1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ስደት

ዓርብ፣ ነሐሴ 16 2006

የኢትዮጵያ መንግስት ያስረናል ወይም ሌላ ጠንካራ እርምጃ ይወስድብናል ብለው የሚሰጉ የግል ጋዜጠኞች ሃገሪቱን ጥለው መሰደዳቸውን እንደ ቀጠሉ ነው።ከሳምንት በፊት ለግል መገናኛ ዘዴዎች ይሰሩ የነበሩ ሶስት ጋዜጠኞች ከሃገር ተሰደዋል።በያዝንው ሳምንት ደግሞ ሌሎች ሰባት ጋዜጠኞች ወደ ውጭ ሃገር ተሰደዋል።

https://p.dw.com/p/1CzVY
Zeitungen Äthiopien
ምስል DW

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት መንግስት ለትችት ትዕግስት አለመኖሩ፤የአገሪቱ የፍትህ ስርዓት ከፖለቲካ ጋር መደባለቁና ሚዲያን የማያበረታቱ አዋጆችንና ፖሊሲዎችን መኖራቸው ዋንኞቹ ምክንያቶች ናቸው።ላለፉት ጥቂት ወራቶች እንኳ ከግሉ ሚዲያ ብዙ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ወይም ሲሰደዱ ሌሎች የህትመት ውጤቶቻቸውን እንዲዘጉ ተገደዋል።ላለፉት 119 ቀናት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች የተከሰሱበት ምክንያት እንኳ ፤ተሟጋቾቹ እንደሚሉት፤ከታሰሩበት ቀን ጀምሮ ለ8ኛ ጊዜ እስከ ተቀጠሩበት ድረስ ያለው የፍርድ ሂደት ለብዙ ሚዲያዎች፤የህግ ተንታኞችና ጉዳዩን ለሚከታተሉ አካላት አነጋጋሪ ሆኖ ዘልቋል።የኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር በቅርብ ጊዜ ሎሚ፤እንቁ፤ጃኖ፤ፋክት መጽሄቶችና አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ የሃሰት ወሬ ነዝተዋል በሚል ከሷቸዋል።ይህንንም ተከትሎ ከሁለቱ መጽሄቶች ውጭ ቁጥራቸው 10 የሚሆኑ የተቀሩት መጽሄቶችና ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች አገር ጥለው ተሰደዋል።

የሎሚ መጽሄትና የአፍሮ ታይምስ ጋዜጣ ጠበቃ አቶ ተማም አባ ቡልጉ የክስ ሂደቱን ሲያስረዱ የተከሰሱበት ጭብጥ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ነው የሚል ነው። ይህም ከጸረ-ሽብር ህጉ ጋር የተያያዘ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ጋር የተያያዘ ነው።

Symbolbild Presse im Visier Pressefreiheit Grafik: DW

 

እነዚህ የሚዲያ ውጤቶች የክስ ወረቀት የደረሳቸው ህትመታቸው ከተዘጋ ወይም እንዳይታተም ከተደረገ ሁለት ሳምንታት በኋላ ሲሆን ህትመቶቹ ላይ የወጡ ጽሁፎችን እንደ ክስ ነጥብ አድርጎ አቃቢ ህግ አንስቷል።እንደ አቶ ተማም አገላለጽ የተጠቀሱት ነጥቦች እውነት የሚያስከስስ አለመሆኑን ተናግረው ለምሳሌ ሎሚ መጽሄት በሰኔ 6/2006 ይዞ በወጣው "በአለም በጨቋኝነቱ አቻ የማይገኝለት የሚዲያ ምህዳር በኢትዮጵያ በሚል ጽሁፍ ነበር።

አቶ ተማም ከ1997 በኋላ የወጡት ህገ ወጥ ህጎች ለምሳሌ የጸረ-ሽብር ህጉ አላስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው እንደምክንያትም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ያሉትን ወንጀሎች ለመቅጣት በቂ መሆኑን ይናገራሉ።

የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው በምህፃሩ ሲፒጄ የምስራቅ አፍሪቃ ዳይሬክተር ሚስተር ቶም ሮድስ በኢትዮጵያ ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱንና በእስር ቤት የሚገኙ ጋዜጠኞችም ቁጥር መጨመሩን ይናገራሉ።

ሲፒጄ ትናንት ባወጣው መግለጫ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ከመንግስት የሚደርስባቸውን ጫና በመሸሽ ከሃገር ለመሰደድ እየተገደዱ ነው።እዚያው ሃገር ውስጥ ለመቆየት የሞከሩት ደግሞ ለእስራት ይደረጋሉ።ጋዜጠኞቹ ለሚመሰረትባቸው ክስም ሆነ ለሚሰነዘርባቸው ጫና ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ምክንያት የለም እንd ድርጅቱ መግለጫ።ቶም ሮድስ እንደሚሉት ከ2001 ጀምሮ በነበሩት አምስት አመታት ውስጥ ብቻ ከ 40 በላይ ጋዜጠኞች አገር ጥለው ተሰደዋል።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ