1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እና የውጭ ባለወረቶች ጥያቄ

Eshete Bekeleረቡዕ፣ ጥቅምት 24 2008

የጀርመኑ ኮሜርስ፤የዩናይትድ ስቴትሱ ሲቲ እና የኬንያው ንግድ ባንኮች በአዲስ አበባ ቢሮ የመክፈት እቅድ ሰንቀዋል። በኢትዮጵያ ቢሮዎቻቸውን የከፈቱት የውጭ ኩባንያዎች ግን በዘርፉ ያለምንም ገደብ የመስራት ፈቃድ የላቸውም።

https://p.dw.com/p/1H0EK
Geld Bank Symbolbild
ምስል Fotolia/Pefkos

የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እና የውጭ ባለወረቶች ጥያቄ

የባንኮቹ ሃሳብ ምን አልባት ወደ ወደፊት ለውጭ አገራት ኩባንያዎችና ባለወረቶች ሊከፈት ይችላል ብለው ተስፋ ባደረጉበት የባንክ አገልግሎት ጥናት ከማካሄድ ያለፈ እንቅስቃሴ እንደሌላቸው የኢኮኖሚ ተንታኞች ይናገራሉ። ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ ዘርፉን ለውጭ ባለወረቶች ክፍት እንድታደርግ ቢወተውቱም አልተሳካላቸው።

መቀመጫውን በታላቋ ብሪታኒያ ዋና ከተማ ለንደን ላይ ያደረገው ዘ-ኢኮኖሚስት መጽሔት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ያካሄደው ጉባኤ ተሳታፊዎች ለውጭ ባለ ወረቶች ዝግ የሆኑ የአገልግሎት ዘርፎች ክፍት እንዲሆኑ ጥያቄ አንስተዋል። ጥያቄው ለአገር ውስጥ ባለ ወረቶች ብቻ የተፈቀዱትን እንዲሁም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙትን እንደ ባንክ፤ የመድሕን ዋስትናና ቴሌኮሙኒኬሽን ያሉ ዘርፎችን የተመለከተ ነው። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ካርሎስ ሎፔዝ ኢትዮጵያ የዘጋቻቸው መስኮች ወቅቱ ከሚያመጣቸው ዕድሎች ጋር ከመተላለፋቸው በፊት ክፍት እንዲደረጉ ጥያቄ ቢያቀርቡም ኢትዮጵያ ወይ ፍንክች ብላለች።

Bildergalerie Millionäre Afrika - Skyline Addis Abeba
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

በውይይቱ ትኩረት ከተደረገባቸው መካከል 16 የግልና ሶስት የመንግሥት ተቋማትን የያዘው የኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት እድገቱ፤ የገንዘብ አቅሙና የሰለጠነ የሰው ኃይል አደረጃጀቱ ውስንነቶች ይታዩበታል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችውን የኢኮኖሚ እድገት የሚያወድሱት እንደ ዓለም ባንክ፤ የአፍሪቃ ልማት ባንክና የዓለም የገንዘብ ተቋም ያሉ ተቋማት ጭምር ዘርፉ በርካታ እንከኖች እንዳሉት ይተቻሉ። የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ከውጭ ባለ ወረቶች ሊያገኛቸው የሚችላቸው ጠቀሜታዎች መኖራቸውን ይናገራሉ። እንደ ኢኮኖሚ ተንታኙ ከሆነ ከዘርፉ በተጨማሪ አጠቃላይ ኢኮኖሚውም ያለበትን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የፋይናንስ ውስንነት ከእነዚሁ የውጭ ተቋማት ሊፈታ በቻለ ነበር።

ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍን ለውጭ ባለወረቶች ለመክፈት ከጎረቤቶቿም ይሁን ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አገራት በተለየ ጥንቃቄን መርጣለች። የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ግን የበዛ ትችት በተከታታይ እንዲሰነዘርበት አድርጓል። ግሎባል ሴንተር ኦን ኮኦፐሬቲቭ ሴኪዩሪቲ (Global Center on Cooperative Security)የተሰኘ ተቋም ባለፈው አመት ይፋ ባደረገው ጥናት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዘርፉ የ70 በመቶ ድርሻ እንዳለው አትቷል። በጥናቱ መሠረት በኢትዮጵያ ለ100,000ሰዎች ያሉት ሁለት ባንኮች ሲሆኑ የኤቲኤም (ATM)ማሽኖች አቅርቦት ደግሞ 0.3 በመቶ ብቻ ነው። ይህ ከኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ አኳያ ሲታይ እንኳ አነስተኛ ነው። የአገሪቱ ባንኮች የአነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎች የሚፈልጉትን የመንቀሳቀሻ ገንዘብ የማቅረብ አቅምም የላቸውም። እንዲህ አይነት ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላሉ ከሚባሉት መፍትሄዎች አንዱ የሆነው የውጭ ባለወረቶችና ተቋማት ተሳትፎ ላይ የተጣለው ገደብና መንግሥት የወሰደው ጥንቃቄ ተገቢ ቢሆንም የበዛ ይሉታል የኢኮኖሚ ተንታኞች።

ከፍተኛ የገንዘብ አቅም፤ እውቀት፤ ቴክኖሎጂና የማስተዳደር ክህሎት ለኢትዮጵያ ሊያመጣ ይችላል የሚባለው የውጪ ተሳትፎ ለጊዜው ፈቃድ አላገኘም። በጥቂት ጊዜያት የኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ለዉጭ ባለወረት ለመከፈቱም ምልክቶች አይታዩም። አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም የኢትዮጵያ መንግሥት የአገር ውስጥ ባንኮች የመወዳደር አቅም በቅድሚያ ማደግ አለበት የሚል አቋም እንዳለው ያብራራሉ።

የውጭ ተቋማት ባላቸው ከፍተኛ የገንዘብና የሰለጠነ የሰው ኃይል ምክንያት ፖሊሲ አውጪዎችንና የመንግሥት ባለስልጣናትን በማግባባት የሚፈልጉትን ለውጥ ለማምጣት ጥረት ያደርጋሉ የሚል ስጋትም ይደመጣል። አቶ ጌታቸው በባንክ አግልግሎት ዘርፍ ለመሠማራት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የሚያመሩት የውጭ አገራት ባለወረቶችና ተቋማት አብዛኛውን የገጠር ነዋሪ ችላ በማለት በከተሞች ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ የሚል ስጋትም አላቸው።

Äthiopien Textilindustrie
ምስል picture-alliance/dpa

የአዲስ አበባው የዘ-ኢኮኖሚስት ጉባኤ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጥረት በባንክ አገልግሎትና የፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ አሉ ያሏቸውን እንቅፋቶች ዘርዝረዋል። የአሜሪካው ጎልድማን ሳክስ ባንክ ሥራ አስኪያጅ ሰርጌ ስታንኮቭስኪ ኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎትን ለውጭ ተሳትፎ ክፍት እንድታደርግ ከወተወቱት መካከል ይገኙበታል። ሰርጌ ስታንኮቭስኪ «የኢትዮጵያ ባንኮች ቁጠባን በማሳደግ ግዙፍ እቅዶችን መደገፍ ወደሚያስችል የፋይናንስ አቅም መቀየር አልቻሉም።» ሲሉ ተናግረዋል። ስታንኮቭስኪ የአገሪቱ የቁጠባ መጠን በራሱ ለግዙፍ የሥራ እቅዶች በቂ አይደለም ሲሉ ተችተዋል። አቶ ጌታቸው ተ/ማርያምም የኢትዮጵያ ባንኮች ውስንነቶች በርካታ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የግል ባንኮች የውጭ ብድር የማግኘት እድላቸው አናሳ መሆን በዘ-ኢኮኖሚስት ጉባኤ ከተተቹ ጉዳዮች አንዱ ነው። በባንክ አግልግሎት ዘርፍ 70 በመቶው በመንግሥት ይዞታ ሥር በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ሀብት መሆኑ በዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም የሚጠቀስ ሌላ ትችት ነው። የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር እና የመንግሥት ጥብቅ ቁጥጥርም እንዲሁ። በአንጻሩ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ የተወሰነው የፋይናንስ ዘርፍ ምዕራባውያያን አንዴ መጣ ሌላ ጊዜ ሄደት እያለ ከሚያምሳቸው የኢኮኖሚ ቀውስ ለመዳኑ አንዱ ምክንያት የውጭዎቹን አለማስጠጋቱ እንደሆነ ይነገራል። ምዕራባውያን የገንዘብ ተቋማት የባንክ አገልግሎቱ ይከፈት ዘንድ ውትወታቸውን አዲስ አበባ ድረስ ዘልቀው ቢያሰሙም ለጊዜው ኢትዮጵያ «አይሆንም» የሚል ቆፍጣና መልስ ሰጥታለች።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ