል አልያም የእጅ አንባር በመስራት በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና በማደጎ የማጡ ልጆች ተሳትፈዋል። የሰሩትን ጌጥ ወደቤት መውሰድ መቻላቸው ደግሞ ልጆቹን የበለጠ ደስተኛ አድርጓቸዋል።

ዘመናዊውን የኢትዮጵያ ስነጥበብ እና የሰዓሊዎች ስራ በሚያቀርበው በአዲስ ፋይን አርት መስራች ራኬብ አማካኝነት  የኢትዮጵያን የስነ -ጥበብ ዕድገት የሚያሳይ ዝግጅትን ቀርቦ ነበር። ራኬብ ስለ ኢትዮጵያ የስዕል ስራ እና ሰዓሊዎች ስትናገር “ሀገራችን በጥንት ታሪኳ ትታወቃለች። ዘመናዊውን የስዕል ስራ ማስተዋወቅ ደግሞ የእኛ ድርሻ ነው” ብላለች። በተለያዩ የሙዚየሙ ክፍል የሚገኙትን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶችንም በባለሙያ ጉብኝት ተደርጓል።

በየመሀሉ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ ለሻተ ደግሞ በጎርጎሮሳዊው 1856 ዓ. ም. ወደ ተገነባው የሙዝየሙ ምግብ ቤት ጎራ ብሎ እንዲያገኝ ተመቻችቷል። በመጨረሻም ዳንኪራ በተሰኛው የኢትዮጵያ የባህል ቡድን የተለያዩ የኢትዮጵያን ባህላዊ መዚቃ ትርዕኢት ከማሳየቱም በላይ መሰረታዊውን የሙዚቃ እንቅስቃሴ ጭፈራችንን አጭር ስልጠና ሰጥቷል።

በሙዚያሙ የተገኙት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ቅርሶችን የሚያሳየዉ ዓዉደ ርዕይ ለንደን ላይ በመከፈቱ ደስታም፤ ሀዘንም እንደተሰማቸው ነው የገለፁልኝ። ደስታው የኢትዮጵያን ቅርስ እንዲህ በክብር፣ ባማረ ወግ ማየታቸው ሲሆን ሀዘኑ በወቅቱ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችው ላይ የደረሰው ስቃይ አሁን ደግሞ የእዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤት የነበረችው ሀገራችን ሀብቷን መሰብሰብ የምትች ሆና አለመገኘተዋ እንደሆነ ገልፀውልኛል።

ሐና ደምሴ 

ተስፋለም ወልደየስ 

ተከታተሉን